ባሕል፡ መጠሪያ ስምን መቀየር እድል ያስተካክል ይሆን?

ቻይናዊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እውን መጠሪያ ስምን መቀየር የተሻለ ዕድል ያመጣ ይሆን? አንዳንድ የቻይና ማህበረሰቦች በዚህ ሀሳብ በእጅጉ ይስማማሉ።

በአንድ የሚያዝያ ከሰአት ላይ ማንዲ ፓንግ በጣም የምትፈራው ነገር ተፈጠረ። የስራ አለቃዋ በዙም ስብሰባ ላይ በድንገት እንድትካፈል አጭር ትዕዛዝ ሰጧት። የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ ባደረሰው ጫና ምክንያት ከስራ መቀነሷ ተነገራት።

ነዋሪነቷን በሆንግ ኮንግ ያደረገችው የ29 ዓመቷ ማንዲ በጣም ተናደደች፤ አዘነች። ትንሽ ወደኋላ መለስ በማለትም ከዚህ በፊት ስላጋጠሟት መጥፎ ነገሮችና ዕድሎች ማስታወስ ጀመረች።

ከስራዋ ከተቀነሰች አንድ ወር በኋላ አሁንም ስራ አጥ ነበረች። ከዚህ በኋላ ነበር ምን ማድረግ እንዳለባት እርግጠኛ የሆነችው። በእሷ አጠራር መጥፎ ዕድል እያመጣብኝ ነው ያለችው ሕጋዊ መጠሪያ ስሟን መቀየር ነበር የመጨረሻ አማራጭ ያደረገችው።

''አንዲት የእናቴ ጓደኛ መጠሪያ ስሜን ብቀይር መጥፎ እድልን ማባረር እንደምችልና ስለእኔ መትፎ የሚያስቡ ሰዎችን መራቅ እንደምችል ነገረችኝ''

በቻይና ባህል መሰረት የሰዎች መጠሪያ ትርጓሜ ትልቅ ቦታ ያለውና ብዙ ነገሮችን መወሰን ሚችል እንደሆነ ይታመናል። በሰሜናዊ እስያ የሚገኙ ቻይናውያን ደግሞ የሰዎች ስም ሕይወታቸውን፣ ጤናቸውን፣ ስኬታቸውን፣ የፍቅር ሕይወታቸውን እንዲሁም ዕድላቸውን የመወሰን ኃይል አለው ብለው ያምናሉ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚዎች ላይ ያሳደረው ጫና እየበረታ ሲሄድ ደግሞ እንደ ማንዲ ፓንግ ያሉ በርካቶች እራሳቸውን ስራ አጥ ሆነው ያገኛሉ። ታዲያ ስራ ለመፈለግ ሲቪያቸውን ማሰማመር ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን እንተነብያለን ወደሚሉ ሰዎችም ፊታቸውን እንዲያዞሩ አስገድዷቸዋል። አብዛኛዎቹ ምክር ደግሞ ለምን መጠሪያ ስማችሁን አትቀየሩም? ነው።

''ቻይናውያን ሕይወታቸውን የመወሰን አቅም ያላቸው 10 ነገሮች አሉ ብለው ያምናሉ'' ይላል በሆንግ ኮንግ አሉ ከሚባሉት የወደፊቱን ከሚተነብዩ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሊ ሺንግ ቻክ። አክሎም ''ሰዎች ከሚወለዱበት ቀን እና ጥሩ ነገር ከመስራት በተጨማሪ መጠሪያ ብዙ ነገሮችን የመቀየር አቅም ያለው ነው'' ብሏል።

ማንዲ ፓንግም ብትሆን ስሟን መቀየሯ እያጋጠማት ያለውን መጥፎ ዕድል እንደሚቀይርላት በጽኑ ታምናለች።

ላውራ

የፎቶው ባለመብት, laura yep

በዚህ ጥንታዊ ባህል መሰረት አንድ ሕፃን የተወለደበትን ትክክለኛ ጊዜ በጥንቃቄ ከተመረመረ በኋላ ወሳኝ ከሚባሉት የቻይናውያን መገለጫዎች (እሳት ፣ እንጨት ፣ ውሃ ፣ ብረት እና ምድር) መካከል በኮከብ ቆጠራ በየትኛው መሰየም አለበት የሚለው ይወሰናል።

በተጨማሪም ደዲስ የሚወለደው/ የምትወለደው ልጅ፣ የሚሰጠው/ የሚሰጣት ስም ለጆሮ ተስማሚ የሆነና የወደፊት ዕድልን የሚያሳካ እንዲሆን ብዙ ነገሮች ከግምት ውስጥ ይገባሉ።

ስለዚህ ሰዎች ካደጉ በኋላ በሕይወታቸው ደስተኛ ካልሆኑና መጥፎ ዕድል እያጋጠማቸው እንደሆነ ካመኑ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ከግምት ውስጥ አስገብተው ሌላ ጥሩ ዕድል የሚያመጣ ስም ይፈልጋሉ።

ሁሉም የወደፊቱን እተነብያለው የሚል ሰው በርካታዎቹን መመዘኛዎች በተለያየ መንገድ መረዳቱን መተርጎሙ ደግሞ ብዙ የስም አማራጭ እንዲኖር ያደርጋል ይላል ሊ።

በተመሳሳይ በቻይናዋ ጉዋንግዶንግ የሚኖረው ቺን ፎኩን ስሙን ከቀየረ አራት ዓመታት ማለፋቸውን ይገልጻል። በወቅቱ የመተንፈሻ አካላለት በሽታ ለወራት ያሰቃየው ነበር። ምንም እንኳን በርካታ የሕክምና ቦታዎች ቢሄድም ምንም ፈውስ ማግኘት አልቻለም።

''እናቴ ስሜን እንድቀይር ነገረችኝ። በወቅቱ በሽታው ለረጅም ጊዜ ሲያሰቃየኝ የነበረ ቢሆንም ልክ መጠሪያ ስሜን ከቀየርኩ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ ከሕመሜ ዳንኩኝ'' ይላል።

ነገር ግን የ24 ዓመቱ ቺን አሁንም ቢሆን ስሙን መቀየሩ ብቻ ከህመሙ እንዳዳነው ሙሉ በሙሉ አያምንም። ''ምናልባት እድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ ሰውነቴ የመከላከል አቅሙን አዳብሮ ሊሆን ይችላል''

ምንም እንኳን መጠሪያ ስምን መቀየር በሕይወታችን ብዙ ለውጦችን ስለማምጣቱ በሳይንሳዊ መንገድ ምንም የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም በርካቶች ግን በስፋት የሚያምኑበት ጉዳይ ነው።

በሲንጋፖር ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዛንግ ያን በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ምርምሮችን አካሂደዋል።

''ሰዎች ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ይፈልጋሉ፤ በተለይ ደግሞ እየሆኑ ስላሉ ነገሮች እርግጠኛ መሆን ሲያቅታቸው። ሰዎች ስማቸውን ሲቀይሩ በሕይወታቸው የሚሆነውን ነገር እየተቆጣጠሩ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ምናልባት ምንም የሚቀይሩት ነገር ላይኖር ይችላል፤ ነገር ግን ጭንቀቱ ስለሚቀንስላቸው እውነትም ነገሮች እየተስተካከሉ ይሄዳሉ'' ይላሉ።

ሆንግ ኮንግ ውስጥ የሚኖረው የላውራ ዪፕ ቤተሰቦች የእነሱን ምክር ተቀብላ የ23 ዓመቷ ወጣት ስሟን ከቀየረች በኋላ ከሰዎች ጋር ያላት ግንኙነት መሻሻሉንና ነገሮች መቀየራቸውን ያምናሉ።

''መላው ቤተሰቤ ስሜን እንድቀይር ይፈልግ ነበር። አጎቴ ስሜን ከቀየርኩ በቶሎ ትዳር እንደምመሰርት የነገረኝ ሲሆን እናቴ ደግሞ ስሜን ከቀየርኩ እድሌ እንደሚሰምርልኝ ነገረችኝ። እኔም በዚህ ነገር አምናለሁ''

ላውራ ዪፕ በሕጋዊ መንገድ ስሟን ለመቀየር ቀላል የሚባል ወጪ አይደለም ያደረገቸው። 1 ሺ 930 ዶላር መክፈል ግድ ያላት ሲሆን የተቀየረውን ስሟን በአገሪቱ መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ ደግሞ ተጨማሪ 500 ዶላር መክፈል ነበረባት።

ይህ መጥፎ ነገር ሲያጋጥም ስምን የመቀየር ልምድ በቻይና ብቻ የሚታይ ነገር አይደለም። በአውሮፓውያኑ 2016 ላይ ደቡብ ኮሪያ ከፍተኛውን የስራ አጥ ቁጥር ባስመዘገበችበት ወቅት ብቻ 150 ሺ ሰዎች ስማቸውን ለመቀየር ጥያቄ አቅርበዋል።

የሆንግ ኮንግ መንግስት ባወጣው መረጃ መሰረትም በርካታ ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ስማቸውን ለመቀየር ጥየቄ አቅርበዋል። በ2020 የመጀመሪያ ወራት ብቻ 1 ሺ 252 ሰዎች ስማቸውን ለመቀየር ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በ2109 ደግሞ 1 ሺ 600 ሰዎች በተመሳሳይ ስማችንን መቀየር እንፈልጋለን ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።