በጀርመን አንድ ቢሊየን ዩሮ የሚያወጣ ኮኬይን ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጀርመን በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ መጠን ያለው የኮኬይን እፅ በሀምቡርግ ወደብ ላይ መያዙን የአገሪቷ የጉምሩክ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
የሶያ ጥራጥሬ በሚል ስም ሲጓጓዝ የነበረው ኮኬይን የተያዘው ከሁለት ሳምንት በፊት የሀምቡርግ የጉምሩክ መስሪያ ቤት በጥርጣሬ ፍተሻ በማካሄዱ ነበር። ከአራት ቶን በላይ የሚለካው ይህ የኮኬይን እፅ ከኡሯጓይ ወደ ቤልጂየም እየተጓጓዘ ነበርም ተብሏል።
ኮኬይኑ 200 በሚሆኑ የስፖርት ሻንጣዎች ተደብቆ በእቃ ማጓጓዣ ኮንቴይነር ውስጥ ሆኖ ነበር የተያዘው።
የጉምሩክ መስሪያ ቤቱ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እፁን ከጥቅም ውጭ አድርጎ ማስወገዱን ገልጿል።
"እፁ ለመንገድ ላይ ንግድ እንዲሆን ሳይዘጋጅ እንዳልቀረ ተገምቷል፤ ይህ 4.5 ቶን የሚለካው ኮኬይንም በገንዘብ ሲተመን አንድ ቢሊየን ገደማ ዩሮ (1.1 ቢሊየን ዶላር) ያወጣል" ሲል የሀምቡርግ የጉምሩክ መስሪያቤት በመግለጫው አስታውቋል።
የሀምበርገር ፖሊስ የኮንቴኔሮችን መዳረሻ የት ሊሆን እንደሚችል ምርመራ እያካሄደ መሆኑን መግለጫው አክሏል።
የጀርመን ባለሥልጣናት እፁን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ዓለም አቀፋዊ የሆነ ሕገ ወጥ የእፅ ዝውውርን ለመቆጣጠር ያላቸውን ብቃት ያሳየ እንደሆነ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የእፁ ከፍተኛ መጠን መሆን በደቡብ አሜሪካ ያለው የእፅ ምርት እየጨመረ ለመምጣቱ አመላካች ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሀምቡርግ በአውሮፓ ካሉ ትላልቅ ወደቦች ሦስተኛው ሲሆን በጀርመን ግን ትልቁ ወደብ ነው።













