አልጄሪያ አንድ ኮንቴይነር ሙሉ ኮኬይን ያዘች

የአልጄሪያ የባሕር ኃይል አባላት መርከቧን ኦራን በተሰኘችው ወደብ ታግታ እንድትቆይ አድርገዋል

የፎቶው ባለመብት, ALGERIAN DEFENCE MINISTRY

የምስሉ መግለጫ, የአልጄሪያ የባሕር ኃይል አባላት መርከቧን ኦራን በተሰኘችው ወደብ ታግታ እንድትቆይ አድርገዋል

የአልጄሪያ ባለሥልጣናት 700 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን በኮንቴይነር ተጭኖ በመርከብ ሊያልፍ ሲል ደርሰውበት በቁጥጥር ሥር አውለውታል። ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ አስተላላፊ ናቸው የተባሉ 20 ሰዎች ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

መርከቡ "ሀላል ሥጋ" የሚል ምልክት የተደረገባቸው ኮንቴይነሮችን ከብራዚል ወደ ስፔን ቫሌንሺያ በማጓጓዝ ላይ ነበር ተብሏል።

ኦራን የተሰኘችው የአልጄሪያ ምዕራባዊ ወደብ ሲደርስ ግን የተወሰኑ ኮንቴይነሮችን ማራገፍ ነበረበት። ካፒቴኑ ግን ለ3 ቀናት ይህን ለማድረግ አለመፍቀዱ ጥርጣሬን ጫረ።

ይህን ተከትሎ ለአልጄሪያ ፖሊስ ጥቆማ በመድረሱ መርከቡን በአስገዳጅ ወደ ወደቡ በመውሰድ ዘለግ ያለ ፍተሻ ተደርጎበታል።

በፍተሻውም በላይቤሪያ ስም የተመዘገበችው ቬጋ ሜርኩሪ በምትባል መርከብ ውስጥ "ሃላል ሥጋ" የሚል ምልክት ተለጥፎበት ተገኝቷል።