አርሜኒያ እና አዘርባጃን ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ስጋት ተፈጠረ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሩሲያ አደራዳሪነት ሰላም ያወረዱት አዘርባጃንና አርሜኒያ ዳግም ወደለየለት ጦርነት እንዳይገቡ ተፈርቷል።
አዘርባጃን 4 ወታደሮቼ በአርሜኒያ ተገድለውብኛል ማለቷን ተከትሎ ነው ፍርሃት የነገሰው።
ወታደሮቹ የተገደሉት ለጦርነቱ ምክንያት በሆነው የናጎሮኖ ካራባህ ክልል ነው ብለዋል የአዘርባጃን መከላከያ ሚኒስትር።
አርሜኒያ በበኩሏ ከሠራዊቷ 6 የሚሆኑት ቆስለውብኛል ይህም የሆነው አዘርባጃን ተኩሳባቸው ነው ስትል ከሳለች።
ሁለቱ አገራት ለ6 ሳምንታት የቆየ ከባድ የሚባል ጦርነት አድርገው በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች በሁለቱም ወገን ካለቁ በኋላ በሩሲያ ሸምጋይነት የተኩስ አቁም ማድረጋቸው አይዘነጋም።
ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውም መፈናቀል ደርሶባቸዋል።
የሁለቱ አገራት ግጭት ናጎርኖ ካራባህ የተሰኘው ክልል ለኔ ይገባል በሚል የተደረገ ነበር።
ይህ ክልል የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕጋዊ የአዘርባጃን ክልል ነው ቢልም በአርሜኒያ የሚደገፉ የአርመን ዜጎች የሚኖሩበትና የሚያስተዳድሩበት ክልል ሆኖ ለዓመታት ቆይቷል። ይህም ከእአአ 1994 ጀምሮ እስከ 2020 የቆየ ነው።
ሁለቱ አገራት ከእአአ 1994 ቀደም ብሎ ከባድ የሚባል ጦርነት ቢያደርጉም ያለ ሰላም ስምምነት ጦርነቱ በማብቃቱ ለረዥም ጊዜ በጠላትነት ሲተያዩ ነው የኖሩት።
ከሳምንታት በፊት ሩሲያ በአወዛጋቢ ግዛቶቿ ሰላም አስከባሪ ማስፈሯ ይታወሳል። አርሜኒያ በቱርክ የሚደገፈውን የአዘርባጃንን ወታደራዊ ጥቃት መቋቋም ባለመቻሏ የሰላም ስምምነት ማድረጓ ይታወሳል።
በኖቬምበር 9 የተፈረመው የሰላም ስምምነት አዘርባጃን በጦርነቱ በጉልበት የተቆጣጠረቻቸውን ግዛቶቿን ይዛ እንድትቀጥል የሚያደርግ ነው።
የአወዛጋቢውን ክልል ሁለተኛዋን ትልቋን ከተማ ሹሻን የሚያካትት ነው።
አርሜኒያ በዚህ ስምምነት መሠረት ከሌሎች 3 ግዛቶች ጦሯን በማስወጣት ቦታዎችን ለአዘርባጃን ማስረከብ ይኖርባታል። 2ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ሰላም ለማስከበር በክልሉ እንዲሰማሩም ስምምነቱ ያዛል።
በዚህ ስምምነት አዘርባጃን ከቱርክ ጋር የሚያገናኛትን ቁልፍ መንገድ እንዲሁም የኢራንና ቱርክ ድንበር ስፍራ አግኝታለች።
በአጠቃላይ የሰላም ስምምነቱ ለአርሜኒያ ከፍተኛ ሽንፈት በመሆኑ አርሜኒያዊያን ቁጣቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚህ ጦርነት በትንሹ 5ሺ ወታደሮች መገደላቸው ይገመታል።
አሁን አገረሸ በተባለው ግጭት ሁለቱ አገራት አንዱ ሌላውን በመካሰስ ላይ ናቸው።
አርሜኒያ ጦርነቱን መቋቋም ባለመቻሏ የፈረመችውን የሰላም ስምምነት የአርሜኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን "ለኔም ለሕዝቤም እጅግ የሚያም ስምምነት ነው የፈረምኩት" ሲሉ ገልጸውት ነበር።












