ሊዮኔል ሜሲ ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ታገደ

ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታዋቂው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አምበል ሊዮኔል ሜሲ ለሦስት ወራት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ ተጣለበት። ሜሲ ላይ እገዳው የተጣለው የአህጉረ አሜሪካ ሃገራት የሚሳተፉበት የኮፓ አሜሪካ እግር ኳስ ውድድር "በሙስና የተበላሸ ነው" በማለት አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ ነው።

የባርሴሎናው የፊት መስመር ተጫዋች ሜሲ ሲካሄድ በሰነበተው የኮፓ አሜሪካ ውድድር ላይ አርጀንቲና ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ ቺሊን 2 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላ የሰጠው አስተያየት ለቅጣት ዳርጎታል።

የ32 ዓመቱ ሜሲ ውድድሩ ብራዚል አሸናፊ እንድትሆን ታቅዶ የተካሄደ ነው ማለቱ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን አስቆጥቶ ከጨዋታ እንዲታገድና የ50 ሺህ ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል።

ሜሲ ለሦስት ወራት ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች የተጣለበት እገዳና የገንዘብ ቅጣቱን በተመለከተ ይግባኝ የመጠየቂያ ሰባት ቀናት አሉት።

የጨዋታ እገዳው የሚጸና ከሆነ ሜሲ ሃገሩ አርጀንቲና በመጪዎቹ መስከረምና ጥቅምት ከቺሊ፣ ከሜክሲኮና ከጀርመን ጋር በምታደርጋቸው የወዳጅነት ግጥሚያዎች ላይ አይሳተፍም።

አርጀንቲና በኮፓ አሜሪካ ውድድር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በብራዚል 2 ለ 0 ስትሸነፍ የሃገሪቱ እግር ኳስ ማህበር በጨዋታው ላይ "በርካታና ወሳኝ የዳኝነት ስህተቶች ነበሩ" ሲል ቅሬታውን አቅርቦ ነበረ፤ የውድድሩ አዘጋጆች ግን ክሱን ውድቅ አድርገውታል።

በግጥሚያው 37ኛ ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ የተባረረው ሜሲ እንዳለው "የዚህ በሙስና የተበላሸ አሰራር ውስጥ መሳተፍ የለብንም" በማለት በውድድሩ ወቅት አክብሮት የጎደለው ሁኔታ እንደገጠማቸው ተናግሯል።

"የሚያሳዝነው ደግሞ ሙስናውና ዳኞቹ ተመልካች በጨዋታው እንዳይደሰት በማድረግ እግር ኳሱን አበላሽተውታል" ሲል ሜሲ ወቅሷል።