የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የቀጠናው ኃያልነት ጉዞ

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በየመን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የባለፈው አመት ለበርካታ አገራት ፈታኝ ቢሆንም ለትንሿ ነገር ግን ሃብታሟ አረብ ኤምሬትስ ኃያልነቷን እያስመሰከረችበት ያለፈችበት አመት ሆኗል።

የገልፍ አገሯ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወደ ማርስ መንኮራኩሯን አምጥቃለች፤ ከእስራኤል ጋር ታሪካዊ የሚባል ሰላማዊ ስምምነትን ፈፅማለች፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝንም በመግታት ምስጋና ከተቸራቸውም መካከል አንዷ ሆናለች።

ከዚያም አልፎ ፋብሪካዎቿ ያመረቱትን የኮሮናቫይረስ የህክምና መከላከያ ቁሳቁሶችን በበላይነት ስታስተዳደራት ለነበረው የዩናይትድ ኪንግደምም ልካለች።

በሊቢያ፣ የመንና ሶማሊያ ላይ ያላትን የበላይነቷንን ለማስመስከርም ከቱርክም ጋር ፉክክር ውስጥ ገብታለች።

አምሳኛ አመት የነፃነት በዓሏን ከወራት በኋላ ልታከብር በዝግጅት ያለችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአለም አቀፉ ላይ ኃያልነቷን ለማስፈን እያደረገች ያለችው ምንድን ነው? ማን ነውስ እየመራው ያለው? የቢቢሲው ዘጋቢ ፍራንክ ጋረድነር እንዲህ ቃኝቶታል

ወቅቱ በጎሮጎሳውያኑ 1999 ነው። የኮሶቮ ጦርነትም ለአንድ አመት ያህል የተጧጧፈበት ጊዜ። በአልባንያና በኮሶቮ ድንበር አካባቢ ባለ ድንኳን አካባቢም ቆሜ ነበር።

ቦታው በኮሶቮ ስደተኞች ተሞልቷል። የስደተኞቹ መጠለያ ካምፕ የተቋቋመው በኤምሬትስ ቀይ ጨረቃ ማህበረሰብ ሲሆን፤ የሚያስፈልገውንም ቁሳቁሶች ሞልተውት ነበር። ምግብ አብሳዮች፣ ሃላል ስጋ፣ የቴሌኮም ኢንጂነሮች (መሃንዲሶች)፣ ኢማሞችና ከአፍ ገደፋቸው የታጠቁ ወታደሮችም በአካባቢው ይታያሉ።

ስፍራው የደረስነውም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአየር ኃይል ነበር።

የኮሶቮና አልባንያ ድንበር

የፎቶው ባለመብት, Frank Gardner

አጠገቤም ሆኖ አንድ ረዘም ያለ፣ ጢማም ሰው ጥርሱን እየፋቀ ነበር። የብሪታንያ ሮያል ወታደራዊ ማሰልጠኛ ምሩቁና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ጦርንም ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ እየሞከረ የነበረው ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ነው።

ለቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ጠየቅኩት ብዙም ፍላጎት ባይኖረውም ተስማማ።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከፈረንሳይ ጋር ስላካሄዱት የሁለትዮሽ ስምምነትም ይነግረኝ ጀመር።

አገሩ 400 የፈረንሳይ ታንኮችን እንድትገዛና በለውጡም ፈረንሳይ የኤምሬትስ ወታደሮችን እንድታሰለጥንና በኮሶቮም ጦርነት ላይ እንዲሰማሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

ምንም እንኳን ጦርነቱ የሚካሄድበት የባልካን ግዛት ከመዲናዋ አቡዳቢ የ3 ሺህ 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ያለ ቢሆንም የአረብ ኤምሬትስ ከገልፍ ውጭ አገራት ባሉት አገራትም ቦታ እንዲኖራትም እየሞከረች የነበረበት ወቅት ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ደግፎ በአውሮፓ ላይ ወታደሮች ስታሰማራ የመጀሪያዋ አረብ አገርም ሆናለች።

'ትንንሾቹ ስፓርታ'

በቀጣይነትም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢላማ አፍጋኒስታን ነበረች።

በርካታ የአገሪቷ ዜጎች ባያውቁም የተባበሩት ኤምሬትስ ኔቶን በመደገፍ ወታደሮቿን አሰማርታለች። ከታሊባን መውደቅ በኋላም የኤምሬትሱ አልጋወራሽ የሆኑት ሼክ መሐመድ ቢንዛይድ የኔቶን በአፍጋኒስታን መሰማራት ተቃውመውታል።

በባግራም የጦር ሰፈር የሰፈሩትን የኤምሬትስ ልዩ ኃይል ለማየትም እድል አግኝቼ ነበር- በጎሮጎሳውያኑ 2008።

በደቡብ አሜሪካ በተለይም ብራዚል በተሰሩ የጦር መኪኖች ተጭነው ራቅ ወዳሉ የአፍጋኒስታን መንደሮች ውስጥ ገብተው ቁርአን ይሰጡ ነበር፤ ጣፋጭም እንዲሁ። በዕድሜ ባለፀጋ ከሆኑት አፍጋኒስታውያንም ጋር ቁጭ ብለው ጊዜ በመውሰድ ይወያያሉ።

በባግራም የጦር ሰፈር የሰፈሩት የኤምሬትስ ልዩ ኃይል

የፎቶው ባለመብት, Frank Gardner

ምን ትፈልጋላችሁ? ወታደሮቹ ይጠይቃሉ። "መስጂድ፣ ትምህርት ቤት፣ ንፁህ ውሃ?" ትፈልጋላችሁ ይሏቸዋል።

ገንዘብም ያመጡና ለአካባቢው ኮንትራክተሮች በመስጠት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ያሰራሉ።

በወቅቱ የአረብ ኤምሬትስ አሻራ ከፍተኛ የማይባል ሊሆን ይችላል ነገር ግን ገንዘብና ሃይማኖትን በመጠቀም የአካባቢው ማህበረሰብ ኔቶ ላይ የነበረውን ጥርጣሬም ለመቀነስ ተጠቅመውበታል።

በሄልማንድ በመሳሰሉ የአፍጋኒስታን ግዛቶችም ከብሪታንያ ሃይሎች ጋር በመጣመር እልህ አስጨራሽ የሚባሉ ጦርነቶችን አካሂደዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ የመከላከያ ኃይል ዋና ፀሃፊ ጂም ማቲስ ኤምሬቶችን 'ትንንሾቹ ስፓርታ' ሲል ጠርተዋቸዋል። ይህም አገሪቷ ትንሽ ከመሆኗ አንፃር፤ የህዝብ ቁጥሯም አስር ሚሊዮን ባይሆንም እያደረሰች ያለቸውን ተፅእኖ ለመግለፅ ነበር።

አሸናፊ የሌለበት የየመን ጦርነት

በከፍተኛ ችግሮች የተሞላው የየመን የጦር ዘመቻ ቀጠለ። የሳዑዲ አረቢያው ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን በየመን የርስበርስ ጦርነት ላይ እጃቸውን ሲያስገቡ ኤምሬቶችም በ2015 ተቀላቀሉ።

ኤፍ-16 የተባሉ የጦር ጄቶችንም በመላክ የሁቲ አማፂያንን መደብደብ ጀመሩ። ወታደሮቿንም በደቡባዊ የመን አሰፈረች።

ከሁለት አመታት በፊትም በየመን ቁልፍ የምትባለውን የሶኮርታ ደሴት ላይ ጦሯን አሰፈረች። በዚህም አልተገታችም በኤርትራዋም አሰብ የጦር ሰፈር በመከራየት ጦሯን በቀይ ባህር ላይ አዘመተች። ይህም የሁዳይዳህን ወደብ ከሁቲዎች ለመንጠቅ ነበር።

የየመን ጦርነት ለስድስት አመታት ያህልም ቀጥሏል። አሸናፊ የሚባልም አካል የለም። ሁቲዎችም ቢሆን መዲናዋን ሰንዓን ጨምሮ በርካታ የአገሪቷ ግዛቲቷን እንደተቆጣጠሩ ነው።

የሶኮርታ ደሴ

የፎቶው ባለመብት, Frank Gardner

ኤምሬቶች ባደረሱት ጥቃትም የበርካታ ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል። በአንድ የሚሳይል ጥቃት አምሳ የመናውያንም መሞታቸውንም ተከትሎ ኤምሬቶች የሶስት ቀናት ኃዘን አውጀው ነበር።

ከአንዳንድ የአካባቢው ታጣቂዎች ጋር ባላቸው ግንኙነትም የኤምሬቶች ስም ጠልሽቷል። ታጣቂዎቹ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ናቸው።

ለሞት በሚያደርስ ሙቀት በመጋዘንም ውስጥ በርካታ እስረኞችን በማጎርም በርካታ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይወቅሷታል አረብ ኤምሬትስን

እስራኤል- አዲሱ ጥምረት

በየመን ያላትን ተሳትፎ ብትቀንስም በቀጠናው ላይ ያላትን ተፅእኖ ለመጨመር አወዛጋቢ በሚባል ሁኔታ ከቱርክ ጋር ፉክክር ላይ ናት።

ቱርክ በሶማሊያዋ መዲና ሞቃዲሾ ተሰማርታ የምትገኝ ስትሆን ኤምሬትስ በበኩሏ ሶማሊላንድን ትደግፋለች እንዲሁም በበርበራና ወደብና በኤደን ገልፍም የጦር ሰፈር አቋቁማለች።

በጦርነት በተጎሳቆለችው ሊቢያም ኤምሬቶች የሩሲያና ግብፅን ጦር ጋር በመሆን የምስራቁን ካሊፋ ሃፍጣርን ኃይልን እየደገፉ ሲሆን በሌላኛው ጎራ ደግሞ የምዕራቡን ጎን ደግሞ በቱርክ፣ ኳታርና ሌሎች ኃይሎች በመደገፍ ተሰልፈዋል።

መስከረም ወር ላይም ግሪክን ለማገዝ ወደ ክሬት ደሴት ተዋጊ ጄቶችን የላከች ሲሆን ይህም በምስራቅ ሜድትራንያን ነዳጅ የማውጣት መብት ጋር በተያያዘ ከቱርክ ጋር በመጋተራቸው ነው።

ከዚህ ሌላ ባልተጠበቀ ሁኔታም ከእስራኤል ጋር ስምምነት ፈፅማለች። ለአመታትም በሚስጥራዊ ሁኔታ ሲያካሂዱት የነበረውን ጥምረትም ይፋ አድርገውታል። እንደ ሳዑዲ አረቢያ ኤምሬት ብትሆን እስራኤል ሰራሽ የደህንነት መሳሪያዎችን በመጠቀም ዜጎቿን ትሰልል ነበር።

የአሁኑ ጥምረት የጤና፣ ባዮ ቴክኖሎጂ፣ ባህላዊና የንግድ ሽርኮች በተጨማሪ የጦርና የደህንነት ግንኙነታቸውንም በበለጠ ያጠናክራሉ ተብሎም ይታሰባል።

የሁለቱም አገራት ጠላት የሆነችው ኢራን የእስራኤልና የኤምሬቶችን ስምምነት አውግዛለች። ኢራን ብቻ አይደለችም፣ ቱርክ እንዲሁም ፍልስጥኤማውያን ቢሆኑም አውግዘውታል። ፍልስጥኤም ራሷን የቻለች ግዛት ለመሆን የምታደርገውን ትግል ያጨለመና ኤምሬትም ፍልስጥኤማውያንን ክዳለች ተብሏል።

ሮኬት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአቡዳቢ ፍላጎት በዚህ አይገታም። በአሜሪካ እርዳታም መንኮራኩር በማምጠቅና ወደ ማርስ በመላክ የመጀመሪያዋ አረብ አገር ሆናለች።

200 ሚሊዮን ዶላር በወጣበትና ተስፋ ተብሎ በተሰየመው የመንኮራኩር የማምጠቅ ጉዞም የተነሳው ከጃፓን ደሴት ነው።

በጠፈርም ላይ 126 ሺህ ኪሎሜትር በሰዓት ይጓዛልም ተብሏል።

495 ሚሊዮን ኪሎሜትር ርቀት ያለውን መዳረሻዋም የካቲት አካባቢ ትደርሳለች ተብሏል።

የሰው አልባ መንኩራኮሯ ተልዕኮ የማርስን ምህዋር በመሾር የአየር ንብረትና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ለቃቅሞ ወደ ምድር ማቀበል ነው።

በአለም አቀፉ ላይ ስፍራ እንዲኖረን እንፈልጋለን ያሉት የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ጋርጋሽ ናቸው።

"የትኞቹንም ጋሬጣዎች ማለፍ እንፈልጋለን። ለዚህም ቁልፍ የሚባሉ አካሄዶችን በመከተል እንሻገራቸዋለን" ብለዋል።