ሕዋ ላይ እንዴት ለአንድ ዓመት ይኖራል?

ጠፈርተኛ ስኮት ኬሊ ለአንድ ዓመት ያህል ሕዋ ላይ ኖሯል።

የፎቶው ባለመብት, NASA

የምስሉ መግለጫ, ጠፈርተኛ ስኮት ኬሊ ለአንድ ዓመት ያህል ሕዋ ላይ ኖሯል።

ከአራት ዓመት በፊት ከናሳ በጡረታ የተገለለው ስኮት ኬሊ ጠፈርተኛ ነው። ለአንድ ዓመት ያህል ሕዋ ላይ ኖሯል።

ጠፈርተኛው 'ኢንዱራንስ' የተባለ መጽሐፍ አሳትሟል ።

እአአ 2015 ላይ በሩስያው መንኮራኩር ውስጥ ከነበሩት አንዱ ነበር።

ከሩስያውያኑ ጌኔዲ ፓዳካላ እና ሚካሂል ኮርኒንኮ ጋር ሳሉ፤ አንድ ብረታማ ቁስ በሰከንድ 14 ኪሎ ሜትር እየተምዘገዘገ ወደ መንኮራኩራቸው እየተጠጋ መሆኑ ተነገራቸው። መንኮራኩራቸው ከተመታ በሕይወት የመትረፍ እድል አይኖራቸውም።

ስኮት እንደዚህ ያለ ለሕይወት የሚያሰጋ ነገር ሲገጥመው የመጀመሪያው አይደለም።

"አደጋ ቢደርስ ኖሮ ሦስታችንም በሚሊሰከንዶች ጊዜ ውስጥ እንደ አቶም በሚሊዮን አቅጣጫዎች እንበተን ነበር" ይላል።

የሕዋ ላይ ኑሮ ከምድር ጋር የሚያመሳስለው ጥቂት ነገር አለ። በቪድዮ መደዋወል፣ ማጽዳት ወዘተ. . .

በአብዛኛው ግን ሕዋ ፈታኝ ነው።

ስኮት ከ2007 አንስቶ ሦስት ጊዜ ወደ ሕዋ ተጉዟል። እውቅና ያተረፈው ግን ከ2005 እስከ 2016 በሕዋ ባደረገው ቆይታ ነው።

ከሱ በፊት ረዥም ጊዜ ሕዋ ላይ የኖረው አሜሪካዊ ጠፈርተኛ ማይክል ሎፔዝ 100 ቀናት ቆይቷል።

ስኮት ይህንን ክብረ ወሰን ሰብሯል።

ሌላ ስኮት የሚታወቅበት ነገር መንታ ወንድሙ ማርክ ነው። እንደሱው ናሳ ውስጥ ይሠራል።

ስኮት ሕዋ ላይ አንድ ዓመት ሲኖር አንድም ቀን ወደ መሬት ለመመለስ እንዳልጓጓ ይናገራል።

"ከአንድ ዓመት በላይ የሚያስቆየኝ ምክንያት ባገኝም እዛው እሆን ነበር" ነው የሚለው።

አንዳንድ ጠፈርተኞች ሕዋ ላይ ያለው የብቸኛነት ኑሮ የሥነ ልቦና ጫና ያሳድርባቸዋል።

መንታ ወንድሙ ማርክ እንደሱው ናሳ ውስጥ ይሠራል።

የፎቶው ባለመብት, NASA

የምስሉ መግለጫ, መንታ ወንድሙ ማርክ እንደሱው ናሳ ውስጥ ይሠራል።

ስኮት ግን "ዋናው ነገር ራስን ማዝናናት መቻል ነው። ለሁሉም ሰው ቀላል ነው ማለት ግን አይደለም" ብሎ ያምናል።

ለሱ ከሕዋ ኑሮ ከባዱ እንደልብ ከመንኮራኩር መውጣት አለመቻል ነው። በጠባብ ቦታ ከሰዎች ጋር ለረዥም ጊዜ አብሮ መኖርም ቀላል አይደለም።

በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ጠፈርተኞች ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ይፈጠራል።

ስኮት ሕዋ ላይ አብረውት ከኖሩ ጠፈርተኞች ጋር ምድር ሲመለስም በወዳጅነት ቀጥሏል። ዓለም አቀፉ የሕዋ ተቋም የአገሮች ትብብር ተምሳሌት እንደሆነ ይናገራል።

ሕዋ ላይ ሳለ ከሥራ በተጨማሪ ዘና ይልም ነበር። በተለይም የዝንጀሮ ልብስ መልበስ በጣም ያዝናናዋል።

የዝንጀሮ መልክ ያለውን ልብስ የሰጠው ናሳ የሚሠራው መንታ ወንድሙ ነው።

ወንድማማቾቹ ያደጉት ኒው ጀርሲ ሲሆን፤ ቤተሰቦቻቸው ፖሊሶች ናቸው።

ስኮት እና ማርክ ልጅ ሳሉ ጀምሮ አደገኛ ነገር መሞከር ይወዳሉ። በተደጋጋሚ ጉዳት ይደርስባቸውም ነበር።

ትምህርት ቤት ሲገቡ ማርክ ጎበዝ ሆነ። ስኮት በተቃራኒው ዝንጉ ነበር። ኮሌጅ ሲገቡ ማርክ ስኮትን ይመክረው እንደነበር ያስታውሳል።

ስኮት መጀመሪያ ላይ የውጊያ አውሮፕላን አብራሪ ሆነ።

በመጀመሪያው የገልፍ ጦርነት ወቅት ተሠማርቶም ነበር። 1996 ላይ ከወንድሙ ጋር ናሳን ተቀላቀለ።

ወንድማማቾቹ በአንድ መንኮራኩር አብራሪነት ተሳትፈዋል።

2003 ላይ ኮሎምቢያ የተባለ መንኮራኩር ወደ ምድር ሲመለስ ተከስክሶ ሰባት ጠፈርተኞች ሞተዋል።

ያ አጋጣሚ የመንኮርኩር በረራ አስጊነትን ያሳየ ነበር። የናሳ የደህንነት ፖሊሲም ተተችቷል።

ያኔ ከሞቱት ጠፈርተኞች አንዱ የስኮት ጓደኛ ነው።

ቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግለት ዓለም አቀፍ የመንኮራኩር ደህንነት ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ሲዘጋጅ ነበር።

ስኮት ለአንድ ዓመት ወደ ሕዋ ሊጓዝ እንደሆነ ሲነገር ትኩረታቸው ከተሳቡ መካከል የዘረ መል ተመራማሪዎች ይገኙበታል።

አንድ ሰው ዘለግ ላለ ጊዜ ሕዋ ላይ ሲኖር የሚያድርበትን ተጽዕኖ ለመረዳት፤ ስኮትን እና መንታ ወንድሙ ማርክን ለማነጻጸር ነበር ተመራማሪዎቹ ያሰቡት።

የስኮትን ሰውነት ምድር ላይ ከቀረው ወንድሙ ጋር በማወዳደር የሥነ ልቦና፣ በሽታ የመከላከል እና የዘረ መል መዋቅር ለውጡን ገምግመዋል።

የስኮት ዘረ መል መዋቅር ላይ የታየው ለውጥ ለጨረራ መጋለጡ ያሳደረበትን ተጽዕኖ ያሳየ ነበር።

ስኮት ከሕዋ ሲመለስ የክሮሞዞም፣ የደም፣ የሰውነት መጠን ለውጥም አሳይቷል። ወደ መሬት ከተመለሰ በኋላ ግን ወደ ቀደመው ተክለ ሰውነቱ ተመልሷል።

ስኮት ከሕዋ ከተመለሰ አራት ዓመታት አስቆጥሯል። በቆይታው ለውጥ ያስተዋለው እይታው እንደሆነ ይናገራል።

ተመራማሪዎች መንታዎቹ ላይ የሠሩት ጥናት፤ ሰዎችን ወደ ማርስ ለመላክ ለተያዘው እቅድም መረጃ ሰጥቷል።

ከመሬት 34 ሚሊዮን ማይል ወደምትርቀው ማርስ ተጉዞ ወደ ምድር ለመመለስ ዘጠኝ ወራት ይወስዳል።

ጠፈርተኞች ለጨረራ የሚጋለጡት በአስር እጥፍ ስለሆነ ለካንሰር ወይም ለሌላ ህመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ ይሰጋል።

"ያለው አማራጭ ራስን መከላከያ መንገድ ማግኘት ወይም በፍጥነት ወደ ማርስ መድረስ ነው። ካልሆነ ግን ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል አምኖ መጓዝ ነው" ይላል ስኮት።

አሁን ከናሳ ጡረታ ወጥቶ ዴንቨር ውስጥ ከባለቤቱ ጋር ይኖራል። በተለያዩ መድረኮች ስለ ሕዋ ቆይታው ንግግር በማድረግ እና በመጻፍ ጊዜውን ያሳልፋል።

ከዚህ በኋላ ምናልባትንም ወደ ሕዋ የሚላክ የሮኬን መንኮራኩር አብራሪ ከተፈለገ ስኮት ይጠራ ይሆናል።