ቅርሶች ፡ የተዘረፉ ቅርሶች ሊመለሱ ይገባል ብሎ የተቃወመው የኮንጎ ተሟጋች በፈረንሳይ ፍርድ ቤት ቀረበ

የፈረንሳዩ ሙዝየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት ወቅት የዘረፈቻቻቸውን ቅርሶች ልትመልስ ይገባል በማለት በፈረንሳዩ ሙዝየም ተቃውሞ ሲያሰማ የነበረ የኮንጎው ተሟጋች ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ከእርሱ በተጨማሪ እንዲሁ አራት ተሟጋቾችም በመዲናዋ ፓሪስ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት በተጨማሪ መቅረባቸው ተዘግቧል።

ኤምሪ ምዋዙሉ ዲያባንዛና አራቱ ተሟጋቾች ቅርሶቹን ሊሰርቁ ሞክረዋል በሚልም ውንጀላ ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት። ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም የአስር አመት እስራትና 176 ሺህ ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ክስተቱ የተፈጠረው ሰኔ ወር ላይ ሲሆን የአርባ አንድ ዓመቱ ተሟጋች ኳይ ብራንሊ በሚባለው ሙዝየም ውስጥ ገብቶ ከቻድ የተዘረፈ የሥርዓተ ቀብር ማስፈፀሚያ ቅርስ አንስቶ በህንፃው ውስጥ ማሳየት ጀመረ።

ቅርሱ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ወቅት የተገመተ ሲሆን ከቻድም በቅኝ ግዛት ተዘርፎ የተወሰደ ነው።

ከዚያም በመቀጠልም በሌሎች ሙዝየሞችም እንዲሁ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ፈፅሟል ተብሏል።

ቫይስ መፅሄት ተሟጋቹን "እውነተኛ ኪሊሞንገር" ብሎታል። ኪሊሞንገር በብላክ ፓንተር ፊልም አንድ ገፀ ባህርይ ሲሆን ከአፍሪካ የተዘረፉ ሃብቶች በአውሮፓ ሙዝየም መከማቸት አጥብቆ የሚቃወም ነው።

ሆኖም የፈረንሳይ ባለስልጣናት ድርጊቱን አውግዘውታል።

"ቅርሶችን የመመለስ ጉዳይ ንግግርና ክርክር የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው" በማለት የሙዝየሙ ዳይሬክተር ኢማኑኤል ካሳርሄሩ መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።