የጣልያኑ ሴሪ ኤ ለጸረ ዘረኝነት ዘመቻው የዝንጀሮ ምስል መጠቀሙ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Serie A
የጣልያኑ ሴሪ ኤ ክለቦች ዘረኝነትን እንዋጋለን ብለው ከተነሱ ከሶስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሴሪ ኤ ለዘመቻው የዝንጀሮ ምስል መጠቀሙ ብዙዎችን ያስቆጣ ሆኗል።
'ለዘረኝነት እምቢ እንበል' የሚለው ዘመቻ ሶስት የዝንጀሮ ምስሎችን የተጠቀመ ሲሆን የሴሪ ኤ ዋና መቀመጫ በሆነችው ሚላን ከተማ ለእይታ ይቀርባል ተብሏል።
በጸረ ዘረኝነት ላይ የሚሰራ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ሲናገር '' አሁንም የጣልያን እግር ኳስ ዓለምን አስደምሟል። ሴሪ ኤ ምን እያሰበ እንደሆነ መገመት ከባድ ነው፤ ማንን አማክረው ነው ይህንን የፈጸሙት? ብሏል።
''በየሳምንቱ የተለያዩ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የዘረኝነት ሰለባ በሚሆኑባት ሀገር ማህበሩ እንዲህ አይነት ተግባር መፈጸሙ እጅግ አሳዛኝና የሚያስቆጣ ቀልድ ነው።''
''የሴሪ ኤ ተግባር ከቃላት በላይ ነው፤ ዘረኝነትን የሚያበረታታና ለማንም የማይጠቅም እርምጃ ነው። ዘራቸው ከአፍሪካ የሚመዘዝ ተጫዋቾችን እንደ ሰው የማይቆጥር ዘመቻ ነው።''
ባለፈው መስከረም ወር ላይ የኢንተር ሚላኑ የፊት መስመር ተጫዋች ሩሜሉ ሉካኩ በሜዳ ውስጥ እያለ የካግሊያሪ ደጋፊዎች የጦጣ ድምጽ በማውጣት የዘረኝነት ጥቃት የፈጸሙበት ሲሆን እሱም ''እግር ኳስና ደጋፊዎቻችን ወደኋላ እየሄድን ነው'' ብሏል።
በቅርቡ ደግሞ 'ኮሪዬሬ ዴሎ ስፖርት' የተባለው የጣልያን ጋዜጣ ሮማ እና ኢንተር ሚላን የሚያደርጉትን ጨዋታ 'ጥቁር አርብ' በማለት የሮማው ተከላካይ ክሪስ ስሞሊንግ እና የኢንተር ሚላኑ አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩን ምስል የፊት ገጽ ላይ ይዞ መውጣቱ የሚታወስ ነው።
የአውሮፓ እግር ኳስ ባለሙያ የሆነው ጄምስ ሆርንካስል የጣልያን እግር ኳስ እጅግ አሳፋሪ እየሆነ መጥቷል ብሏል።
'' ሴሪ ኤ ስለዘረኝነት ያለው አመለካከት በጣሙን የተሳሳተ ይመስለኛል፤ ለዚህም ነው ክለቦች በራሳቸው የጸረ ዘረኝነት ዘመቻዎችን ለማካሄድ እየወሰኑ ያሉት።''
ለሴሪ ኤ ዘመቻ የዝንጀሮዎቹን ምስል የሰራው ሰአሊው ሲሞን ፉጋዞቶ በበኩሉ '' ሁሌም ቢሆን በስራዎቼ ዝንጀሮዎችን እጠቀማለሁ፤ ሰዎች ስለዘረኝነት ያላቸውን አስተሳሰብ ለመቀየር እጠቀምበታለው'' ብሏል።
የሴሪ ኤ ዋና ሀላፊ ሉዊጂ ዴ ሴርቮ ደግሞ ''ማንኛውም አይነት የተሳሳተና ሰዎች በተለየ መልኩ እንዲታዩ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችን እንቃወማለን፤ ዘረንነት በሊጉ እጅግ እንደተንሰራፋማ እናውቃለን'' ብለዋል።












