የተዘረፉ የአፍሪካ ቅርሶችን ከፓሪስ ሙዝየም ለመውሰድ የሞከረው ተሟጋች ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት ወቅት የዘረፈቻቸው የአፍሪካ ቅርሶች ፓሪስ ሙዝየም ውስጥ ሊቀመጡ አይገባም በሚል ከሙዝየሙ ሊወስድ የሞከረው ተሟጋች የገንዘብ ቅጣት ተጣለበት።
ኤመሪ ምዋዙሉ ዲያባንዛ ፈረንሳይ ከቻድ የዘረፈችውን የቀብር ስነ ስርዓት ማስፈፀሚያ ቅርስ በፖሪስ በሚገኘው ብራንሊ ሙዝየም ውስጥም በጭራሽ ሊቀመጥ አይገባም በሚልም ተቃውሞም ነው ቅርሱን ከተቀመጠበት ቦታ ለመውሰድ የሞከረው።
ኤመሪ "የተዘረፉ የአፍሪካ ቅርሶችንና ንብረቶችን ላስመልስ ነው የመጣሁት" በማለት በቪዲዮ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ለዚህ ተግባሩ አንድ ሺህ ዩሮ ቅጣት ተጥሎበታል።
በዝርፊያ ወንጀል ቅጣት የጣለበት ፍርድ ቤት ዳኛም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባር እንዳይፈፅሙ ለመከላከል ነው ብለዋል።
"ፖለቲከኞችንም ሆነ ህዝቡን የቅኝ ግዛት ዘረፋን ጉዳይ ለማስታወስ ሌላ መንገድ መጠቀም ይቻል ነበር" ብለውታል ዳኛው።
ከኤመሪ በተጨማሪ ሶስት ተሟጋቾችም እንዲሁም 250፣750ና 1 ሺህ ዩሮ ቅጣት እንደተጣለባቸው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል።
ተሟጋቾቹ ቅርሱን ከቦታው አንስተው ወደሚገባው አገሩ እንወስደዋለን በማለት ይዘው ሲሄዱ የሙዝየሙ ጥበቃዎች ከበር እንዳይወጡ ሲከለክሏቸውም በዩቲዩብ የወጣው ቪዲዮ ያሳያል።
የኮንጎ ዜግነት ያለው ኤመሪ ከዚህ ቀደምም በሌሎች የፈረንሳይ ከተሞች እንዲሁም በኔዘርላንድስ ተመሳሳይ ተግባርም ፈፅሞ ነበር።
"ከአፍሪካ የተዘረፉና የኛ የሆኑ ቅርሶችን በዚህ ሙዝየም ለማየት ገንዘብ መክፈል ትክክል አይደለም። እነዚህ ቅርሶች መቀመጥ ያለባቸው በአገራቸው ነው" በማለት በባለፈው ወር ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግሯል።
ኳይ ብራንሊ ሙዝየምንም "የተዘረፉ ቅርሶችን ያከማቸ ሙዝየም" ነው በማለት ኤመሪ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, YouTube
ከሁለት አመታት በፊት በፕሬዚዳንት ማክሮን የተቋቋመው አንድ ኮሚቴም ሪፖርት ባደረገው መሰረት 90 ሺህ የሚጠጉ ቅርሶች ከአፍሪካ ተዘርፈው በፈረንሳይ እንደሚገኙ ገልጿል።
በባለፈው ሳምንት የፈረንሳይ ምክር ቤት ከቤኒንና ሴኔጋል የተዘረፉና በፓሪስ ሙዝየሞች ውስጥ ከሚገኙት ቅርሶች መካከል የተወሰኑት እንዲመለሱ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።
ከአፍሪካ የዘረፈቻቸውን ቅርሶች እንድትመልስ ተቃውሞ እየቀረበባት ያለው ፈረንሳይ ብቻ ሳትሆን በእንግሊዝም እንዲሁ ተመሳሳይ ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው።
የ33 አመቱ ኢዛያህ ኦጉንደሌም በለንደን ከባርነት ጋር የተያያዙ ቅርሶችን የያዘው ሙዝየም ውስጥ በርካታ ቅርሶችን ወርውሯቸዋል ተብሏል። በሌለበትም ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል ተብሏል።












