ትዊተር የዶናልድ ትራምፕን 33 ሚሊዮን የትዊተር ተከታዮች ለጆ ባይደን አላወርሳቸውም አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እጅግ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አንዱ የሆነው የትዊተር ኩባንያ ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በኋላ ሥልጣን ሲለቁ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆናቸው ምክንያት ያገኙትን የትዊተር ስምና ተከታዮች ለመጪው ተመራጭ ፕሬዝዳንት አላወርስም ብሏል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተከታዮች በሙሉ ከገጹ ከተሰረዙ በኋላ ነው ጆ ባይደን ከዜሮ ተከታይ እንዲጀምሩ የሚደረገው ሲል ኩባንያው አስታውቋል።
የጆ ባይደን ድጋፍ ሰጪ ቡድን ግን ትዊተር የትራምፕን ተከታዮች በሙሉ ለጆ ባይደን አሳልፎ እንዲሰጥ ከፍተኛ ውትወታና ጫና ሲያደርጉ ነበር።
ትዊተር ኩባንያ ይህ የማይናወጽ አቋሜ ነው። የፕሬዝዳንቱን ተከታዮች በሙሉ እደልዛለሁ ሲል የመጨረሻ ውሳኔውን አሳውቋል።
በፈረንጆቹ 2016 ትራምፕ ወደ መንበረ ሥልጣኑ ሲመጡ የባራክ ኦባማ 13 ሚሊዮን የትዊተር ተከታዮች በሙሉ ወደ ዶናልድ ትራምፕ እንዲሸጋገሩ ተደርጎ ነበር።
አሁን ትዊተር ይህን አሰራሩን ለምን እንደቀየረ ያለው ነገር የለም።
በታሪክ ትዊተርን ለመጠቀም የመጀመርያው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ቢሆኑም መድረኩን በስፋት 'ለልማትም ሆነ ለጥፋት' የተጠቀሙበት ትራምፕ እንደሆኑ ይነገራል።
በእርግጥ የዛሬ 4 ዓመት ትዊተር የባራክ ኦባማን ተከታዮች ወደ ዶናልድ ትራምፕ ያወረሰው ከትራምፕ ቡድን በቀረበለት ጥያቄ ነበር።
ስለዚህ ትራምፕ የትዊተር ተከታዮቻቸው 13 ሚሊዮን ሆነው ጀምረው ነው 33 ሚሊዮን ያደረሱት። ጆ ባይደን ግን ከ3 ሳምንት በኋላ ዋይት ሐውስ ሲገቡ የትዊተር ተከታዮቻቸው ብዛት ዜሮ ሆኖ ነው የሚጀምሩት።
ትራምፕ ከ4 ዓመታት በፊት የተሰጣቸው የትዊተር ተከታዯች የመውረስ እድል ለባይደንም እንዲሰጥ የጆ ባይደን ቡድን ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ አይቻልም ተብሏል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የትዊተር ስም በእንግሊዝኛ @POTUS ይሰኛል።
ትራምፕ ከ4 ዓመታት በፊት የወረሱት ይህንን ስምና ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የዋይት ሐውስ ጽሕፈት ቤቱ የሚያንቀሳቅሰውን @WhiteHouse ተከታዮችን ጭምር ነበር።
ይህ ግን በ2020 ሊደገም አልቻለም። ትዊተር ባይደን ከዜሮ እንዲጀምር ነግሮናል ብለዋል አንድ የባይደን ረዳት።
ትዊተር በበኩሉ ትራምፕን በትዊተር እየተከተሉ ያሉ ሰዎች በሙሉ ባይደንን ይከተሉ ይፈልጉ እንደሆነ ምርጫ ይሰጣቸዋል። ካልሆነ ግን ከትራምፕ ጋር የነበራቸው ታሪክ ወደ ማኀደር ክፍል ይገባል። በቀጥታ ጆ ባይደንን እንዲከተሉ ግን አይደረግም ብሏል።
የጆ ባይደን የግል የትዊተር ስም @JoeBiden ሲሆን 21.7 ሚሊዮን ተከታዮች ብቻ ነው ያሉት።
ትራምፕ የትዊተር ሰሌዳቸውን በአግባቡ ለግልና ለሥራ በመጠቀም ብዙ ተከታይ ማፍራታቸው ይነገራል። ብዙውን ጊዜ የካቢኔ ሹመⶉችን እንኳን ለማሰናበት ትዊተር ሰሌዳቸውን ሲጠቀሙበት ነበር።
በርካታ የዓለም ሚዲያዎችም ትኩስ መረጃ ለማግኘት የትራምፕ የትዊተር ሰሌዳ ሁነኛ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐውስን ከረገጡ ጀምሮ 50ሺህ ጊዜ በሰሌዳቸው ላይ መረጃን ጽፈው አሰራጭተዋል።
ፋክትቤት የተሰኘ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን የሚተነትን ዌብሳይት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ከጥቅምቱ ወር የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወዲህ ትራምፕ የትዊተር ተከታዮቻቸው ቀንሰውባቸዋል። በትዊተር ሰሌዳቸው 369ሺህ 849 ተከታዮችን ማጣታቸውን ይፋ አድርጓል፥ ፋክትቤት።
በአንጻሩ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ጆ ባይደን 2 ሚሊዮን 671 ሺህ 790 አዳዲስ ተከታዮችን አፍርተዋል።
ይህ የትራምፕን ተከታዮች ለጆ ባይደን በቀጥታ አላወርስም የሚለው የትዊተር ውሳኔ ይፋ ከመደረጉ በፊት የትዊተር ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ ትራምፕን፥ ባይደንን እና ከማላ ሐሪስን በግሉ መከተል ማቆሙ ተዘግቦ ነበር።












