የቀድሞው የጣሊያን ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ፓውሎ ሮሲ አረፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጣሊያን በ1982 (እአአ) የዓለም ዋንጫን ባሸነፈችበት ወቅት ኮከብ የነበረው ፓውሎ ሮሲ በ64 ዓመቱ ማረፉን ቤተሰቦቹ አሳወቁ።
ስፔን ውስጥ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የጣሊያን ብሔራዊ ቡደን ዋንጫውን ባነሳበት ጊዜ ፓውሎ ሮሲ ኮከብ ግብ አግቢና ተጫዋች በመሆን የተመረጠ ሲሆን ዝናው በዓለም ዙሪያ ናኝቶ ነበር።
ሮሲ በጣሊያን ሊግ ውስጥ እውቅናን ማግኘት የጀመረው ቪያቼንዛ ለተባለው ቡድን በተጫወተበት ጊዜ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የነበረ ሲሆን፤ ከዚያም ወደ ታዋቂዎቹ የጣሊያን ክለቦች ጁቬንቱስና ኤሲ ሚላን ተዘዋውሮ ተጫውቷል።
የጣሊያን መገናኛ ብዙሃን ሮሲ ለረጅም ጊዜ በህመም ከቆየ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ገልጸዋል።
የሮሲ ባለቤት ፌዴሪካ ካፔሌቲ ሞቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ከሮሲ ጋር አብረው የተነሱትን ፎቶ በመለጠፍ "ለዘላለም" የሚል ጽሁፍ አስፍራለች።
ባለቤቱ፤ ፓውሎ ሮሲ በምን ምክንያት ለሞት እንደበቃ ምንም ያለችው ነገር ግን የለም።
ሮሲ ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድን በተጫወተባቸው 48 ጨዋታዎች ላይ 20 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በሴሪ አ ለቪያቼንዛ፣ ፔሩጂያ፣ ለጁቬንቱስ፣ ሚላንና ቬሮና በተጫወተባት ጊዜ ከ100 በላይ ግቦችን አስቆጥሯል።
በ1077 (እአአ) ወደ ሴሪ አ እንዲያድግ ያደረገው ቪያቼንዛ ቡድን የሮሲ ሞት በክለቡ ላይ የፈጠረውን ስሜት "አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም የተሰማንን ህመም የምንገልጽባቸው ቃላቶችን እናጣለን" በማለት ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል።
ሮሲ በዓለም ዋንጫ የአገሩ ብሔራዊ ቡድን ዋንጫ እንዲያገኝ ካደረገ በኋላ በወቅቱ ለአውሮፓዊ የዓመቱ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች ይሰጥ የነበረውን የቦሎን ዶር ሽልማትን አግኝቶ ነበር።
ፓውሎ ሮሲ እግር ኳስ መጫወት ካቆመ በኋላ ለስካይ፣ ሚዲያሴት እና ራይ ለተባሉ የመገናኛ ብዙሃን የእግር ኳስ ተንታኝ ሆኖ ሰርቷል።















