በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለ ዓይን ለምን ከኢሉሚናቲዎች ጋር ይያያዛል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለ ዓይን የኢሉሚናቲ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ኢሉሚናቲዎች በምሥጢር ዓለምን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው የሚለው የሴራ ትንታኔ ዘመናት አስቆጥሯል።
በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለው ዓይን (Eye of Providence) በብዙ ቤተ ክርስቲያናት እና የፍሪሜሰን ተከታዮች ሕንጻ ላይ ይገኛል።
የአሜሪካ አንድ ዶላር ላይም ምሥሉ ይታያል።
በሦስት ማዕዘን ውስጥ ካለው ዓይን ሥር ፒራሚድ ስለሚታይ የምልክቱ መነሻን ጥንታዊ ሥልጣኔ አድርገው የሚተነትኑም አሉ።
ፍሪሜሰኖች እና ኢሉሚናቲዎችን በሦስት ማዕዘን ውስጥ ካለው ዓይን ጋር ማስተሳሰር የተለመደ ነው።
በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለው ዓይን መነሻው ክርስትና ነው። በተሃድሶ (ሬነሰንስ) የሥነ ጥበብ ዘመን ሥዕሎች ላይ ምሥሉ በብዛት ይታያል። በዚህም ፈጣሪን ይወክላል።
በአውሮፓውያኑ 1525 የተሳለው 'ሰፐር አት ኤሙስ' ይህ ምልክት ይታይበታል።
እአአ በ1593 የታተመው 'ኢኮኖሎጊያ' የዚህ ምልክት ዋነኛ መነሻ ነው። የፈጣሪን ቸርነት የሚወክል ምልክት ተደርጎ ነው የሚወሰደው።
በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለው ዓይን ለመጀመሪያ ጊዜ መቼ ጥቅም ላይ እንደዋለ ባይታወቅም መነሻው ቀደምት ሃይማኖቶች ናቸው።
በክርስትና የአብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው ሦስት ማዕዘን ነው።
እግዚአብሔርን በሦስት ማዕዘን የብርሃን አክሊል ማሳየትም የተለመደ ነበር። የፈጣሪን ብርሃንነት ለማሳየትም የብርሃን ፍንጣቂዎች በሥዕል ይቀመጣሉ።
እግዚአብሔር ከደመና በሚወጣ እጅ የሚወከልም ሲሆን፣ በዓይን ሲወከል ግን አልተስተዋለም።
ስለዚህም የዓይን ምሥል በሦስት ማዕዘኑ የታከለው ምልከታን ለማሳየት እንጂ በሃይማኖታዊ መሠረት ነው ለማለት ያስቸግራል።
በዝግመተ ለውጥ አንዳንድ እንሰሳት ራሳቸውን ከጠላት ለመከላከል ሰውነታቸው ላይ ዓይን የሚመስል ምልክት ይታይባቸዋል።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው ዓመተ ዓለም ሱሜርያኖች ቅድስናን ለማሳየት የዓይን መጠንን ከፍ አድርገው ያሳያሉ።
ቀራጺያን ዓይን በመግለጥ በአደባባይ የሚያሳዩነት ትዕይንት ይካሄድም ነበር።
ግብፃውን ዓይንን እንደ ምልክት በመጠቀም በጉልህ ይጠቀሳሉ። በመቃብር ላይ ዓይን ሲሳል ሟቾች ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ማየት እንዲችሉ በማሰብ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሆራስ ዓይን (Eye of Horus) ታዋቂ የግብፅ ምልክት ነው።
የሰው እና የንሥር ዓይንን በማዳቀል በጥንታዊ ግብፅ የሚታዩ ምልክቶች ከአፈ ታሪክ እና ከንግርት ጋር ይተሳሰራሉ።
ሆሩስ የተባለው አምላክ በአሞራ የሚወከል ሲሆን፣ ከአጎቱ ሴት ልጅ ጋር ሲዋጋ ዓይኑን እንዳጣ ይነገራል።
ኋላ ላይ ቶታህ ረድቶት ዓይኑ መልሶ ማየት ይጀምራል። በቅርጾች ላይ ዓይኑ እንደ ምልክትም ይወሰዳል።
በሬነሰንስ የሥነ ጥበብ ዘመን የግብፅ ሥነ ጥበብ ዘዬ ወደ አውሮፓም ተስፋፍቷል። የግብፅ ጽሑፎች ብዙዎችን ቢማርኩም ትክክለኛ ትርጉማቸውን መረዳት ግን ቀላል አልነበረም።
ከ1400 እስከ 1500 በነበሩት ዘመናት ጽሑፎቹ የነበራቸው ሚና የላቀ ነበር። ረቂቅ ትርጉም እንዳላቸውም ይታመናል።
ታዋቂ ከሆኑ ምልክቶች መካከል እንሰሳት፣ አእዋፋት እና ረቂቅ ምልክቶችን መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህ ምልክቶች ራሳቸውን የቻሉና ትርጉም ያላቸው ተደርገው ነው የሚቀመጡት።
ይህ በሦስት ማዕዘን ውስጥ መሃል ላይ የተቀመጠው ዓይን የኢሉሚናቲዎች ምልክት ተደርጎም በተለያዩ ሁኔታዎች ሲቀርብ ይታወቃል።
"ኢሉሚናቲዎች በምሥጢር ዓለምን ተቆጣጥረው አዲስ ሥርዓት ሊዘረጉ ነው" የሚለው መላ ምት ለዘመናት ሲሰማ ቆይቷል።
የዚህ ሃሳብ መነሻ በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ የነበረ ልብ ወለዳዊ ክስተት ነው።
ጀርመን የነበረው 'ኢንላይትመንት ኢራ' ወይም የዕውቀት አብርሆት ዘመን ከኢሉሚናቲ መነሻ ጋር ይተሳሰራል።
ባቫሪያን የሚባል ምሥጢራዊ ስብስብ ነበር። ይህም በአውሮፓውያኑ 1776 ነበር የተጀመረው።
የተማሩ ሰዎች ተሰባስበው ሃይማኖታዊ ሥርዓት እና መዋቅርን ይነቅፉ ነበር።
ፍሪሜሰን እንደተባለው ሌላ ምሥጢራዊ ቡድን ሁሉ ኢሉሚናቲም ተራማጅ ተደርገው ይወሰዳሉ።
ወግ አጥባቂ እና ክርስቲያን ተቺዎች ግን አልተቀበሏቸውም። ለተወሰነ ጊዜ ጠፍተው በ1960ዎቹ ዳግመኛ አንሰራርተዋል።
እነዚህን ሁለት ቡድኖችን በሦስት ማዕዘን ውስጥ ካለው ዓይን ጋር ማስተሳሰርም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው።
አንዳንዴ ስለ ምልክቱ የሚሰጡ ትርጓሜዎች የተለያዩ ናቸው።
ከፈረንሳይ አብዮት በኋላ በተጻፉ መጻሕፍት ይህ ምሥል ሲካተት አዲስ የተገነባችውን አገር እንደሚጠብቅ ኃይል ነበር የሚወሰደው።
እአአ በ1974 በእንግሊዝ የኪነ ሕንጻ ባለሙያ ዊሊ ሬቪሊ የሠራው ምልክት እንደ አብዮት ዘብ ተወስዷል።
እንደ ፍትሕ ምልክትም ይወሰድ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ 1782 ወዲህም ቶማስ ጄፈርሰን፣ ቤንጃሚን ፍራንክሊን እና ጆን አዳምስ የየራሳቸውን ምልክት ለማካተት ሐሳብ ሰንዝረዋል።
ቻርልስ ቶምሰን በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለ ዓይን እና ፒራሚድ እንደ ምልክት እንዲወሰዱ በማድረግ ስማቸው ይነሳል።
ዊልያም ባርቶን ከተባለ ጠበቃ እና አርቲስት ጋር ነበር ይህንን እውን ያደረጉት።
አሁን ያለው ኢሉሚናቲ ከባቫሪያን ምሥጢራዊ ቡድን እንደሚለይ በኢሉሚናቲ ላይ ጥናት የሠራው ዴቪድ ብራምዌል ይናገራል።
ከፍሪሜሰንስ ጋር የሚያያዙ ምልክቶችን ኢሉሚናቲዎችም እንደሚጠቀሙ ቢታወቅም በግልጽ ምልክቶቹ ያላቸውን ዋጋ መግለጽ ግን ቀለላ አይደለም።
ጆን ኤፍ ኬኔዲን ማን ገደላቸው? የሚለውን ጨምሮ በይፋ ከማይታወቁ ነገሮች ጀርባ ያሉት ኢሉሚናቲዎች ናቸው የሚለው የሴራ ትንታኔ አሁንም ድረስ ገናና ነው።
ጄ ዚ እና ቢዮንሴን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ኢሉሚናቲ ናቸው ተብሎ ይታመናል።
የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ ሦስት ማዕዘን ያለው ቅርጽ በመሥራት መድረክ ላይ ሲያሳዩ ይስተዋላል።
ነገሩ እውነት እንዳልሆነ ቢታወቅም አሁንም ድረስ ከ1960ዎቹ የተነሳው የሴራ ትንታኔ በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ ዘልቋል።
ፍሪሜሰንስ በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለ ዓይን በይፋ መጠቀም የጀመሩት በ18ኛው ክፍለ ዘመን ነው።
በአሜሪካ አንድ ዶላር ላይ ያለው በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለ ዓይን ስለ ኢሉሚናቲዎች የሚነግረን ሳይሆን በ18ኛው ክፍለ ዘመን ስላለው ሥነ ጥበብ ምርጫ የሚገልጽ ነው።
ማዶና፣ ካንዬ ዌስት እና ሌሎችም ታዋቂ አርቲስቶች የሚያሳዩት ምልክት ስለ ኢሉሚናቲ የሚነግረን ነገር ባይኖርም አርቲስቶቹ ያላቸውን የጥበብ ከፍታ ለመግለጽ ዓይንን ከገናናነት ምልክት (iconic) ጋር ማስተሳሰራቸውን መመልከት ይቻላል።
የኢሉሚናቲዎች መነሻ ሐሳቡ ከ200 ዓመት በላይ አስቆጥሯል።
ከፈረንሳይ አብዮት፣ በአሜሪካ ላይ ከተፈጸመው የመስከረም 11 ጥቃት እንዲሁም ከሌሎች ጉልህ የዓለማችን ክስተቶች ጀርባ ኢሉሚናቲዎች እንዳሉ የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም።
በሦስት ማዕዘን ውስጥ ያለ ዓይንን ጨምሮ ሌሎችም ምልክቶች፣ ጽሑፎች እና ክስተቶች ከኢሉሚናቲዎች ጋር ማስተሳሰርም ቀጥሏል።















