የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችን በጠቅላላ አባረረ

ጋና የብሔራዊ ቡድኗን አሠልጣኞች በጠቅላላ አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖች አልጣኞች ከሥራ አባሯል።

ሐሙስ ምሽት ውሳኔውን ይፋ ያደረገው ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ኩዊሲ አፒያህን ጨምሮ የሥራ አጋሮቹ መበተናቸውን አሳውቋል።

ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን ለምን እንዳሳለፈ ሲያስረዳ የጋናን እግር ኳስ ለማነቃቃትና ወደ ቅድሞ ክበሩ ለመመለስ ነው ሲል አትቷል።

አፒያህና አጋሮቹ ብቻ ሳይሆኑ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች እንዲሁም ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች አሠልጣኞችም እንዲበተኑ ተደርጓል።

በሙስና ምክንያት ባለፈው ጥቅምት ተበትኖ እንደአዲስ የተቋቋመው የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአዲሱ አመራር ሥር በርካታ ለውጦችን እያከናወነ ይገኛል።

ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ፤ «የብሔራዊ ቡድኖቻችን አሠልጣኞች እስከዛሬ ላደረጉልን ሁሉ እናመሰግናለን። በሄዱበት ሁሉ እንዲቀናቸውም እንመኛለን» ሲል የስንብት ቃሉን አሰምቷል።

በውጤት ቀውስ የነበሩት የጥቁር ኮከቦቹ አሠልጣኝ አፒያህ ከብሔራዊ ቡድኑ ሊባረሩ እንደሚችሉ ግምቶች ቢኖሩም በእንደዚህ መልኩ ይሆናል ብሎ የጠበቀ አልበረም።

የሴቶችም ሆነ የወንዶች ከ17 ዓመታች፣ ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም ከ23 ዓመት በታች አሠልጣኞችና የቴክኒክ ባለሙያዎች ጠቅላላ ተበትነዋል።

የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደ አዲስ ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።

የቀድሞው የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ፌዴሬሽኑ ቀልጦ እንደ አዲስ መሠራቱ አይዘነጋም።