እግር ኳስ፡ 'ከዘረኝነት መልዕክት' እስካልተጠበቁ ውጤቶች ያስመዘገበው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ

ፒኤስጂ እና ኢስታንቡል ባሻክሺር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትናንት ምሽት ፒኤስጂ እና ኢስታንቡል ባሻክሺር በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሊያደርጉት የነበረው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ በዕለቱ አራተኛ ዳኛ የዘረኝነት መልዕክት ተላልፏል በሚል ተጫዋቾች ሜዳውን ለቅቀው በመውጣታቸው ጨዋታው በድጋሚ ዛሬ ሊካሄድ እንደሆነ ተገልጿል።

ኢስታንቡል ባሻክሺር እግር ኳስ ክለብ እንዳስታወቀው አራተኛ ዳኛው ሴባስቺያን ኮልትስኩ ስለምክትል አሰልጣኙ ፒዬር ዌብ ሲናገሩ ዘረኛ የሆነ መልዕክት አስተላልፈዋል ብሏል።

የቀድሞ የካሜሩን ተጫዋቹ ዌቦ ከሜዳ ውጪ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኖም ነበር።

ይህንን ተከትሎ የኢስታንቡል ባሻክሺር ተጫዋቾች ሜዳውን ለቅቀው የወጡ ሲሆን የፒኤስጂ ተጫዋቾችም ተከትለዋቸው ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ክስተቱ የተፈጠረው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታው ተጀምሮ 14 ደቂቃዎች ያክል ከተጫወቱ በኋላ ሲሆን ተጫዋቾቹ ሜዳውን ለቅቀው እስከሚወጡ ድረስ ደግሞ ምንም አይነት ግብ አልተቆጠረም ነበር።

ጨዋታው ዛሬ ምሽት በድጋሚ እንደሚካሄድ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ያስታወቀ ሲሆን ትናንት ምሽት ማንቸስተር ዩናይትድ በአርቢ ላይፕሲዥ መሸነፉን ተከትሎ ደግሞ ፒኤስጂዎች ከጨዋታው በፊት ወደ ጥሎ ማለፍ ድልድል ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ባወጣው መግለጫ '' ከሁለቱም ቡድኖች ጋር ከተነጋገርን በኋላ ጨዋታው በድጋሚ ከቆመበት እንዲጀምርና ሌሎች ዳኛዎች ጨዋታውን እንዲመሩት ወስነናል'' ብሏል።

አክሎም ''በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እጅግ ፈጣንና ጥልቅ ምርመራ ይካሄዳል፤ የተጣሰ ህግ ካለም ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል'' ሲል አስታውቋል።

ተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረው የኢስታንቡል ባሻክሺር አጥቂው ዴምባ ባ ከአራተኛው ዳኛ ጋር ''ለምን ያኛው ጥቁር ሰው'' ብለህ መጥቀስ አስፈለገህ እያለ ሲከራከር ተስተውሏል።

በሌላ ምስል ደግሞ የፒኤስጂው ተከላካይ ''ይህ ሰው የምሩን ነው? በቃ እንሂድ'' ሲል ታይቷል።

ምንም እንኳን የፒኤስጂ ተጫዋቾች ለረጅም ሰአት መልበሻ ክፍሉ አካባቢ ሰውነታቸውን እያሟሟቁ ቢጠብቁም የኢስታንቡል ባሻክሺር ተጫዋቾች ባለመመለሳቸው ምክንያት ጨዋታው ለመቋረጥ ግድ ሆኗል።

የፒኤስጂው አጥቂ ኪሊያን ምባፔም በበኩሉ በትዊተር ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት ''ዘረኝነት ይብቃ። ዌብ አብረንህ ነን'' ሲል ጽፏል።

በሌሎች ጨዋታዎች በጉጉት ሲጠበቅ የማንቸስተር ዩናይትድና አር ቢ ላይፕሲዥ ጨዋታ በአርቢ ላእፕሲዥ 3 ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ምንም እንኳን ማንቸስተር ዩናይትዶት ከምድቡ ለማለፍ አቻ ብቻ የሚቃቸው የነበረ ቢሆንም በመጀመሪያዎች 20 ደቂቃዎች አርቢ ላይፕሲዦችን መቋቋም አቅቷቸው ተስተውሏል።

ጨዋታው በተጀመረ 13 ደቂቃዎች ውስጥም ሁለት ግቦችን አስተናግደው የመጀመሪያው አጋማሽ 2 ለባዶ የተጠናቀቀ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ሌላ ሶስተኛ ግብ አስተናግደዋል።

በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ ማንቸስተር ዩናይትዶች ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ቢችሉም አቻ ማድረግ ግን ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ከምድቡ አለማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል በሌላኛው የተጠበቀ ጨዋታ ጁቬንቱስ ባርሴሎናን 3 ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱን ግቦች ክርስቲያኖ ሮናልድ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረ ሲሆን ሶስተኛዋ ግብ ደግሞ ማክኬኒ በጨዋታ ማስቆጠር ችሏል።

ይህን ውጤት ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ከምድባቸው አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

ዛሬም የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን አትሌቲኮ ማድሪድ ከሬድ ቡል ሳልዝበርግ እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ከቦርሺያ ሞንቼግላድባክ የሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች የጁቬንቱሱ አልቫሮ ሞራታ፣ የቦርሺያ ዶርትሞንዱ ኢርሊንግ ሃላንድ እና የማንቸስተር ዩናይትዱ ማርከስ ራሽፎርድ በ6 ግቦች ኮኮብ ጎል አግቢነቱን እየመሩት ነው።