ሕዋ ፡ ከአሜሪካ ተባሮ ቻይናን ወደ ሕዋ እንድትመጥቅ ያስቻላት ሰው

ኩዊያን ዙሴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይናዊው ሳይንቲስት አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ኃያል አገራትን ወደ ሕዋ እንዲመጥቁ አድረጓል። ነገር ግን ታሪኩ የሚወሳው በአንደኛዋ አገር ውስጥ ብቻ ነው።

ለዚህ ሰው መዘከሪያ ሻንጋሃይ፣ ቻይና ውስጥ አንድ ሙሉ ሙዚዬም ቆሟል።

በዚህ ሙዚዬም ውስጥ 70 ሺህ የሚደርሱ ቁሳቁሶች ቻይና 'የሕዝብ ሳይንቲስት' እያለች የምትጠራውን ኩዊያን ዙሴንን ለማስታወስ ተሰድረዋል።

ኩዊያን የቻይና ሚሳኤልና የሕዋ ፕሮግራም አባት ነው።

ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዋ ያመጠቀችውን የመጀመሪያ ሳተላይትን ገንብተው ዕውን ካደረጉት መካከል ነው። አገሪቱ ላደረገችው የሚሳኤል ግንባታ ያበረከተው ጥናትም ቻይናን ኒውክሌር ታጣቂ አድርጓታል።

ሰውዬው ቻይና ውስጥ ስሙ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል።

ነገር ግን ከአስር ዓመት በላይ በተማረባትና በሠራባት ሌላኛዋ ኃያል አገር እምብዛም አይታወስም።

ኩዊያን የተወለደው በጎሮጎሳውያኑ በ1911 ነበር። ቤተሰቦቹ የተማሩ ናቸው። አባቱ የቻይናን ዘመናዊ ትምህርት ሥርዓት ከዘረጉት ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ኩዊያንም እጅግ ጎበዝ ተማሪ ነበር። ከሻንግሃይ ጂያዎ ቶንግ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ተመርቆ የአሜሪካው ማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ የመማር ዕድል አገኘ።

በ1935 ፀጉሩን በመስመር የተቆረጠ፤ ቦላሌ በልኩ የታጠቀ ቻይናዊ ለትምህርት ቦስተን ደረሰ - ማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ለመማር።

ትምህርቱን እንደጨረሰ ካልቴክ እየተባለ ወደ ሚቆላመጠው ዝነኛው የካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ተቋም አቀና።

በወቅቱ ተቋሙ አሉ የሚባሉ መምህራን የሚያስተምሩበት ነበር። ቢሮውን ደግሞ የሚጋራው ታዋቂው ሳይንቲስት ፍራንክ ማሊና ነበር።

ጊዜው የሮኬት ሳይንስን በተመለከተ ጥቂት ተማሪዎች ላይ ብቻ ፍላጎት የሚያሳዩበትና የሚወያዩበት ርዕስ ነበር። የትኛውም ተማሪ ኒውክሌር ሳይንስ የወደፊቱ ዐብይ ርዕስ ይሆናል ብሎ ደፍሮ አይናገርም።

ይህ የተቀየረው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው።

ፍራንክ ማሊና እና ሌሎች ሳይንቲስቶች 'ሳይንስ ስኳድ' ተብለው ነው የሚጠሩት። ይህ ቡድን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤትን ቀልብ መሳብ ጀመረ።

መከላከያው ለቡድኑ ድጋፍ በማድረግ ትናንሽ ክንፍ ያላቸውና በአጭር ርቀት መንደርደሪያ የሚነሱ አውሮፕላኖች እንዲሠሩ ማድረግ ጀመር።

በዚህ ፕሮጀክት ተሳታፊ ከነበሩ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ቻይናዊው ኩዊያን ነው።

በወቅቱ ቻይና ሪፐብሊክ የአሜሪካ አጋር ነበረች። ስለዚህ የኩዊያን በፕሮጀክቱ ላይ መሳተፍ እምብዛም አሳሳቢ አልነበረም።

ይህን ዕድል የተጠቀመው ኩዊያን ድብቅ የሆኑ ጥናቶችን ሳይቀር የማግኘት እድልን አገኘ። ለአሜሪካ ሳይንስ አማካሪ ቦርድም ይሠራል ነበር።

ጦርነቱ ሲያበቃ ኩዊያን ዓለም ውስጥ አሉ ከሚባሉ የጄት ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ለመሆን ችሎ ነበር። ወደ ጀርመን አቅንቶም በጊዜያዊነት ሌፍተናንት ኮሎኔል ሆኗል።

ቻይናዊው ሳይንቲስት አድራሻውን አሜሪካ ባደረገ በአስር ዓመቱ ነገሮች ይወሳሰቡ ጀመር።

በ1949 ሊቀ-መንበር ማኦ አገራቸው ቻይና የኮሚኒስት ሪብሊክ ሆናለች ሲሉ አወጁ። በዚህ ጊዜ ቻይናዊያን አሜሪካ ውስጥ እንደ ጠላት መታየት ጀመሩ።

በተመሳሳይ ወቅት አሜሪካ ውስጥ ሰላዮች እንዳሉ ይነገር ጀመረ። ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ ደግሞ ሊቁ ኩዊያን ሆነ።

ምንም እንኳ ሳይንቲስቱ ሰላይ ስለመሆኑ ማስረጃ ባይቀርብበትም የይለፍ ወረቀቱን ተነጥቆ የቁም እሥረኛ እንዲሆን ተፈረደበት።

የካሊፎርኒያ ቴክኖሎጂ ተቋም [ካልቴክ] ባልደረቦቹ እሱ ንፁህ ነው ብለው ቢከራከሩለትም የሚሰማ ጆሮ ጠፋ።

ከአምስት ዓመት የቁም እሥርና እንግልት በኋላ ፕሬዝደንት አይዘንአወር ወደ ቻይና እንዲባረር ወሰኑ። ሳይንቲስቱም ከባለቤቱና አሜሪካ ከተወደሉ ሁለት ልጆቹ ጋር በመሆን በጀልባ ከአሜሪካ ወጣ፤ ወደዚያች አገር ላይመለስም ቃል ገባ። ቃሉንም አላጠፈም።

ሳይንቲስቱ ቻይና ሲገባ የጀግና አቀባበል የተደረግለት ሲሆን የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ አባል እንዲሆን ጥሪ ቀረበለት። ከዚያም ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሁን ድረስ አገሪቱን በብቸኝነት እያስተዳደረ ያለው ኮሚዩኒስት ፓርቲ አባል ሆነ።

ቻይና ሲገባ የሮኬት ሳይንስ ጉዳይ ብዙም የሚታወቅ አልነበረም። ነገር ግን ከ15 ዓመታት በኋላ ቻይና የመጀመሪያውን ሳተላይት ስታመጥቅ ምርመሩን የመራው እሱ ነበር።

ኩዊያን ለዘመናት ቻይናዊያንን ስለ ሮኬት ሳይንስ አስተምሯል። የቻይና ሉናር ኤክስፕሎሬሽን ፕሮግራም የተሰኘው ተቋም እንዲቋቋም አስተዋፅዖ አድርጓል።

የሚገርመው ቻይና በእሱ አጋዥነት ያበለፀገችውን መሣሪያ አሜሪካ ላይ መተኮሷ ነው። ይህ የሆነው በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ወቅት በፈረንጆቹ 1991 ነበረ።

ዛሬ ቻይናና አሜሪካ መልሰው ፍጥጫ ውስጥ ናቸው። የአሁኑ ፍጥጫ የንግድ ነው፤ የቴክኖሎጂ ደኅንነት ጉዳይም ያጨቃጭቃቸዋል፤ ሌላው ደግሞ ፕሬዝደንት ትራምፕ እንደሚሉት ቻይና ኮቪድ-19ኝ ወደሌሎች አገራት እንዳይዛመት አላደረገችም በሚል ነው።

ምንም እንኳ አሜሪካውያን ኩዊያን ማን እንደሆነ ባያውቁትም በርካታ ቻይናዊ አሜሪካዊያን ይህንን ሊቅ በደንብ ያውቁታል።

ምናልባትም አሜሪካ በግዛቷ ተምሮ ታላቅ ሥራዎችን ማከናወን ያቻለውን ኩዊያንን ወደ ትውልድ አገሩ ቻይና ባታባርረው ኖሮ 'ታላቅ አሜሪካዊ ሳይንቲስት' እተባለ ሥራው ሊወሳ ይችል ነበር።

ኩዊያን አንድ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ እዚህች ዓለም ላይ ኖሯል። በዚህ ጊዜ ቻይና ከድህነት ወደ ዓለም ኃያልነት ተሸጋግራለች።

ከመሬት አልፋ ሕዋ ላይ የበላይ ከሚባሉ አገራት ተርታ ተሰልፋለች።