በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ሮናልዶና ሜሲን ማን ይተካቸው ይሆን?

ሮናልዶና ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሲ ከአውሮፓውያኑ 2010 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት የዓለምን እግር ኳስ ተቆጣጥረውና የኳስ አፍቃሪውን ይሄኛው ይበልጣል ያኛው በሚል ክርክር ውስጥ ከትተው ቆይተዋል።

ነገር ግን ለጁቬንቱስ የሚጫወተው የ34 ዓመቱ ሮናልዶና የባርሴሎናው የ32 ዓመት አጥቂ ሜሲ ለዘለዓለም ሊቆዩ አይችሉም። ለመሆኑ የእነሱን ቦታ ማን ሊተካው ይችል ይሆን?

የቢቢሲ ስፖርት ክፍል ተከታዮቹን ተጫዋቾች ተተኪ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መርጧቸዋል።

ኪሊየን ምባፔ (ፒኤስጂ እና ፈረንሳይ)

ኪሊየን ምባፔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውልደት ቀን: ታህሳስ 20/1998 (በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

የሚጫወትበት ቦታ: አጥቂ

ምባፔ ገና በ21 ዓመቱ ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር 2018 የዓለም ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ማንሳት ብቻ ሳይሆን ለቡድኑ ዋንጫ ማንሳት የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል ማለት ይቻላል።

እጅግ አስገራሚ ፍጥነትና ተፈጥሮአዊ ግብ የማስቆጠር ችሎታው በዓለማችን እጅግ ተፈላጊውና ውዱ ተጫዋች አድርጎታል።

በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም የዓለማችንን እግር ኳስ አፍቃሪ ቀልብ ይዞ እንደሚቆይ ጥርጥር የለውም። የሮናልዶና ሜሲ ተተኪ ለመሆን የሚገዳደረው ያለ አይመስልም።

በአሁኑ ሰአት ለፈረንሳዩ ፒኤስጂ የሚጫወተው ምፓቤ በሚቀጥለው የክረምት የዝውውር መስኮት በዓለማችን ከፍተኛው በሆነ ዋጋ የስፔኑ ታላቅ ክለብ ሪያል ማድሪድን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።

ምናልባት ሜሲ እና ሮናልዶ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ የዓለም ምርጥነት ቦታውን ሊፎካከሩት ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት አብዛኛውን የዓለም ምርጥነት ሽልማቶች መሰብሰቡ የጊዜ ጉዳይ ይመስላል።

ጃዎ ፌሊክስ (አትሌቲኮ ማድሪድና ፈረንሳይ)

ጃዎ ፌሊክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውልደት ቀን : ሕዳር 10/1999(በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

የሚጫወትበት ቦታ: አጥቂ

የ20 ዓመቱ ፌሊክስን ባለፈው የዝውውር መስኮት ነበር አትሌቲኮ ማድሪድ 113 ሚሊየን ዩሮ በሆነ ዋጋ ከቤኔፊካ የገዛው። በወቅቱ ሶስተኛ ከፍተኛው የዝውውር ወጪ ነበር።

በፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ውስጥም ቢሆን የክርስቲያኖ ሮናልዶ ተፈጥሯዊ ተተኪ እንደሚሆን በማሰብ ከአሁኑ ብዙ ሀላፊነቶች እየተሰጡት ይገኛሉ። ባለፈው ዓመትም የዓለማችን ምርጡ ታዳጊ ተጫዋች ተብሎ ዱባይ ላይ ተሸልሟል።

ጆርዳን ሳንቾ (ቦርሺያ ዶርትመንድ እና እንግሊዝ)

ጆርዳን ሳንቾ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውልደት ቀን : መጋቢት 25/2000(በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

የሚጫወትበት ቦታ: የክንፍ መስመር አጥቂ

ይህ ተጫዋች በዶርትመንድ እጅግ አስገራሚ ብቃቱን በማሳየት ላይ ይገኛል። ለግብ የሚሆኑ በርካታ ኳሶችን ከሳምንት ሳምንት ለቡድን አጋሮቹ ከማቀበል ባለፈ ምርጥ ምርጥ ግቦችንም በስሙ ያስመዘግባል።

በራስ መተማመኑም ቢሆን በሜዳ ውስጥ በደንብ ይታያል።

አንሱ ፋቲ (ባርሴሎና እና ስፔን)

አንሱ ፋቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውልደት ቀን : 31 ጥቅምት 2002(በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

የሚጫወትበት ቦታ : የክንፍ መስመር አጥቂ

እጀግ አስገራሚ ፍጥነትና ኳስ የመግፋት ችሎታ የታደለው አንሱ ፋቲ አስቸጋሪ ኳሶችን እንኳን ወደ ግብነት የመቀየር አቅሙ ከፍተኛ ነው። ነገሮችን ይበልጥ ተስፋ ሰጪ የሚያደርጋቸው ደግሞ ታዳጊው ለባርሴሎና መጫወቱ ነው።

ከአጠገቡ ሊዮኔል ሜሲና ሌሎች ከዋክብት መኖራቸው ያለውን አቅም ይበልጥ አሟጥጦ እንዲጠቀም ሊረዳው ይችላል ተብሎ ይታሰባል።

የ17 ዓመቱ አንሱ ፋቲ በባርሴሎና ታሪክ በእድሜ ትንሹ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን በሻምፒዮንስ ሊግም ግብ በማስቆጠርና ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ በማቀበል የባርሴሎናን ታሪክ መቀየር ችሏል።

ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ (ሊቨርፑልና እንግሊዝ)

ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውልደት ቀን: ጥቅምት7/1998(በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

የሚጫወትበት ቦታ: ቀን ተመላላሽ

21 ዓመቱ የሊቨርፑል ተጫዋች ባለፈው ዓመት ከቡድኑ ጋር ቻምፒየንስ ሊግን ማሸነፍ ችሏል። ከባርሴሎና ጋር በነበራቸው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የነበረውን አስተዋጽኦ ማንም አይረሳውም።

በመካከሉ ድንቅ ከመሆን ባለፈ ወደ ግብ የሚልካቸው ኳሶች የቡድን አጋሮቹን በትክክል ነው የሚደርሱት።

በዚህ አጨዋወቱ የሚቀጥል ከሆነ ይህ ተጫዋች ምንም እንኳን ዋና ሃላፊነቱ መከላከል ላይ ያተኮረ ቢሆንም ወደፊት በመሄድ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎቹ ተስፈኛ መሆኑን ያመላክታሉ።

ካይ ሃቨርትዝ (ባየር ሊቨርኩሰን እና ጀርመን)

ካይ ሃቨርትዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውልደት ቀን: ሰኔ 11/ 1999(በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

የሚጫወትበት ቦታ: አማካይ

ጀርመኖች በእግር ኳሳቸው አስደሳች ተጫዋቾችን ማየት ባቆሙበት ወቅት ይህ ወጣት ብቅ ማለቱ ተስፋን እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል። ከፍተኛ የሆነ የኳስ እውቀት አለው የሚባለው ሃቨርትዝ ገና በ 20 ዓመቱ በጀርመን ቡንደስሊጋ ከ100 በላይ ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል።

ፊል ፎደን (ማንቸስተር ሲቲ እና እንግሊዝ)

ፊል ፎደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውልደት ቀን : ግንቦት 28/2000(በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር)

የሚጫወትበት ቦታ: አማካይ

በእንግሊዝ ፕሪምር ሊግ የአሰለጣጠን ስልቱና ተጫዋቾችን የማብቃት ክህሎቱ ከፍተኛነት በሚነገርለት የማንቸስተር ሲቲው ፔፕ ጋርዲዮላ ስር መሆኑ ለዚህ ታዳጊ ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ ብዙዎች እየተናገሩ ነው።

በተጨማሪነት ደግሞ እንደ ኬቨን ደብራይነ፣ ዳቪድ ሲልቫና በርናርዶ ሲልቫን የመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾችን እያየ መጫወቱ ለወደፊቱ ብዙ ነገሮችን ማድረግ እንደሚችል አመላካች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የሪያል ማድሪዱ ሮድሪጎና የማንቸስተር ዩናይትዱ ሜሰን ግሪንዎድም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የዓለምን እግር ኳስ ተቆጣጠር እንደሚቆዩ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።