እግር ኳስ፡ ህይወቱ በሱስ ምክንያት የተመሳቀለው የፕሪምየር ሊግ ቡድን አምበል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በጣም ብዙ እርዳታ አስፈልጎኝ ነበር። ወደ ሌላ አይነት ሕይወት ለመሸጋገር ከብዶኝ ነበር፤ ምክንያቱም ህይወቴን በሙሉ እግር ኳስን ብቻ ነበር የማውቀው። ከእንደዚያ አይነት ቦታ መውደቅ ከባድ ነው።"
ክላውስ ሉንደክቫም ቁርጭምጭሚቱ ላይ ባጋጠመው ተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት በአውሮፓውያኑ 2008 ከእግር ኳስ እራሱን እንዲያገል መገደዱን በተመለከተ የተናገረው ነው።
ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ደግሞ የአልኮልና የአደንዛኝ እጽ ሱሰኛ ሆነ።
ክላውስ በወቅቱ የ35 ዓመት እግር ኳስ ተጫዋች የነበረ ሲሆን በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በሚጫወተው ሳውዝሃምፕተን ውስጥ እጅግ የላቀ ብቃት አላቸው ከሚባሉት ተጫዋቾች መካከል ነበር።
ለቡድኑ ከ400 በላይ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1996 ነበር ከኤስኬ በርገን ሳውዝህምፕተንን የተቀላቀለው። በሳውዝህምፕተን ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ክብርና መወደድን ማግኘት ችሏል።
ክልጅነቱ ጀምሮ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መጫወት ህልሙ እንደነበር በተደጋጋሚ ይገልጻል። "የመጀመሪያም የመጨረሻም ፍላጎቴ በእንግሊዝ እግር ኳስ መጫወት ነበር" ይላል።
"የልጅነት ህልሜ ነው እውን የሆነው። እውነቱን ለመናገር ያንን ያክል ጊዜ ተፎካካሪ ሆኜ እቆያለሁ ብዬ አላስብኩም ነበር" ይላል የኖርዌይ ዜግነት ያለው ክላውስ። ከኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን ጋር በመሆንም 40 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል።
''ለእኔ ከሌላ አገር መጥቶ ለሳውዝህምፕተን ለ12 ዓመታት መጫወትና የቡድኑ አምበል ለመሆን መቻል ልዩ እና ትልቅ ቦታ ያለው ነገር ነው" ይላል።
በ2008 (እአአ) 18 ሺህ የሳውዝሀምፕተን ደጋፊዎች በተገኙበት ቡድኑ ሴልቲክን ገጥሞ ነበር። በወቅቱ ክላውስ ከነጉዳቱ ነበር ወደ ሜዳ ገባው። ነገር ግን የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ደቂቃዎች ከተጫወተ በኋላ ተቀይሮ ሲወጣ በከፍተኛ ጭብጨባ ነበር የተሸኘው።
ያቺ ዕለት ለክላውስ የእግር ኳስ ሕይወቱ ማብቂያ የመጀመሪያዋ ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከመጨረሻው ጨዋታ አንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ክላውስ ሉንደክቫም ሙሉ በሙሉ ሌላ ዓለም ውስጥ ገብቶ በሱስ የተጠመደ ሰው ሆኖ ነበር። የቀን ተቀን ሕይወቱን ይመራበት የነበረው የታቀደና በስልጠና የታገዘ የኑሮ ዘይቤው ሲቀየር እግር ኳስ ከህይወቱ ወጣ።
ለበርካታ ዓመታት የሚያውቀው ስልጠና ማድረግ፣ ለጨዋታ መጓዝ፣ እግር ኳስ መጫወት፣ ከጉዳት ማገገም የሚባሉት ነገሮች ታሪክ ሆነው ቀሩ።
ከእግር ኳስ በኋላ በሳውዝሃምፕተን የነበረው ቆይታ በተስፋ መቁረጥና በጭንቀት የተሞላ ነበር። ይህንን አስጨናቂ ጊዜ ለማለፍም ፊቱን ወደ አልኮልና ወደ አደንዛዥ እጽ አዞረ።
"በሕይወቴ በርካታ ስህተቶችን ሰርቻለሁ። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው በጣም ከባድ ጊዜ ነበር። በተለይ እግር ኳስ ተጫዋቾች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ተስፋና ትርጉም የሚሰጣቸው ነገር ሊኖር ይገባል። ከእግር ኳስ በኋላም ቢሆን የሚሰሩት ነገር መኖር አለበት።"
''እኔ በወቅቱ ሁሉም ነገር ነበረኝ። በጣም ብዙ ገንዘብ ነበረኝ፣ በጣም ምርጥ ቤተሰብ እና መኖሪያ ቤት ነበረኝ። ኖርዌይ ውስጥም የራሴ መኖሪያ ቤት ነበረኝ። ጀልባዎች፣ መኪናዎች፤ ሁሉም ነገር ነበረኝ። ነገር ግን በደግንገት ድብርት ውስጥ ገባሁና ብቸኝነት ተሰማኝ። የሚፈልገኝ ሰው እንደሌለ ተሰማኝ።"
"የእግር ኳስ መልበሻ ክፍሉን ናፈቅኩት። በየሳምንቱ ከቡድን ጓደኞቼ ጋር መሰልጠንና መጫወት አማረኝ። ይሄ ሁሉ ነገር በድንገት ከህይወቴ ሲጠፋ በጣም ከባድ ጊዜን እንዳሳልፍ አደረገኝ።"
በርካታ እግር ኳስ ተጫዋቾች ጫማቸውን ከሰቀሉ በኋላ በተመሳሳይ የህይወት መስመር ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ። እጅግ በተራቀቀውና ትንሿ ስህተት እንኳን ትልቅ ዋጋ በምታስከፍልበት የእግር ኳስ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በየቀኑ መጣርና መልፋት ግድ ይላል።
ይሄ ሁሉ ልፋትና የዕለት ተዕለት ስልጠና በአንድ ጊዜ ሲቋረጥ ተጨዋቾች ከፍተኛ ድብርትና የህይወት መመሰቃቀልና ትርጉም ማጣት ውስጥ ይገባሉ።
ምንም እንኳን ልክ እንደ ክላውስ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች የሚፈልጉት ነገር በሙሉ የተሟላላቸው ቢሆንም ከድብርት ግን ማምለጥ አይችሉም።
"በየቀኑ ስኬታማ ለመሆን መጣር፣ የውስጥ አቅምን አሟጥጦ መጠቀም፣ በየቀኑ እና በየሳምንቱ ምርጥ ሆኖ ለመገኘትና በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን ለማስደስት የሚደረገው ትግል በጣም አስደሳችና ሰውነትን የሚያነቃቃ ነው" ይላል ክላውስ።
ክላውስ ሉንደክቫም ከኖርዌዩ ኤስኬ ብራን ወደ ሳውዝሃምፕተን የተቀላቀለው በ350 ሺህ ፓውንድ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በነበረው የእግር ኳስ ህይወትም ሁሉም ተጫዋት ሊተማመንበት የሚችል አይነት ሰው ነበር። ምርጥና ቀጣይነት ያለው አቋም የሚያሳይ ተጫዋች ነበር። ነገር ግን ከእግር በኋላ የነበረው ማንነት ከመጀመሪያው በፍጹም የተለየ ነበር።
በአንድ ወቅት እንደውም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እስከመዋልና በሱሱ ምክንያት ሆስፒታል እስከመግባት ደርሶ ነበር።
"እግር ኳስ ካቆምኩኝ በኋላ ምናልባት ለትንሽ ዓመታት ቀለል ያለ ሕይወት መኖር አለብኝ ብዬ ለእራሴ ነገርኩት። በወቅቱ በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ እሳተፍ ነበር። በሄድኩበት ቦታ ሁሉ መጠጥ ነበር። በዚያውም ለመዝናናት እየተባለ መጠጥ ቤት መሄድ ተጀመረ።"
"ወዲያው እራሴን መቆጣጠር አቃተኝ። ከባድ ድብርት ውስጥም ገባሁ። ሳላስበው ከዚህ በፊት አይቼው በማላውቀው ሁኔታ እራሴን ተስፋ ቆርጬ አገኘሁት። ፊቴንም ወደ መጠጥና ኮኬይን አዞርኩኝ። ነገር ግን የአልኮልና የኮኬይን ጥገኛ ስሆን ነገሮች እንደውም እየከፉ መጡ።"
"በየቀኑ መጠጣትና አደንዛዥ እጽ መጠቀም ጀመርኩ። ባለቤቴ እና ሁለት ሴት ልጆቼ ወደ ኖርዌይ ተመለሱ።"
"ከአንዴም ሁለት ጊዜ እራሴን ለማጥፋት ሞክሬያለው። በጣም ከባድ ጭንቀት ውስጥ ገባሁና ሁሉም ነገር ትርጉም አጣብኝ። ድሮ የማውቀው ማንነቴ ጠፋብኝ። በወቅቱ የመረጥኩት ሁሉንም ለመርሳት አልኮል መጠጣት ነበር። ጥፋተኝነቴንና ሃፍረቴን ለመደበቅ ሁሌም መስከር ነበረብኝ።"
ምንም እንኳን ክላውስ ሉንደክቫም በጣም አስቸጋሪ የህይወት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት ብዙ ጊዜ ቢፈጅበትም እርዳታ ለመጠየቅ ግን አልቦዘነም ነበር። የቀድሞው የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ፒተር ኬይ ወዳቋቋመው የስፖርተኞች ክሊኒክ ገባ።
"የቀድሞው ሳውዝሀምፕተን አምበል እና በርካቶች እንደ ጀግናቸው የሚቆጥሩት የነበረው ሰው እንደዚህ ተሰብሮ ማየት ከባድ ነው። በወቅቱ በጣም ከባድ ቢሆንም አብረውኝ ለነበሩ ሰዎች ስሜንና ያለብኝን ችግር ስናገር ብዙዎቹ ይደነግጡ ነበር።"
ረጅም ጊዜ የፈጀው የማገገም ሂደት ቀላል አልነበረም። ተመልሶ አልኮል መጠጣትና ኮኬይን መጠቀምን ጨምሮ ሌሎች አስቸጋሪ ፈተናዎች ነበሩ በመሀል ላይ። ነገር ግን ቆራጥ መሆንና ሕይወትን ለመቀየር እራስን ማሳመን ወሳኝ መሆኑን ክላውስ ይናራል።
"በጣም ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ። ሁለት ጊዜ ወደ ሱሴ ተመልሼ ነበር። አሁን ጥቂት ዓመታት አልፎታል ግን ሱሰኛ መሆኔን አምኜ ለመቀበል ትንሽ ጊዜ ፈጅቶብኝ ነበር።"
"በነበረኛ ቆይታ ያለ አልኮልና አደንዛኝ እጽ ጥሩ ሕይወት መኖር እንደሚቻል እየገባኝ መጣ። በጣም ደስተኛ ሆንኩኝ፤ በእራሴም ኮራሁ። ምንም እንኳን ያሳለፍኩት ጊዜ ቀላል ባይሆንም አሁን ካለሁበት ሁኔታ ላይ በመገኘቴ በጣም እድለኛ ነኝ።"
ምንም እንኳን ክላውስ ሉንደክቫም እና ባለቤቱ በአውሮፓውያኑ 2014 ላይ ትዳራቸውን አፍርሰው ፍቺ ቢፈጽሙም አሁን ጥሩ የሚባል ግንኙነት ያላቸው። ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር ያለውም ግንኙነት ከምን ጊዜውም በበለጠ ጥሩ የሚባል ነው።
ክላውስ ለሳውዝሀምፕተን በሚጫወትበት ወቅት ስለ አእምሮ ጤና እና ጭንቀት ማውራት ብዙም የተለመደ ነገር አልነበረም። ነገር ግን አሁን ነገሮች በፍጥነት እየተቀየሩ ይመስላል። ሰዎች በህይወታቸው የሚገጥማቸውን ጭንቀትና አስቸጋሪ ነገር ማጋራት ጀምረዋል።
ክላውስ በአሁኑ ጊዜ አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙና ሱሰኛ የሆኑ ሰዎችን በመርዳት ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ከቀድሞ ክለቡ ሳውዝሀምፕተን ጋር በተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ ለመስራትም ፍላጎት አለው።
ከቀድሞ ቡድኑም ጋር ግንኙነት የፈጠረ ሲሆን በቡድኑ ታሪክ ስማቸው ከሚጠቀስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደመሆኑ፤ ተጫዋቾች ሊያጋጥሟችው ስለሚችሉ ፈተናዎች ግንዛቤ ማስጨጥ ደግሞ ህልሙ ነው።
















