ስነ ፅሁፍ፡ "የአንዳንድ ቋንቋዎች የበላይነት ባህልን እያጠፋ ነው" ኬንያዊው ደራሲ ጉጊ

የፎቶው ባለመብት, Massimiliano Donati/Awakening
ኬንያዊው ስመ ጥር ደራሲ፣ የተውኔት ፀሃፊ፣ አቀንቃኝ፣ ጉጊ ዋ ቲያንጎ አፍሪካውያንም ሆነ የደቡቡ አለም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሊናገሩ እንዲሁም ሊፅፉ ይገባል በማለት ይታወቃሉ።
በቅኝ ግዛት አማካኝነት የተስፋፋፉት የአውሮፓውያን ቋንቋዎች በተለይም የእንግሊዝኛ ቋንቋ በአለም ላይ ያለውን የበላይነት በማስመልከትም በርካታ ፅሁፎችን አበርክተዋል። ከነዚህም መካከል 'ዲኮሎናይዚንግ ዘ ማይንድ ይገኝበታል።
ከሰሞኑም የአለም አቀፍ የስነ ፅሁፍ ሽልማት በሚቀበሉበት ወቅት በኪኪዩ ቋንቋ በመናገር በርካቶችን አስደምመዋል፤ መነጋገሪያም ሆነዋል።
ሽልማቱ ካታሎን የአለም አቀፍ ሽልማት ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን በወቅቱም የካታላን መንግሥት ባለስልጣናትም የተገኙበት ነው።
ሽልማቱ ለአለም ህዝብ በጎ ነገርን ላበረከቱ የሚሰጥና ከፍተኛ ስፍራ ያለውም ሲሆን ከዚህ ቀደምም ለፀረ- አፓርታይድ ታጋዩ ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ፣ የመብት ታጋይዋ ማላላ ዩስፋዚ ጃፓናዊው ፀሐፊ ሃሩኪ ሙራካሚ፣ ፈላስፋው ካርል ፖፐር ይገኙበታል።
ሽልማቱንም ለእናታቸው ማስታወሻ ይሁንልኝ ብለዋል ፀሃፊው
አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ ቢወጡም በቋንቋ፣ ባህልና በሌሎች መልኩ ማስቀጠላቸውንም በመተቸት "የቅኝ ገዥዎችን ቋንቋ ሊተው ይገባል በማለትም ለስድስት አስርት አመታት የታገሉት ጉጊ እርሳቸውም የሚፅፉት በኪኩዩ ቋንቋ ነው።
"በቋንቋዎች እኩልነት አምናለሁ፤ የተናጋሪው ቁጥር አይወስነውም። አምስት ሰዎች እንኳን ቢናገሩትም ከየትኛውም ቋንቋ አያንስም፤ በራሱ ምሉዕ ነው" በማለት ጉጊ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን ፈተና እየሆነ ያለው ጉዳይ ከሆነ ማህበረሰብ የሚመጡ ሰዎች ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በራሳቸው ቋንቋ እያወሩ የቋንቋ የበላይነት እንደሌለ ያስባሉ። የነሱ ቋንቋ በሌሎች ማህበረሰቦች እንዲሁ መነገሩ የበላይነት መሆኑን ታሪካዊ አመጣጡን አይረዱትም ብለዋል።
ፀሐፊው አክለውም የአንዳንድ ቋንቋዎች የበላይነት ባህልን እያጠፋ ነው ለመግባባትም እክል መሆኑንም አስረድተዋል።
"አንድ ቋንቋ ብቻ መሆን የባህል ካርቦንዳይኦክሳይድ ሲሆን የብዝኃ ቋንቋነት ደግሞ የባህል ኦክስጅን ነው" ብለዋል።
የ82 አመቱ ኬንያዊ ፀሃፊ በርካታ ድርሰቶችንና የተውኔት ፅሁፎችን የፃፉ ሲሆን ከነዚህም መካከል 'ዘ ሪቨር ቢትዊን'፣ 'ዊፕ ኖት ቻይልድ'፣ 'ኤ ግሬይን ኦፍ ዊት' የተወሰኑት ናቸው።
ከስራዎቻቸውም ጋር በተያያዘ ለበርካታ አመታት ለእስርና ለግዞት ተዳርገዋል። በአሁኑ ወቅት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ እያስተማሩም ይገኛሉ።












