ኮሮናቫይረስ ፡ ወደ ታይዋን ኮቪድ-19 ቫይረስ አስገብቷል የተባለው አብራሪ ከሥራ ተባረረ

ኢቫ ኤር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኮሮናቫይረስን ወደ ታይዋን ይዞ ገብቷል የባለ ኒው ዚላንዳዊው የአውሮፕላን አብራሪ ከሥራ ተሰናብቷል።

ሰውዬው ታይዋን ውስጥ ከወራት በኋላ ለተከሰተው የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ሥርጭት ተጠያቂ ነው ተብሎ ነው ከሥራው የተባረረው።

አብራሪው ኢቫ ኤይር ለተሰኘው የታይዋን አየር መንገድ ይሰራ የነበረ ሲሆን፤ ባለፈው ማክሰኞ ከአብራሪው ጋር ግንኙነት የነበረው ግለሰብ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘበት ተገልጿል።

ታይዋን ለ253 ቀናት አንድም በአገር ውስጥ ያለ ሰው በኮቪድ-19 አልተያዘባትም ነበር።

ይህ ዜና ከተሰማ ወዲህ መንግሥት ሕዝቡ የገና በዓል ግርግሩን ገታ እንዲያደርገው አሳስቧል።

ከገና ተከትሎ የሚከበረው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ቀንም ሰዎች ከቤታቸው ንቅንቅ እንዳይሉ ተነግሯቸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ማናወጥ ከጀመረ ወዲህ ታይዋን 777 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሲሆን ሰባት ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን አሳውቃለች።

የአውሮፕላን አብራሪው በቫይረሱ የተያዘው በያዝነው የታኅሣሥ ወር መግቢያ ላይ ቢሆንም ምንም የበሽታው ምልክት ግን አልነበረውም ተብሏል።

አብራሪዎች ወደ ታይዋን ሲመጡ ለሦስት ቀናት ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ የሚገደዱ ቢሆንም ምልክት ካላሳዩ ምርመራ እንዲያደርጉ አይመከሩም።

ሰውዬው ምልክት ባይኖረውም ከዩናይትስ ስቴትስ አውሮፕላኑን እያበረረ ሲመጣ ግን ሲያስል ነበር ተብሏል።

ይህንንም ተከትሎ አብራሪው መሬት እንዳረፈ ምርመራ ተደርጎለት ቫይረሱ እንዳለበት ተደርሶበታል።

የታይዋን ባለሥልጣናት አንድ ሰው ቫይረሱ እንደተገኘበት ካረጋገጡ በኋላ ከየት ነው የመጣውን የሚለውን ሲያጣሩ ነበር አብራሪው ላይ የደረሱበት።

ኒው ዚላንዳዊው አብራሪ ከመመርመሩ በፊት ከማን ጋር ግንኙነት እንደነበረው ባለማሳወቁ ነው ሥራውን ያጣው።

ሰውዬው በዚህ ጥፋቱ 300 ሺህ የታይዋን ዶላር [415 ሺህ ብር ገደማ] እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

ኢቫ ኤይር አብራሪው ከሥራው የተሰናበተው የአየር መንገዱን ደንብ ባለማክበሩና የአውሮፕላኑ ጋቢና [ኮክፒት] ውስጥ ሳለ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረጉ ነው ብሏል።

ሰውዬው ከአንዲት ሴት በተጨማሪ ሁሉት የሥራ አጋሮቹንም በበሽታው እንዲያዙ አድርጓል ተብሎ ተወቅሷል።

ስሙ ያልተጠቀሰው ይህ አብራሪ "ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት" ችላ ብሏል የሚል ትችት ገጥሞታል።

ታይዋን ኮሮናቫይረስ በአውሮፕላን ተሳፍሮ ወደ አገሯ መግባቱን ከሰማች ወዲህ ጥብቅ የመከላከያ መንገዶች እንደ አዲስ ለመዘርጋት አቅዳለች።

ቫይረሱን ከአብራሪው ተላልፎባታል ከተባለችው ሴት ጋር በአንድም ሆነ በሌላም መንገድ ግንኙት አላቸው የተባሉ 170 ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

የቻይና ጎረቤት የሆነችው ታይዋን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ጥብቅ እርምጃ ከወሰዱና ከተሳካላቸው ጥቂት የዓለማችን ግዛቶች መካከል ናት።

የታይዋን 23 ሚሊዮን ነዋሪዎችም በሽታውን ለመከላከል ከባለሥልጣናት የሚሰጡ መመሪያዎችን በማክበር አስተዋፅዖ አበርክተዋል ተብለው ይመሰገናሉ።