በሱዳን ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ቅጥረኛ ተዋጊዎች እንዳሉ ተነገረ

በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የመጡ ቅጥረኛ ተዋጊዎች እንደሚሳተፉ የሱዳን ባለሥልጣናት ተናገሩ። የሱዳን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም የሱዳን ጦር ኃይልን በመቀናቀን ከሚዋጋው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ተሰልፈው ሲዋጉ ነበር ባላቸው ከ120 በላይ የውጭ አገር ቅጥረኛ ወታደሮች ላይ ክስ መሥርቷል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በሱዳን ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ቅጥረኛ ተዋጊዎች እንዳሉ ተነገረ

    ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የመጡ ቅጥረኛ ተዋጊዎች እንደሚሳተፉ የሱዳን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    በጦነርቱ ተሳታፊ የሆነው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ውጭ አገራት ቅጥረኛ ተዋጊዎችን እንደሚያሰልፍ እና የተያዙም እንዳሉ ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።

    የሱዳን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም የሱዳን ጦር ኃይልን በመቀናቀን ከሚዋጋው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ተሰልፈው ሲዋጉ ነበር ባላቸው ከ120 በላይ የውጭ አገር ቅጥረኛ ወታደሮች ላይ ክስ መሥርቷል።

    በሱዳን ጦር ኃይል የሚመራው የሱዳን መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኢንቲሳር አሕመድ አብደል ሙታአል የወንጀል ክስ የቀረበባቸው የውጭ አገራት ተዋጊዎች የተለያየ ዜግነት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

    ዐቃቤ ሕጓ እንዳሉት ቅጥረኛ ተዋጊዎቹ ሦስት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ ከሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ጎን በመሰለፍ በመዋጋታቸው ነው ክሱ የቀረበባቸው።

    የሱዳን ባለሥልጣናት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሱዳን ጦር ሠራዊት ጋር በሚያካሂደው ጦርነት ውስጥ አባላቱን ለማጠናከር የሚዋጉለትን ቅጥረኛ ወታደሮች ከተለያዩ አገራት እየመለመለ ያሰልፋል ሲሉ ይከሳሉ።

    ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከቻድ እና ከደቡብ አሜሪካ ደግሞ ከኮሎምቢያ ቅጥረኛ ወታደሮችን እንደሚመለምል ባለሥልጣነቱ አመልክተዋል።

    የሱዳን መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ጨምረው የተወሰኑ የውጭ ቅጥረኛ ወታደሮች ክስ ተመሥርቶባቸው ጥፋተኛ ሆነው ሞት የተፈረደባቸው እንዳሉ ገልጸዋል።

    ነገር ግን በቅጥረኛ ተዋጊዎቹ ላይ የተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ተግባራዊ ስለመሆኑ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

    በሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ በጄነራል አል ቡርሐን እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይሉ መሪ በጄነራል ጋዳሎ መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ፉክክር በተቀሰቀሰው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ ሚሊዮኖች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

  2. የትራምፕ አስተዳደር ለኢትዮጵዊያን የተሰጠው የሕግ ከለላ እንዲነሳ በማድረጉ ክስ ቀረበበት

    የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም

    የስደተኞች መብት ተሟጋቾች የትራምፕ አስተዳደር ለኢትዮጵዊያን ስደተኞች የተሰጠው የሕግ ከለላ እንዲነሳ ማድረጉ ትክክል አይደለም የሚል ክስ መመሥረታቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    በአሜሪካ በጊዜያዊ የሕግ ከለላ ሥር የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያን ስደተኞች በትራምፕ ውሳኔ መሠረት ከዩናይትድ ስቴትስ ሊባረሩ ይችላሉ።

    ሦስት ኢትዮጵያዊያን እና አፍሪካን ኮሚዩኒቲስ ቱጌዘር የተሰኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በቦስተን ፌዴራል ፍርድ ቤት በከፈቱት ክስ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ 5 ሺህ ግለሰቦችን አደጋ ላይ ጥሏል ብለዋል።

    በእንግሊዝኛው ቲፒኤስ እየተባለ የሚጠራው ጊዜያዊ የሕግ ከለላ በሀገራቸው ተፈጥሯዊ አደጋ፥ የትጥቅ ግጭት እንዲሁም ሌሎች አደጋዎች ለተጋረጡባቸው ሰዎች ከለላ ይሰጣል።

    ቲፒኤስ የተሰጣቸው ሰዎች በአሜሪካ የመኖር እና የመሥራት እንዲሁም ከመባረር የመጠበቅ ከለላ አላቸው።

    ክሱ እንደሚለው ‘ኢትዮጵያ አሁንም ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ እያለች የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሯ ክሪስቲ ኖም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የኢትዮጵያዊያን የሕግ ከለላ በ60 ቀናት እንዲቋረጥ አድርገዋል። ይህም ሕገ-መንግሥቱን ያልተከተለ እና ነጭ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ነው” ይላል።

    ከሶሪያ፣ ከቬኔዙዌላ፣ ከሃይቲ፣ ከኒካርጉዋ እና ከደቡብ ሱዳን ለመጡ ዜጎች የተሰጠው የሕግ ከለላ መነሳቱን ተከትሎ በርካታ ክሶች ተመሥርተዋል።

    በቅርቡ የትራምፕ አስተዳደር ለሶማሊያዊያን ተሰጥቶ የነበረው የሕግ ከለላ እንዲነሳ መወሰኑ አይዘነጋም።

    በአውሮፓውያን 2022 በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሕግ ከለላ የሰጠው የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር እንደነበር ይታወሳል።

  3. “ጦርነት በየትኛውም ሰዓት ሊፈንዳ ይችለል” የኢራን ባለሥልጣን

    የኢራን ፀጥታ ኃይል አባል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚሽን አባል የሆኑት ሳላር ቬላያትማዳር በኢራን እና በባላንጣዎቿ መካከል “ጦርነት በየትኛውም ሰዓት ሊፈንዳ ይችለል” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    የምክር ቤት እና የደኅንነት ኮሚሽን አባሉ እንዳሉት የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጦርነት እንደሚመጣ “ለዓመታት ስትጠብቅ ነበረ” በማለት ባለፈው ዓመት ሰኔ ከእስራኤል ጋር ለ12 ቀናት የተካሄደውን ጦርነት አስታውሰዋል።

    ከዚያም በኋላ ኢራን በዚህ ጦርነት ውስጥ ናት በማለት “የጦርነቱ እሳት ያልጠፋ ሲሆን፣ የሚዲያ፣ የፖለቲካ እና የመግለጫው ጦርነት” ቀጥሏል ብለዋል።

    ከቀናት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግዙፍ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ኢራን ወደ ምገትኝበት ቀጣና ማሰማራታቸውን ተናግረዋል።

    ባለሥልጣኑ ጨምረውም በቅርቡ በመላው አገሪቱ በተካሄደው ተቃውሞ “የታሰሩት እና የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው ተቃውሞ ጋር ሲነጻር ከሦስት በመቶ ያነሰ ነው” ሲሉ ጉዳቱን ዝቅ አድርገውታል።

    ይህ ንግግራቸው የተሰማው በተቃውሞው ወቅት የተገደሉ ሰዎች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ነው የሚሉ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

    የፓርላማው የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚቴ አባሉ ጨምረውም ተቃዋሚዎቹ ከእስራኤል የደኅንነት ተቋማት ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው በማለት ከስሰዋል።

    ተቃዋሚዎቹ "ለጥቂት ቀናት አስቸጋሪ ሁኔታን ከመፍጠር በዘለለ ያደረጉት ነገር የለም፤ የተቀደሰውን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጫፍ አልነኩም” በማለት ተቃውሞውን አጣጥለውታል።

    በምጣኔ ሀብት ቀውስ እና በአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ምክንያት ከሦስት ሳምንት በላይ በበርካታ ኢራን ከተሞች በተካሄደው ሕዝባዊ አመጽ የተረጋገጠ መረጃ ማግኘት ባይቻልም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ይገልጻሉ።

  4. በአሜሪካ በከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት በረራዎች ተሰረዙ፣ ኤሌክትሪክ ተቋረጠ

    በከባድ በረዶ ጭጋግ የተሸፈነ አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አብዛኛው የአሜሪካ ክፍል ከተለመደው በላይ የከፋ ቅዝቃዜን ወደሚያስከትል የክረምት ወቅት መግባቱን ተከትሎ በርካታ የአውሮፕላን በረራዎች ሲሰረዙ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጥ ማጋጠሙ ተዘገበ።

    ከ200 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሚከሰተው በዚህ ቅዝቃዜ ቅዳሜ ብቻ ከ4,000 በላይ በረራዎች ሲሰረዙ፣ ከ160 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተጠቃሚዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተቋርጧል።

    የቅዝቃዜ ወጀቡን “ታሪካዊ” በማለት የጠሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከ12 በላይ በሚሆኑ ግዛቶች ላይ የአደጋ ጊዜ አስቸኳይ ድንጋጌ አስተላልፈዋል።

    ፕሬዝዳንቱ "ይህንን ቅዝቃዜ ከሁሉም ግዛቶች ጋር በመሆን በቅርበት እንከታተላለን” በማለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ለዜጎቻቸው መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

    የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት አስንዳስታወቀው ዋሺንግተን ዲሲ እና ሰባት ግዛቶች በአየር ሁኔታው የተነሳ አስቸኳይ ጊዜን አውጀዋል።

    የበረዶ ወጀብ እና ግግሩ በቀጣይ ቀናት እየበረታ ይሄዳል በተባለው በዚህ ከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚቋረጥባቸው አካባቢዎች እየጨመረ እንደሚሄድ የተነገረ ሲሆን፣ ይህ እንቅስቃሴዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሽመደምድ ሊሆን እንደሚችል የአገሪቱ አየር ሁኔታ አገልግሎት አስጠንቅቋል።

    ቅዳሜ ዕለት ከተሰረዙት በሺዎች ከሚቆጠሩ በረራዎች በተጨማሪ፣ ለዛሬ እሁድ ተይዘው የነበሩ ከ9,400 በላይ በረራዎች እንዲሰረዙ ተደርገዋል።

    አየር መንገዶችም በበረራዎች ላይ ለውጥ ወይም መሰረዝ ሊኖር እንደሚችል ተጓዦችን አሳስበዋል።

    በአሜሪካ ምክር ቤት ግቢ ውስጥ በረዶ የሚያጸዱ ሠራተኞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  5. ቻይና የሀገሪቱ ከፍተኛ ጄነራል ላይ ምርመራ ከፈተች

    ጄነራል ዣንግ ዩዢያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጄነራል ዣንግ ዩዢያ

    ቻይና የሀገሪቱ ከፍተኛው ወታደራዊ ማዕረግ ባለቤት የሆኑት ጄነራል “የዲሲፕሊን እና የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል” በሚል ምርመራ እንደከፈትባቸው አስታወቀች።

    ነገር ግን የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር በተከሰሱት ጄነራል ዣንግ ዩዢያ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

    ግለሰቡ የፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግ የቅርብ ሰው ሲሆኑ፣ ሌላኛው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጄነራል ሊዩ ዤንሊም ምርመራ እንደተከፈተባቸው ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

    ምንም እንኳ ሚኒስቴሩ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም ብዙውን ጊዜ ባለሥልጣናል የዲሲፕሊን ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው የሚከሰሱት በሙስና ሲጠረጠሩ ነው።

    ቻይና ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ ዘጠኝ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ከሥልጣን ያነሳች ሲሆን፣ ይህ ለዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ነው።

    የ75 ዓመቱ ዣንግ የማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ሲሆኑ አለቃቸው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጂንፒንግ ናቸው።

    አልፎም 24 ግለሰቦች የሚመሩት የሀገሪቱ ውሳኔ ሰጪ አካል የሆነው ፖሊትቢሮ አባልም ናቸው።

    የጄነራሉ አባት ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ መሥራቾች መካከል ሲሆኑ፣ ስማቸው በጉልህ ይነሳል።

  6. በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በአሜሪካ መካከል የተደረገው ንግግር ያለውጤት አበቃ

    የሦስቱ አገራት ተደራዳሪዎች ከኤምሬት መሪ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የሦስቱ አገራት ተደራዳሪዎች ከኤምሬት መሪ ጋር

    አቡ ዳቢ ውስጥ የተካሄደው ሩሲያ፣ ዩክሬን እና አሜሪካ የተሳተፉበት የመጀመሪያው የሦስትዮች የሰላም ንግግር ተጨባጭ ውጤት ሳያስገኝ ተጠናቀቀ።

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የውይይቱ ሁለተኛ ዙር በቀጣይ ሳምንት ሊካሄድ እንደሚችል ቢጠቁሙም፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን ከሳምንት በኋላ ይጀምራል ብለዋል።

    አቡ ዳቢ ውስጥ የተካሄደው ንግግር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከጀመረች ከአራት ዓመት በኋላ የተካሄደ የመጀመሪያው የሦስትዮሽ ውይይት ነው።

    ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በኤክስ ገፃቸው እንዳሰፈሩት የንግግሩ "ዋነኛ ትኩረት ጦርነቱን ለማቆም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከር ነበር” ብለዋል።

    አክለውም ሁሉም ወገኖች ወደ አገሮቻቸው ተመልሰው ከመሪዎቻቸው ጋር በመመካከር ለቀጣይ ውሳኔዎች እንዲዘጋጁ ከስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።

    ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ቀጣዩ ዙር ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ አቡ ዳቢ ውስጥ እንደሚካሄድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ለሁለት ቀናት የተካሄደው ንግግር ያበቃው ሩሲያ ክፉኛ የተጎዳውን የዩክሬን የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ አድርጋ ከባድ የአየር ጥቃቶችን ከፈጸመች በኋላ ነው።

    የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት በጥቃቱ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች 35 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በሩሲያ በኩል ደግሞ በምትቆጣጠረው የዩክሬን አካበቢ በአምቡላንስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት የሕክምና ባለሙያዎች ተገድለዋል ስትል የዩክሬን ኃይሎችን ከስሳለች።

  7. ታዋቂ አየር መንገዶች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚያደርጓቸውን በረራዎች ሰረዙ

    የሉፍታንዛ አውሮፕላኖች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, በረራቸውን ከሰረዙ አየር መንገዶች መካከል ሉፍታንዛ አንዱ ነው

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ውጥረት በነገሰበት በአሁኑ ወቅት ታዋቂ አየር መንገዶች ቅዳሜ ዕለት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚያደርጓቸውን በረራዎች ሰረዙ።

    የፈረንሳዩ ኤር ፍራንስ፣ የጀርመኑ ሉፍታንዛ፣ የካናዳው ኤር ካናዳ እና የኔዘርላንድሱ ኬኤልኤም አስከ እሁድ ድረስ ወደ እስራኤል፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንደማይበሩ አሳውቀዋል።

    በረራዎቹ የተሰረዙት አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ውጥረት ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊያመራ ይችላል በሚሉበት ውቅት ነው።

    የእስራኤሉ ቻናል አይ24 የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ “በኤርፖርቶች ድረ ገጽ ላይ የሰፈረን የበራረ መረጃን” መሠረት እድርጎ እንደዘገበው የኔዘርላንድሱ ሮያል ደች አየር መንገድ እና የስዊትዘርላንዱ ስዊስ ኤር በተመሳሳይ በረራቸውን ሰርዘዋል።

    የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር አርብ ማታ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት በረራዎችን በተመለከተ ከአገሪቱ የደኅንነት ዕዝ የተለወጠ ነገር እና የተላለፈ ትዕዘዝ የለም ብሏል።

    የኢራን ሲቪል አቪየሽን ድርጅት ቃል አቀባይ “የኢራን የአየር ክልል አልተዘጋም፤ የበረራ መስመሩም ከበረራ ነጻ እንዲሆን አልተደረገም” በማለት በኢንተርኔት ላይ የሚዘዋወረውን መረጃ ውድቅ አድርገውታል።

    የጀርመኑ አየር መገንድ ሉፍታንዛ አስከ መጋቢት መጀመሪያ ድረስ፣ እንዲሁም የሉፍታንዛ አካል የሆነው የኦስትሪያ አየር መንገድ አስከ የካቲት አጋማሽ ድረስ ወደ ኢራን በረራዎች እንደማይኖሯቸው ከቀናት በፊት አሳውቀዋል።

  8. የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ከግሪንላንድ መሪ ጋር ሊወያዩ ነው

    የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን በኑክ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የግሪንላንድ መሪ ጄንስ-ፍሬድሪክ ኒልሰን ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን በኑክ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የግሪንላንድ መሪ ጄንስ-ፍሬድሪክ ኒልሰን ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

    ወደ ግሪንላንድ መዲና ኑክ ያቀኑት የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን፤ ከግዛቲቱ መሪ ጄንስ-ፍሬድሪክ ኒልሰን ጋር እንደሚወያዩ ተገለጸ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ማቀዳቸው ያስነሳው ውጥረት አልረገበም።

    ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል “ወታደራዊ አማራጭ” እንደማይጠቀሙ ቢናገሩም፤ ዕቅዳቸውን የማይቀበሉ የአውሮፓ አገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸው አይዘነጋም።

    ባለፈው ሳምንት በዳቮስ የምጣኔ ሃብት ጉባዔ ላይ ግን ታሪፍ የመጣል ዕቅዳቸውን እንደሰረዙ ገልጸዋል።

    የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን በኑክ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የግሪንላንድ መሪ ጄንስ-ፍሬድሪክ ኒልሰን ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ “ግሪንላንድ የተገኘሁት የዴንማርክን ድጋፍ ለማሳየት ነው። ከባድ ጊዜ ላይ እንደሆንን ሁሉም ያውቃል” ብለዋል።

    በቀጣይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ከግዛቲቱ መሪ ጋር እንደሚወያዩ ጠቅሰው፤ “ዲፕሎማሲያዊ እና የፖለቲካ መንገድ እንከተላለን” ሲሉም አክለዋል።

  9. ጦርነት ለማስቆም ውይይት እየተደረገ ባለበት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ

    ሩሲያ ባደረሰችው የሰው አልባ አውሮፕላን እና ሚሳዔል ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፣ 23 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸው ተገልጿል።

    የፎቶው ባለመብት, State Emergency Service of Ukraine

    የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካ የተሳተፈችበት ውይይት እየተደረገ ባለበት ወቅት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ።

    ሩሲያ ባደረሰችው የሰው አልባ አውሮፕላን እና ሚሳዔል ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፣ 23 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸው ተገልጿል።

    የዩክሬን መዲና ኪቭ ከንቲባ “በጠላት ከፍተኛ ጥቃት” እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል። የካርኪቭ ከተማ ከንቲባ ደግሞ 19 ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጸዋል።

    የሩሲያ፣ ዩክሬን እና አሜሪካ ልዑካን በአቡ ዳቢ የመጀመሪያ ዙር ውይይት ለማድረግ መገናኘታቸው ይፋ ተደርጓል።

    ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ሩሲያ የተሳተፈችበት የመጀመሪያው የሦስትዮች ውይይት እንደሆነ ተገልጿል።

    አንድ የቢቢሲ ምንጭ እንደተናገሩት፤ በውይይቱ የተወሰነ ለውጥ ቢስተዋልም ከግዛት ይዞታ ጋር የተያያዙ ቁልፍ ጉዳዮች መፍትሔ አላገኙም።

  10. የአውሮፓ ኅብረት እና ቻይና ቁልፍ የንግድ ስምምነት እንደሚፈጽሙ ተገለጸ

    የአውሮፓ ከሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቮን ደር ሌይን እና የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ

    የፎቶው ባለመብት, Hindustan Times via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ ከሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቮን ደር ሌይን እና የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ዛቻ ያሰጋቸው የአውሮፓ ኅብረት እና ሕንድ የንግድ ስምምነት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።

    የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ሉዊስ ዳ ኮስታ እና የአውሮፓ ከሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቮን ደር ሌይን በቀጣይ ሰኞ በሚካሄደው የሕንድ ብሔራዊ ቀን ላይ ዋነኛ የክብር እንግዶች ሆነው ይታደማሉ።

    አሜሪካ 50% ታሪፍ የጣለችባት የእስያ ሦስተኛ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ያላት ሕንድ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ቁልፍ ስምምነቶች እንደምታደርግ ተገልጿል።

    ተንታኞች እንደሚሉት የአውሮፓ ኅብረት እና የሕንድ መቀራረብ የትራምፕ አስተዳደር የፈጠው የንግድ አለመረጋጋት ውጤት ነው ሊባል ይችላል።

    የሚፈረመው የንግድ ስምምነት ገና ይፋ ባይደረግም “የስምምነቶች ሁሉ ቁንጮ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።

    ትራምፕ ግሪንላንድን የመጠቅለል ዕቅዳቸውን የማይደግፉ የአውሮፓ አገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸው ውዝግብ ፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም። በዳቮስ የምጣኔ ሃብት ጉባዔ ላይ ግን ታሪፍ የመጣል ዕቅዳቸውን እንደሰረዙ ገልጸዋል።

  11. የታሊባን አስተዳደር ወጣቷን ስፖርተኛ ለሁለት ሳምንት አስሮ ለቀቀ

    ኻዲጃ አህመድዛዳ

    የፎቶው ባለመብት, Social Media

    የምስሉ መግለጫ, ኻዲጃ አህመድዛዳ

    አፍጋኒስታናዊቷ ወጣት ለሴቶች ቴክዋንዷ የሚያሰለጥን ጂም በመክፈቷ በታሊባን አስተዳደር ለሁለት ሳምንት ያህል ታስራ ተፈታች።

    የ22 ዓመቷ ኻዲጃ አህመድዛዳ ሴቶችን የሚመለከቱ የስፖርት ማሠልጠኛዎችን ስለምክፈት በአገሪቱ ያለውን ደንብ በመጣስ ለ13 ቀናት ታስራ መቆየቷን የታሊባን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

    ወጣቷ ሂጃብ በአግባቡ ባለመልበስ፣ ሙዚቃ በማጫወት እና ወንዶች እና ሴቶች በአንድ ላይ እንዲሆኑ በመፍቀድ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣት በኋላ የአስራ ሦስት ቀናት እስር እንደተፈረደባት ባለሥልጣኑ ገልጸዋል።

    እስላማዊ ሕጎችን በጥብቅ ትርጓሜ የሚያስፈጽመው ታሊባን ወደ አፍጋኒስታን የመሪነት መንበርን ከአምስት ዓመት በፊት ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ “አመቺ ሁኔታ ሲኖር ይከፈታሉ” ተብሎ ሁሉም የሴቶች የስፖርት ለክቦች ተዘግተዋል።

    ነገር ግን አስካሁን ድረስ ለአንድም የስፖርት ክለብ ፈቃድ ያልተሰጠ ሲሆን፣ ሴቶችም በስፖርት ውድድሮች ላይ መሳተፍ አይችሉም።

    ታሊባን ወደ ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ የሴቶችን የመሥራት እና መማር መብቶች የገደበ ሲሆን፣ ጥብቅ የአለባበስ ደንቦችንም ተግባራዊ እያደረገ ነው።

  12. የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ከእስራኤል ፕሬዝዳንት እና ከትራምፕ ልጅ ጋር ተወያዩ

    ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ከትራምፕ ልጅ ኤሪክ ትራምፕ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Somaliland TV

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ከትራምፕ ልጅ ኤሪክ ትራምፕ ጋር

    የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ከተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ስብሰባ በተጓዳኝ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተነገረ።

    ዳቮስ ተገኝተው የነበሩት ፕሬዝዳንቱ ባደረጓቸው የተለያዩ ውይይቶች ትኩረት ያደረጉት የግዛቲቱን ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ማጠናከር እና የውጭ አገራት መዋዕለ ነዋይ መሳብ ላይ ነው ተብሏል።

    የፕሬዝዳንት አብዲራህማን ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞክ እና የትራምፕ ድርጅቶች ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሆነው የትራምፕ ልጅ ኤሪክ ትራምፕን ጨምሮ ከሌሎችም ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የንግድ ሰዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

    የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት እንዳሉት የፕሬዝዳንቱ ውይይት በምጣኔ ሀብታዊ ትብብር፣ በኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲሁም አካባቢው በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ባለው ቁልፍ ሚና ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል።

    በተጨማሪም የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት የበርበራ ወደብ ለመርከቦች ያለውን አመቺነት በመጥቀስ አገራቸው ለኢንቨስትመንት ክፍት መሆኗን በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል።

    የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አብዲራህማን ዱዋሌ ባይሌ ለቢቢሲ ሶማሊኛ እንዳረጋገጡት ከኤሪክ ትራምፕ ጋር በተደረገው ውይይት በሶማሊላንድ ስላለው የኢንቨስትመንት ዕድሎች ማንሳታቸውን እና ኤሪክ ያለውን ፍላጎት መግለጹን ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ከእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, @Isaac_Herzog

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ከእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ጋር
  13. የአሜሪካ የጦር መርከቦች ወደ ኢራን እያቀኑ መሆናቸውን ትራምፕ ተናገሩ

    ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን

    ኢራን ተቃዋሚዎችን በመግደል እና የኑክሌር ፕሮግራሟን መልሳ በመጀመሯ እያስጠነቀቁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ የጦር መርከቦቻቸውን ወደ አካባቢው ማሰማራታቸውን ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ ከስዊትዘርላንድ ወደ አገራቸው ሲመለሱ እንደገለጹት የጦር መርከቦች ቡድን መንቀሳቀሱን፤ ነገር ግን በኢራን ላይ እንደማይጠቀሟቸው ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

    "አስፈላጊ ከሆን በማለት በርካታ መርከቦቻችን ወደዚያ አቅጣጫ እያመሩ ነው. . . ምንም ነገር እንዳይከሰት ነው የምፈልገው፤ ነገር ግን በጣም በቅርበት ነው እየተከታተልናቸው ያለነው” ሲሉ ትኩረታቸው ኢራን ላይ መሆኑን ትራምፕ ተናግረዋል።

    ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የጦር አውሮፕላን ተሸካሚው ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን የተባለው የጦር መርከብን ጨምሮ ሌሎች አውዳሚ መርከቦች በቀጣይ ቀናት ወደ መካከለኛው እንደሚደርሱ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    በቀጣናው ያሉትን የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮችን ከኢራን ጥቃቶችን ለመጠበቅ ተጨማሪ የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓቶች በመካከለኛው ምሥራቅ ለመትከል እየታሰበ ነው ሲሉም አንድ ባለሥልጣን ገልጸዋል።

    በኢራን ውስጥ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ ከአሜሪካ ጋር የነበረው ፍጥጫ በጠነከረበት ባለፈው ሳምንት በእስያ ፓሲፊክ አካባቢ ተሰማርተው የነበሩ የአሜሪካ መርከቦች ወደ አካባቢው ጉዞ ጀምረዋል።

    ትራምፕ በርካታ ተቃዋሚዎች በተገደሉበት ጊዜ አሜሪካ ጣልቃ እንደምትገባ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ የቆዩ ሲሆን፣ ተቃውሞው ግን እየተቀዛቀዘ መጥቷል።

    ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎችን ኢራን እንዳትገድል በሰጡት ማስጠንቀቂያ 840 የሚደርሱ ሰዎችን ሕይወት ማዳናቸውን ትራምፕ ተናግረዋል።

  14. ቲክቶክ ድርሻውን ለትራምፕ ደጋፊዎች በማጋራት በአሜሪካ ከመታገድ አመለጠ

    ቲክቶክ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቲክቶክ ከአሜሪካውያን ባለድርሻዎች ጋር ሽርክና በመመሥረት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ ውስጥ እንዳይሠራ ሊጥሉበት ከነበረው ዕገዳ ማምለጡ ተነገረ።

    በስምምነቱ መሠረት በአሜሪካ ውስጥ በሚኖረው እንቅስቃሴ ብዙኃኑ በአሜሪካውያን ድርሻነት የተያዘ ሽርክና በመፍጠር በቻይናውያን ተይዟል የሚለውን ክስ ለማስቀረት ችሏል።

    በሽርክናው ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ባለሀብቶች ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸው ተነግሯል።

    ከእነዚህም መካከል የትራምፕ የረዥም ጊዜ ወዳጅ እና የሪፐብሊካን ፓርቲ ከፍተኛ ገንዘብ ለጋሽ የሆኑት ላሪ ኤሊሰን ይገኙበታል።

    ኦራክል የተባለው የኤሊሰን የቴክኖሎጂ ኩባንያ በሽርክናው ውስጥ የ15 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ኦራክል ቲክቶክን ለስኬት የሚያበቃውን ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) ያዘጋጃል።

    የቲክቶክ ባለቤት የሆነው የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ 19.9 በመቶ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።

    ለቲክቶክ ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት ካላገኘ በአሜሪካ ውስጥ እንዲታገድ እንደሚያደርጉ ሲያስጠነቅቁ የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ አሁን በተደረሰው ስምምነት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

    በአሜሪካ የቲክቶክ ባለቤትነት ላይ በተደረገው ለውጥ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች ከዚህ በፊት ሲያዩ የነበሩትን ዓለም አቀፍ ይዘቶችን ላያገኙ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው። በርካታ ተጠቃሚዎችም በስምምነቱ ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።

    ቲክቶክ በአሜሪካ ውስጥ 200 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን በመያዝ ከፍተኛ ተከታይ ካላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች መካከል አንዱ ነው።

  15. አሜሪካ በጋዛ የሚገነቡ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ይፋ አደረገች

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጋዛ የሚገነቡ ሕንጻዎችን ከሚያሳይ ምሥል ጎን ተቀምጠው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጋዛ የሚገነቡ ሕንጻዎችን ከሚያሳይ ምሥል ጎን ተቀምጠው

    አሜሪካ በጦርነት የወደመችውን ጋዛ በማጽዳት ልትገነባቸው ያቀደቻቸውን ሰማይ ጠቅስ ሕንጻዎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ይፋ አደረገች።

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲስ የሰላም ቦርድ ስዊትዘርላንድ ዳቮስ ውስጥ ይፋ በሆነበት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ወቅት በቀረቡት ምሥሎች ‘አዲሲቷ ጋዛ’ ወደፊት የሚኖራት ገጽታ እንዲታይ ተደርጓል።

    በምሥሎቹ ላይ ጋዛ በስተምዕራብ በኩል በምትዋሰነው የሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ ተከትለው የሚገነቡ በርካታ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች፣ በራፋህ አካባቢ የሚሠሩት የመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ደረጃ በደረጃ የሚገነቡ አዳዲስ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ቦታዎች በካርታ ቀርበዋል።

    ትራምፕ በዚህ ዕቅዳቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ "ከልቤ የሪል ስቴት ግንባታ ሰው ነኝ፤ ለዚህ ደግሞ ቦታ ወሳኝ ነው” በማለት በውቡ የጋዛ የባሕር ዳርቻ የሚገነቡት ሕንጻዎች የብዙ ሰዎች ንብረት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

    እስራኤል በጋዛ ላይ ለሁለት ዓመታት ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ከባድ ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ ጦርነቱ እንዲቆም ካገዙ ሰዎች መካከል የሆነው የትራምፕ የልጃቸው ባል ጃሬድ ኩሽነር በዚህ የግንባታ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተነግሯል።

    ኩሽነር እንዳለው እስራኤል በጦርነቱ 90 ሺህ ቶን አውዳሚ ፈንጂዎችን በጋዛ ጥቅም ላይ ያዋለች ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ 60 ሚሊዮን ቶን ፍርስራሽ ግዛቲቷን ሞልቷታል።

    ጋዛን መልሶ መገንባቱ ከመጀመሩ በፊት የተከመረውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ፍርስራሽ ማጽዳት የሚፈለግ ሲሆን ይህም ረዥም ጊዜ እንደሚፈልግ ተነግሯል።

  16. በጋምቤላ ከተማ በተሽከርካሪዎች እና በአገልግሎቶች ላይ ገደብ ተጣለ

    የጋምቤላ ከተማ

    የፎቶው ባለመብት, Gambella city

    ለሳምንታት በውጥረት ውስጥ የቆየችው የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር በአገልግሎቶች እና በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጣለ።

    ከአንድ ወር በፊት በጋምቤላ ክልል ባጋጠሙ ግጭቶች የተነሳ ዋና ከተማዋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎ የነበረ ሲሆን አሁን የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ ገደቦችን መጣሉን አስታውቋል።

    የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር በዝርዝር ባልገለጸው ነገር ግን “በከተማው ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ” ምክንያት ከዛሬ አርብ ጥር 15/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑ ክልከላዎችን አስታውቋል።

    በዚህም መሠረት ሞተር ሳይክሎችን በከተማዋ ውስጥ ማሽከርከር ላልተወሰነ ጊዜ በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፣ ባጃጆች ከጥዋቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ገደብ ተጥሏል።

    በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች እና ግሮሰሪዎች አግልግሎት መስጠት የሚችሉት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲሆን ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

    ከአንድ ወር በፊት የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ መገደልን ተከትሎ በተፈጠረ የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።

  17. አሜሪካ ያለባትን ዕዳ ሳትከፍል ከዓለም የጤና ድርጅት በይፋ ለቀቀች

    ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

    አሜሪካ ከዓመት በፊት በሰጠችው ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሠረት የሚጠበቅባትን ክፍያ ሳትፈጽም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ከሆነው የዓለም የጤና ድርጅት አባልነት በይፋ ለቅቃ ወጣች።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመናቸውን በጀመሩበት ዕለት ካስተላላፏቸው ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔዎች መካከል አንዱ የሆነው ከዓለም ጤና ድርጅት መውጣት ተግባራዊ ሆኗል።

    ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከሚገኘው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት እንዲነሳ መደረጉን ሮይተርስ የዜና ወኪል የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።

    ከአሜሪካ ጤና እና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች በጋራ በወጣው መግለጫ መሠረት ከዚህ በኋላ አገሪቱ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ውስን እና ከተቋሙ መውጣቷን ለማጠናቀቅ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን ተጠቅሷል።

    የአሜሪካ የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ይህ እርምጃ የተወሰደው የዓለም የጤና ድርጅት የኮቪድ ወረርሽኝን “በአግባቡ ስላልያዘው”፣ ለውጥ ለማድረግ ባለመቻሉ እና በአባል አገራት ፖለቲካዊ ተጽእኖ ስላለበት መሆኑን ጠቅሷል።

    ድርጅቱ የቀረቡበትበትን ክሶች የተቃወመ ሲሆን፣ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የአሜሪካ ከተቋሙ መውጣት ጉዳቱ ለዓለም ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካ ጭምር ነው ብለዋል።

    በተለምዶው አሜሪካ ለለዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ገንዘብ ከሚሰጡ አገራት መካከል የነበረች ብትሆንም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሚጠበቅባትን ክፍያ ባለመፈጸሟ በድርጅቱ ውስጥ በርካታ ሠራተኞች እንዲቀነሱ አድርጓል።

    የድርጅቱ ጠበቆች አሜሪካ ቃል በገባችው መሠረት የቀረውን 260 ሚሊዮን ዶላር የመክፈል ግዴታ አለባት በማለት እየተከራከሩ ሲሆን፣ አሜሪካ ግን ገንዘቡን ለመክፈል የሚያስገድዳት ምክንያት እንደሌለ ገልጻለች።

    አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት የጤና ባለሥልጣን "በድርጅቱ ውስጥ በታዛቢነት የመሳተፍም ሆነ መልሶ አባል የመሆን ዕቅድ የለንም” ሲሉ ተናግረዋል።

    በበሽታዎች ቁጥጥር እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው በሌሎች የኅብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ላይ በዓለም አቀፍ ድርጅት በኩል ሳይሆን በቀጥታ ከአገራት ጋር ለመሥራት አቅዳለች።

    በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመራው እና ከ190 በላይ አገራትን በአባልነት ከያዘው ተቋም አሜሪካ ለመውጣት መወሰኗ በአሜሪካ እንዲሁም በቀሪው የዓለም ክፍል የሚከናወኑ የጤና ሥራዎችን የሚጎዳ መሆኑ እየተነገረ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ የሚጠበቅበትን አላከናወነም በሚል ከድርጅቱ ለመውጣት ወስነው የነበረ ቢሆንም በጆ ባይደን በመሸነፋቸው ተግበራዊ ሳይሆን መቅረቱ ይታወሳል።

    አሜሪካ እራሷን ያገለለችው ከዓለም ጤና ድርጅት ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከበርካታ የመንግሥታቱ ድርጅት አካላት ከሆኑ ተቋማት ለመውጣት ከመወሰኗ በተጨማሪ፣ የሰላም ቦርድ በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያስተዋወቁት ስብስብ የተባበሩት መንግሥታትን ሚና የሚያዳክም ነው በሚል እየተተቸ ይገኛል።

  18. ቻይና በትራምፕ የሰላም ቦርድ ላይ ያላትን ብርቱ ጥርጣሬ እየገለጸች ነው

    ዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ

    ቻይና በትራምፕ የሰላም ቦርድ አባል እንድትሆን ብትጋበዝም ለመሳተፍ ገና ፈቃደኝነቷን ካለመግለጿ በተጨማሪ በተቋሙ ላይ ብርቱ ጥርጣሬ እንዳላት አሳወቀች።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ "የቱንም ያህል የዓለም ሁኔታ ቢቀያየርም፣ ቻይና የተባበሩት መንግሥታትን ማዕከል ያደረገ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓትን ነው የምትደግፈው” ሲሉ ቤይጂንግ ውስጥ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    የቻይና መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንም በትራምፕ የሰላም ቦርድ ላይ ትችት ያቀረቡ ሲሆን፣ ኮሚቴው “በሃቅ ለሰላም የሚሠራ ነው ወይ?" የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

    በተጨማሪም ቦርዱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት “የግል ክልብ ወይም ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጣ የንግድ የዳይሬክተሮች ቦርድ” እየፈጠሩ ነው የሚል ስጋትንም አንስተዋል።

    በቻይና በኩል ያለው ዋነኛ ስጋት ትራምፕ የተባበሩት መንግሥታትን የመተካት ፍላጎት አላቸው የሚል ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንትም የሰላም ቦርዱ የመንግሥታቱ ድርጅትን የሚተካ ተቋም እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሊሆን ይችላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት መሥራች አባል እና ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ ያለውን ተሳትፎ ለማስፋት ተጨባጭ ጥረት ስደታርግ ለቆየችው ቻይና ይህ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ምላሽ የሚያስደነግጥ ነው።

    ቻይና በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል እና ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ካላቸው አምስት አገራት መካከል አምዷ ናት።

    ስለዚህም በአሜሪካ በሚመራው እና የመጨረሻው ውሳኔ በፕሬዝዳንት ትራምፕ በሚሰጥበት የሰላም ቦርድ ውስጥ ከአሜካ ጋር በአቻነት በማትታይነት ሁኔታ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት ያላት አትመስልም።

    ነገር ግን ውጥረት ውስጥ ገብቶ የነበረው ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በተረጋጋበት በአሁኑ ወቅት በዶናልድ ትራምፕ ዕቅድ ላይ በይፋ ትችት ለመሰንዘር አልፈለገችም።

    ከዚያ ይልቅ ግን ቻይና በይፋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስፈላጊነትን አጽንኦት በመስጠት ዲፕሎማሲያዊ መንገድን መከተል መርጣለች።

  19. ሊቨርፑል ከፍተኛ ገቢ ያገኘ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ሆነ

    ሊቨርፑል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሊቨርፑል ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ገቢ ያገኘ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ መሆን መቻሉን የፋይናንስ ተቋም ሆነው ዴሎይት አስታወቀ።

    ባለፈው ዓመት የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻሉት ቀያዮቹ 702 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባታቸው ነው የተገለጸው።

    ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ ዴሎይት ደረጃውን ይፋ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ዝቅተኛ የሚባለውን ደረጃ ማስመዝገቡ ተገልጿል። ማንቸስተር ሲቲም ደረጃው መቀነሱ ነው የተነገረው።

    ሪያል ማድሪድ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ለመሆን ባይችልም 1.2 ቢሊዮን ዩሮ በማስገባት ቀዳሚ ክለብ ለመሆን ችሏል። ባርሴሎና በበኩሉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

    የካታላኑ ቡድን ሜዳው እየተጠገነ በመሆኑ ያለፈውን የውድድር ዓመት ከኑ ካምፕ ውጭ ለመጫወት ቢገደድም ከ2019-20 የውድድር ዓመት በኋላ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዝ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆኗል።

    የጀርመኑ ባየር ሚዩኒክ በ861 ሚሊዮን ዩሮ ሦስተኛ፣ የቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፓሪ ሳን ዠርሜን በ837 ሚሊዮን ዩሮ አራተኛ እና ሊቨርፑል አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

    ማንችስተር ሲቲ 829 ሚሊዮን ዩሮ ከሁለተኛ ደረጃ ወደ ስድስተኛ ዝቅ ብሏል።

    በፕሪሚየር ሊጉ 15ኛ ሆኖ የጨረሰው እና በአውሮፓ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ በቶተንሃም የተሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ በ739 ሚሊዮን ዩሮ ከነበረበት አራተኛ ደረጃ ወደ 8ኛ ደረጃ ወርዷል።

  20. ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስላቋቋሙት የጋዛ የሰላም ቦርድ ምን ይታወቃል?

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ትራምፕ የሚመሩት የጋዛ የሰላም ቦርድ መጀመሪያ ላይ ዓላማው አድርጎ የተነሳው ለሁለት ዓመታት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም እና ጋዛን መልሶ ለመገንባት ነበር።

    ነገር ግን ሾልኮ የወጣው የቦርዱ የመተዳደሪያ ቻርተር ላይ ስለፍልስጤም ግዛት ምንም ነገር ካለመጥቀሱ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሚና ለመተካት የታሰበ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬን ፈጥሯል።

    በቦርዱ የሰላም ማዕቀፍ ውስጥ “የጋዛ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ” የሚባል አካል ግን ተካቶበታል። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እንደሚለው ይህ አካል በጋዛ አስተዳደር ቡድን አማካኝነት በጋዛ ውስጥ የሚከናወኑ ሁሉንም ተግባራትን የመምራት ኃላፊነት አለበት።

    ስለ ቦርዱ ምን ይታወቃል?

    ሾልኮ የወጣው ሰነድ እንደሚያመለክተው ቦርዱ በዓለም አቀፍ ሕግ ሥር በመሆን የሰላም ግንባታ ተግባራትን የማከናወን ሥልጣን ያለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እንደሚሆን ተጠቅሷል።

    ይፋ ባልተደረገው ቻርተር ላይ እንደሰፈረው ቦርዱ ወደ ሥራ የሚገባው ሦስት መንግሥታት በይፋ ለዓላማው ተባባሪ መሆናቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው።

    የቦርዱ አባል አገራት የሚታደስ የሦስት ዓመታት መቀመጫ በቦርዱ ውስጥ የሚኖራቸው ሲሆን፣ ቋሚ የቦርዱ አባል ለመሆን አንድ ቢሊዮን ዶላር መዋጮ መክፈል እንደሚያስፈልጋቸው ሰነዱ አመልክቷል።

    ዶናልድ ትራምፕ የቦርዱ ሊቀ መንበር እና በተናጠል ደግሞ የአሜሪካ ተወካይ ሆነው ይሳተፋሉ። በዚህም የሥራ አስፈጻሚ አባላትን መሾም እና ሌሎች ተጨማሪ አካላትን የማቋቋም ወይም የማፍረስ ሥልጣን አላቸው።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮን፣ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋን እና የቀድሞውን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌይርን ጨምሮ አስካሁን ሰባት መሥራች የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት በትራምፕ ተሰይመዋል።

    ሩሲያስ?

    ትራምፕ እንደተናገሩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሰላም ቦርዱ ውስጥ ለመሳተፍ “ፈቃደኛ” መሆናቸውን እና እንዳይንቀሳቀስ የተያዘባቸው የሩሲያ ሀብት ለቦርዱ ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃደኛ መሆናቸውን ተነግሯል።