እግር ኳስ፡ ዩናይትድ፣ አርሴናል፣ ቼልሲ . . . ምን አስበዋል?

አላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አላንድ

የስፖርት ጋዜጦች ስለ እግር ኳስ ምን እያሉ ነው? በሚቀጥለው ጥር የሚከፈተው የዝውውር መስኮትስ ምን ያሳየን ይሆን?ዋና ዋናዎቹን በዚሀች አጭር ዘገባ እንዳስሳለን።

አላንድ፡ የቦሩሲያ ዶርትመንዱ አጥቂ ኧርሊንግ ብራውት አላንድ ፈላጊው በዝቷል። አሁን ደግሞ ቼልሲዎች ተጫዋቹን ለማስፈረም ዕቅድ እንዳላቸው እየተነገረ ነው።

ነገር ግን ማንቸስተር ሲቲዎች ተጫዋቹ የእኛ ነው እያሉ ነው። ይህን የዘገበው '90 ሚኒት' ጋዜጣ ነው።

ቼልሲ አላንድንና የዌስትሃሙን ዴክሌን ራይስ ለማስፈረም ሰባት ተጫዋቾቹን ሊሸጥ እንደሚችል ስካይ ስፖርት ዘግቧል። ባርክሌይ፣ አሎንሶ፣ ሩዲገር፣ ክሪስቴንሰን፣ ጆርጊንሆ፣ ድሪንክዎተርና ሞሰስ ለገበያ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተነግሯል።

በሌላ በኩል ማንቸስተር ዩናይትድም አላንድን ማስፈረም ይፈልጋል።

ነገር ግን የተጫዋቹ ወኪል የሆነው ሚኖ ራዮላ ከዩናትድ ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊ ስላልሆነ ችግር ሊፈጥር ይችላል እየተባለ ነው ይላል ሚረር ባወጣው ዘገባ።

ዩናይትድ አላንድን ማስፈረም ካልቻለ ፊቱን ወደ ኤቨርተኑን ዶሞኒክ ካልቨርት-ሌዊን ሊያዞር ይችላል።

ሩዲገር፡ ቼልሲ ሊሸጣቸው ካሰባቸው ተጫዋቾች መካከል የሆነው ጀርመናዊው አንቶኒዮ ሩዲገር በፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን ይፈለጋል። ይህን ያተመው የፈረንሳዩ 'ለ ፓሪዚያ' ነው።

ሊቨርፑል፡ ቀያዮቹ የሪያል ማድሪዱን ብራዚላዊ ተከላካይ ኤደር ሚሊቶን ለማስፈረም አቅደዋል። አርጀንቲናዊው የ34 ዓመት ተጫዋች እዝቄል ጋሬይም በሊቨርፑሎች እየተፈለገ ነው። ይህን ዜና ያሰማው የስፔኑ ቶዶፊቻሄስ ነው።

አርሴናል፡ የመድፈኞቹ አሠልጣኝ ማይክል አርቴታ የሪያል ማድሪዱን ብራዚላዊ አጥቂ ቪኒሺዬስ ጁኒዬርን ወደ ኤሜሬትስ ለማምጣት አቅደዋል።

የ22 ዓመቱ አጥቂ ወደ ኤሜሬትስ በሚቀጥለው ጥር ወር በውሰት ሊመጣ ይችላል ተብሏል።

አርቴታ ከወጣቱ አጥቂ በተጨማሪ የ28 ዓመቱን ስፔናዊ አማካይ ኢስኮ፤ ይፈልገዋል። ነገር ግን ተጫዋቹ ወደ ዩቬንቱስ መሄድን ይመርጣል - 'የደይሊ ስታር' እንደዘገበው።

ባርሴሎና፡ የካታሎኑ ክለብ የአርሴናሉን ተከላካይ ሹከርዳን መስጣፊን ይፈልገዋል ይላል 'ስፖክስ' ጋዜጣ። የ28 ዓመቱ ሙስጣፊ ከአርሴናል ጋር ያለው ውል እየተገባደደ ነው።

ጆንስ፡ የደርቢ ካውንቲ አሠልጣኝ የሆነው ዋይኒ ሩኒ የቀድሞ የቡድን አጋሩ ፊል ጆንስን ማስፈረም ይሻል። እንደ 'ሜትሮ' ዘገባ ከሆነ በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ዕድል ያጣው ጆንስ በዌስትብሮምም ይፈለጋል።

የአውሮፓ እግር ኳስ የዝውውር መስኮት በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ጥር ወር ይከፈታል። ማን ወደ የት ይሄዳል? ጊዜ ይፈታዋል።