እግር ኳስ ፡ ለጡረታ እየተዘጋጁ ያሉት የ80 ዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች

ፒተር ዌብስተር

የፎቶው ባለመብት, FIGTREE FOOTBALL CLUB

ለእግር ኳስ ጥልቅ ፍቅር ያላቸው የ80 አመቱ የእድሜ ባለፀጋ እግር ኳስ ተጫዋች ከሰሞኑ የመጨረሻ ጨዋታዬን አደርጋለሁ ብለዋል።

በአውስትራሊያ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት እንግሊዛዊው ፒተር ዌብስተር ለጡረታም መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

በባለፉት ጥቂት አመታት አቅማቸው ደክሞ ከዚህ ቀደም በነበራቸው የሰውነት አቋም ባለመሆናቸውም ከሚወዱት የእግር ኳስ ጨዋታ ለመገለልም ምክንያት ሆኗቸዋል።

"ለባለፉት ጥቂት አመታት በእንደዚሁ አይነት ሁኔታ የነበርኩት። የምለብሰውንም ማልያ እያባከንኩ መሰለኝ" በማለትም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፒተር ዌብስተር የተወለዱት በጎሮጎሳውያኑ አቆጣጠር 1948 በእንግሊዟ ፕሬስተን ነው።

በህፃንነታቸው ራግቢና እግርኳስ ይጫወቱ የነበረ ሲሆን በተለይም ከአስራ አምስት አመታቸው በኋላ ዝንባሌያቸው ወደ እግር ኳስ ሆነ።

በፕሮፌሽናል ተጫዋችነትም በዌልስ ለሚገኙ ክለቦች በሃያዎቹና በሰላሳዎቹ እድሜያቸው ተጫውተዋል።

በ1981ም ከባለቤታቸውና ከሶስት ልጃቸው ጋር ወደ አውስትራሊያ የሄዱ ሲሆን እዚያም ባለው የእግር ኳስ ደረጃ ከፍተኛ መሆን አድናቆትን እንደፈጠረባቸውም ከሰሞኑ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ፒተር ዌብስተር

የፎቶው ባለመብት, Neil Webster

ለአስርት አመታትም በአውስትራሊያ ፊግትሪ የእግር ኳስ ክለብም ተጫውተዋል። የመጨረሻ ጨዋታቸውንም በያዝነው ሳምንት አርብ እለት እንዳደረጉም ተዘግቧል።

በክለቡም ሆነ በአካባቢው ከፍተኛ ዝናን ያተረፉት ፒተር በሳቸውም ስም ውድድር ተሰይሞላቸዋል- ፒተር ዌብስተር ካፕ የሚባል።

"እንዲህ አይነት ውድድሮች በስም የሚሰየሙት አንድ ሰው ገንዘብ ከከፈለ ወይም ከሞተ ነው። እኔ አልሞትኩምም አልከፈልኩም፤ እስቲ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ እሞክራለሁ" ብለዋል።

ለረዥም አመታት በእግር ኳስ ተጫዋችነታቸው ለመቆየት ሚስጥሩ ሳያቋርጡ መጫወታቸውና ከፍተኛ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ነው።

ለአመታትም ሩጫ፣ ሳይክል መንዳትን ያዘወትሩ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ከእድሜ ጋር ተያይዞ የልጅ ልጃቸውን ውሻ ይዘው ለመራመድ ይወጣሉ።

ምንም እንኳን እግር ኳስ ከመጫወት ራሳቸውን ቢያገሉም የልጅ ልጆቻቸው እግር ኳስ ሲጫወቱም እመለከታለሁ ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ራሳቸው ጨዋታ ስለነበራቸው የነሱን ጨዋታ መመልከት አልቻሉም ነበር።

ባለቤታቸውም በቤት ስራዎች እንዲያግዙዋቸው ጡረታ የሚወጡበትን ቀን በጉጉት እየጠበቀች እንደሆነም ተናግረዋል።

የፊግ ትሪ የእግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት ማይክ ዶድ የእድሜ ባለፀጋው እግር ኳስ ተጫዋች አስተዋፅኦ "ከቃላት በላይ ነው" በማለትም አሞግሰዋቸዋል።