ሊዮኔል ሜሲ ቫላዶሊድ ላይ ባስቆጠራት ግብ የፔሌን ክብረ-ወሰን ሰበረ

ሜሲ በጨዋታው 65ኛ ደቂቃ ላይ በሪያል ቫላዶሊድ ላይ ግብ ሲያስቆጥር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሜሲ በጨዋታው 65ኛ ደቂቃ ላይ በሪያል ቫላዶሊድ ላይ ግብ ሲያስቆጥር

ከዓለማችን ኮከብ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሊዮኔል ሜሲ 644ኛ ጎሉን ለክለቡ ባርሴሎና በማስቆጠር የፔሌን ክብረ ወሰን ሰብወል።

ሜሲ የከፍተኛውን ግብ ክብረ ወሰን በእጁ ለማስገባት የቻለው ቡድኑ ባርሴሎና ከሪያል ቫላዶሊድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ላይ ከመረብ ያገናኘው ጎል ነው።

በዚህም ሜሲ ለአንድ ክለብ ብዙ ጎሎች በማስቆጠር የብራዚላዊውን እግር ኳሰኛ ፔሌ ክብረ ወሰን ሰብሯል።

የ33 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ባርሴሎና ሪያል ቫላዶሊድን ባሸነፈበት ጨዋታ ከክለብ አጋሩ ፔድሪ የተቀበላትን የቅንጦት ኳስ ወደ ጎል ቀይሮ ነው ክብረ ወሰኑን የጨበጠው።

ሊዮኔል ሜሲ በትላንቱ ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።

ብራዚላዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ ፔሌ ለሳንቶስ ክለብ ከ1956 እስከ 1974 ተጫውቷል።

ለ19 የውድድር ዘመኖች ለአገሩ ክለብ የተጫወተው ፔሌ 643 ጎሎች ከመረብ ማገናኘት ችሏል።

ሜሲ ለባርሳ የመጀመሪያ ጎሉን ያሰቆጠረው በፈረንጆቹ 2005 ነበር።

አርጀንቲናዊው አጥቂ ከባርሳ ጋር 10 ጊዜ የላሊ ጋ ዋንጫ አንስቷል። 4 ጊዜ ደግሞ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ባለድል ሆኗል።

አጥቂው በአሁኑ ወቅት ከክለቡ ጋር ያለው ውል እየተገባደደ ነው። በሚቀጥለው ጥር ከሚፈልጉት ክለቦች ጋር መደራደር ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሜሲ ባለፈው ነሃሴ ከባርሴሎና በነፃ መሰናበት እፈልጋለሁ ብሎ ጥያቄ ቢያቀርብም ክለቡ ውድቅ አድርጎበት ነበር።

በወቅቱ ባርሴሎና ሜሲን የሚፈልግ ክለብ 700 ሚሊዮን ዩሮ ማቅረብ አለበት ሲል ጠይቋል።

ሜሲ፤ ይህ ከክለቡ ጋር የነበረው አለመግባባት በእግር ኳስ ሕይወቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮበት እንደነበር ተናግሯል።

ማክሰኞ ምሽት ከቫላዶሊድ ጋር የነበረውን ጨዋታ የረታው ባርሴሎና ከስምንተኛ ደረጃ ወደ አምስተኛ ከፍ ብሏል።

ባርሴሎና ላ ሊጋውን እየመራ ካለው አትሌቲኮ ማድሪድ ስምንት ነጥብ ዝቅ ብሎ ይገኛል።