'ግማሽ ቢሊዮን ቻይናዊያን ከመጠን በላይ ክብደት ጨምረዋል'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነብስ ካወቁ ቻይናዊያን መካከል ከግማሽ በላዩ ወይም ደግሞ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ቻይናዊያን ከመጠን በላይ ክብደት መጨመራቸውን አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።
ቻይናዊያን ክብደት መጨመር የጀመሩት ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ ነው ይላል ጥናቱ።
በወቅቱ 29 በመቶ ቻይናዊያን ብቻ ነበሩ ከመጠን በላይ ክብደት የነበራቸው።
ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያሳየችው ያለው የምጣኔ ሃብት እመርታ በብዙ ዜጎቿ የአኗኗር ዘይቤ ላይ ለውጥ አምጥቷል።
አመጋገብ ተቀይሯል፤ አካላዊ እንቅስቃሴም እንዲሁ።
ከመጠን ያለፈ ክብደት መጨመር ለልብ በሽታ፣ ለስትሮክ እና በተለምዶ ስኳር በሽታ ተብሎ ለሚታወቀው ዳያቢቲስ ሊያጋልጥ ይችላል።
የቻይናዊያን ክብደት መጨር ጉዳይ ዓይን ውስጥ መግባት የጀመረው በተለይ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወዲህ ነው።
ከመጠን ያለፈ ክብደት ያላቸው ሰዎች ከሌሎች በላቀ ሁኔታ በኮሮናቫይረስ የመሞት ዕድላቸው የሰፋ ነው።
ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን ረቡዕ ዕለት ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ከ50 በመቶ በላይ ቻይናዊያን ከመጠን ያለፈ ክብደት አላቸው።
ከእነዚህ መካከል 16 በመቶው ደግሞ እጅግ መጠን የለሽ ክብደት አላቸው ይላል ዘገባው።
የኮሚሽኑ መግለጫ ከ18 ዓመት በላይ ከሆኑ ቻይናዊያን ሲሶው ብቻ ናቸው ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ይላል።
አልፎም የቻይናዊያን አንጀት ለስጋ መከፈቱና ለፍራፍሬ ያለው አመለካከት የተዛባ መሆኑ ለክብደት መጨመር ምክንያት ነው ተብሏል።
የአመጋገብ ሥርዓት ባለሙያው ዋንግ ዳን በርካታ ቻይናዊያን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አይሠሩም፣ ጫና አለባቸው፣ የሥራቸው ፀባይም ጤናማ አይደለም ይላሉ።
ቻይና፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዜጎቿ ከመጠን በላይ ክብደት የጨመሩባት ብቸኛዋ ሃገር አይደለችም።
ከወራት በፊት የዓለም ጤና ድርጅት በመላው ዓለም መጠን ያለፈ ክብደት ከ45 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በሶስት እጥፍ ጨምሯል ብሎ ነበር።
እንደ ደርጅቱ ከሆነ ከ40 በመቶ በላይ ነብስ ያወቁ ሰዎች ከመጠን በላይ ክብደት ጨምረዋል።
ትንሽዬዋ የባሕረ ሰላጤ ሃገር ኳታር በክብደት መጨመር ወደር አልተገኘላትም ተብሏል።
ከ70 በመቶ በላይ የሃገሪቱ ሰው ከመጠን ያለፈ ክብደት አለው ይላሉ ጥናቶች።













