ሜሲ ከባርሴሎና ጋር ይቆያል፡ ፔፕ ጋርዲዮላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ የስፖርቱ ቤተሰቦች ሰሞኑን አንድ ነገር ላይ ስምምነት ነበራቸው። የስድስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ጋር ሰሞኑን የፈጠረው ቅራኔ መዳረሻውን ማንችስተር ሲቲ ያደርጋል የሚል።
"ሜሲ የእግር ኳስ ዘመኑን በባርሳ የሚያጠናቅቅ ይመስለኛል፤ የማምነውም እንደዚያ እንደሚሆን ነው" በማለት የማንቺስትር ሲቲው አለቃና የቀድሞው የሜሲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ግን የበርካቶችን ግምት ከግምት እንዳያልፍ አድርጎታል።
የ32 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የኮከብ የእግር ኳስ ሕይወቱን ያሳለፈው ከባርሴሎና ጋር ነው። ነገር ግን በዚህ የውድድር ዘመን መጨረሻ ክለቡን በነጻ ዝውውር መልቀቅ የሚያስችል ስምምነት አለው።
የአሁኑ የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከ2008 እ.አ.አ ጀምሮ እስከ 2012 ድረስ ለአራት ዓመታት ያክል ሜሲን አሰልጥኖታል። በአራት ዓመት ጊዜውም ሦስት የላሊጋና ሁለት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በአንድ ወቅትም "እኔ በጣም እድለኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ቢያንስ የዓለማችንን ምርጡን ተጫዋች ሌዮኔል ሜሲን አሰልጥኜዋለሁ" በማለት ጋርዲዮላ ለሜሲ ያለውን አድናቆት ገልጿል።
ይህ ወደጅነታቸውም አሁን እንደገና ሊያገናኛቸው ይችላል የሚለውን ግምት በበርካቶች ዘንድ አሳድሯል። ነገር ግን ጋርዲዮላ የማይታሰብ ነው ብሏል። "እዚያው [ባርሴሎና] ይቆያል፤ የእኔ ፍላጎት ይህ ነው" በማለት።
ጋርዲዮላ ባርሴሎናን ለቆ ወደ ባየር ሙኒክ ሲያመራ ባርሴሎናን በዋንጫ አንበሽብሾት ነበር። የክለቡም በጣም ስኬታማው አሰልጣኝ የነበረ ሲሆን በአራት ዓመት ቆይታው 14 ዋንጫዎችን ለስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ገቢ አድርጓል።
ከዚያም ወደ ጀርመን አቅንቶ ጋርዲዮላ ከባየር ሙኒክ ጋር ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ማሸነፍ ችሏዋል። ወደ እንግሊዝ በማምራትም ማንችስተር ሲቲን በማሰልጠን ያለፉትን ሁለት ተከታታይ የውድድር ጊዜያት በበላይነት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አሸፏል።
በዚህኛው የውድድር ዘመን ግን ጋርዲዮላ የሚደግመው አይመስልም፤ አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈው ሊቨርፑል 13 ጨዋታዎች ብቻ እየቀሩት ማንችስተር ሲቲን በ22 ነጥብ ርቆ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የባርሴሎናው የምንጊዜም ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ስድስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊ በመሆን የምድራችን ብቸኛ ተጫዋች ሲሆን በባርሳ ቆይታው 10 የላሊጋና አራት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አሸንፏል። እስከ ፈረንጆቹ 2021 በባርሳ የሚያቆየው ኮንትራትም አለው።
ነገር ግን የባርሴሎናው ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ኤሪክ አቢዳል ተጫዋቾች በቀድሞው የክለቡ አሰልጣኝ ኧርኔስቶ ቫልቨርዴ ጊዜ "ጠንክረው አይሰሩም ነበር" የሚል ክስ ማንሳቱን ተከትሎ ሜሲ የአጸፋ መልስ ሰጥቷል።
በእንደዚህ አይነት ጠንካራ ንግግሩ ለዓመታት የማይታወቀው ሜሲ አሁን መልስ መስጠቱ ክለቡ ጋር መለያየትን ስለመረጠ ሊሆን ይችላል በማለት ተንታኞች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አሁን በአቢዳልና በሜሲ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ጋርዲዮላ ማራገብ አልፈለገም። ሁለቱንም በአንድ ወቅት ባርሳ ውስጥ ያሰለጠኑት ጋርዲዮላ "ስለሌላ ክለብ ተጫዋቾች ማውራት አልፈልግም፤ ሜሲ ግን የእግር ኳስ ዘመኑን እዚያው ባርሴሎና ውስጥ የሚያጠናቅቅ ይመስለኛል" ብሏል።












