"የቻይናን ኃያልነት ለመግታት ረፍዷል"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻይና መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር የሚታወቀው አርቲስትና የፊልም ባለሙያ አይ ዌይዌይ ቻይና በአለም አቀፉ ያላት ኃያልነት ከፍተኛ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት መግታት አይቻልም ብሏል።
"የምዕራቡ አለም ስለ ቻይና መጨነቅ የነበረበት ከአስርት አመታት በፊት ነበር። በአሁኑ ሰዓትም ግን ረፍዷል። ምክንያቱም ምዕራባውያን ከቻይና ጋር ጠንካራ ስርአት ዘርግተዋል ዝም ብለው ቢያቋርጡትም በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳሉ። ለዚያም ነው ቻይና የእብሪተኛ ባህርይ የምታሳየው" ብሏል።
በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክስ የወፍ ጎጆ ስታዲየምን ዲዛይን ያደረገው አርቲስቱ የቻይናን መንግሥት መተቸቱንም ተከትሎ ነው ከባለስልጣናቱ ጋር ችግሮች መፈጠር የጀመሩት።
በ2015ም ቻይናን ለቆ በበርሊን ኑሮውን አድርጎም ነበር። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ መኖሪያውን ካምብሪጅ አድርጓል።
አይ ዌይዌይ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት ቻይና ያላትን የምጣኔ ኃብት ኃያልነት ለፖለቲካዋ ተፅእኖም ትጠቀምበታለች።
በቅርብ አመታት የቻይና የፖለቲካ ተፅእኖ በጉልህ መታየት ጀምሯል።
እየጨመረ የመጣው ተፅእኖ
ከአስር አመታት በፊት የነበረችው ቻይና ልታይ ልታይ የማትልና፣ ድምጿም በአለም ጎልቶ አይሰማም ነበር።
የመንግሥት ባለስልጣናቷም ይዘውት የነበረው መፈክርም "ብርሃንን ደብቆ ጊዜን መግዛት" የሚል ነበር።
በርካታ ሚኒስትሮቿም ቻይና አሁንም ቢሆን ታዳጊ አገር ናት ከምዕራቡ አለምም ብዙ መማርን ትሻለች ሲሉም ይሰሙ ነበር።
ሆኖም የዢ ሺንፒንግ ወደ ስልጣን መምጣት ቻይና በአለም ታሳየው የነበረውን ባህርይ ሙሉ በሙሉ ቀየረው።
በ2012 ዢ ሺንፒንግ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ሆኑ፣ በቀጣዩ አመት ፕሬዚዳንት
ዢ ሺንፒንግ ቻይና በአለም ላይ ያላትን ቦታም ሆነ ገፅታ በአዲስ መልክ ያዋቀሩ ናቸው ይባልላቸዋል።
የአገሪቷም መፈክር "ለስኬት እንስራ" በሚል ተተካ።
በሆነ መንገድ ቻይና አሁንም ቢሆን ታዳጊ አገር ናት ምክንያቱ 250 ሚሊዮን ህዝቦቿ ከድህነት ወለል በታች ስለሚገኙ።
በአለም ላይ ሁለተኛ ታላቅ የምጣኔ ኃብት ባለቤት ናት። በአሁኑም ወቅት አሜሪካን የምትገዳደራትና በቀጣዩ አመታትም ትቀድማታለችም ተብሎ የምትጠበቅም ሃገር ናት፣ ቻይና።
ቻይና በአለም ላይ ያላት ተፅእኖ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ እየታየ ነው። በተቃራኒው ኃያሏ አገር አሜሪካም በሚታይ መልኩ ተፅእኖዋ እያሽቆለቆለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና በፖለቲካው ላይ ያላት ተፅእኖና ጫና በመላው አለምም እየተንሰራፋ ነው። ከጫፍ ጫፍ በሚባል ሁኔታ ከግሪላንድ፣ ካሪቢያን ደሴቶች፣ ፔሩ፣ አርጀንቲና፣ ፓኪስታን፣ ሞንጎሊያ የቻይና እጅ የሌለበት የለም።
በቅርቡም የካሪቢያኗ ባርቤዶስ ደሴት የእንግሊዟን ንግሥት በርዕሰ ብሄርነት አንፈልጋቸውም ማለቷን ተከትሎ የእንግሊዙ የፓርላመንት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ቻይና ናት ሃሳቡን ያመጣችው በማለት ወቅሰዋታል።
ቻይና በአለም ላይ ያላት ተፅእኖ በዚህ ተመለስ የሚባል አይደለም፤ በብሄራዊ ፍላጎቷ የሚመጣንም አገር ዝም ብላ አታልፈውም።
የቲቤት መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማ በቅርቡ ለንደንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ የእንግሊዝና የቻይና ግንኙነት በተወሰነ መልኩ ሻክሮ ነበር።
በቅርቡም የቼክ ሪፐብሊክ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ፣ ከፍተኛ ዲፕሎማት አስጠንቅቀዋል። ግልፅ በሆነ መልኩ ቻይናን ለመተንኮስም ሆነ ከጀርባቸው ሆነው የሚያሴሩ የፀረ- ቻይና ኃይሎችን አገራቸው እንደማትታገስና የሚከተለው ነገር ክፉ ይሆናል ብለዋል።
የቻይናና የሌሎች አገራት ፍጥጫ
ምንም እንኳን አንዳንዶች ቻይና ያላትን ምጣኔ ኃብት በመጠቀም ከፍተኛ ተፅእኖም ታሳርፋለች ቢሉም ተናጋሪውና ተፅእኖ ፈጣሪው የቻይና ግሎባል ታይምስ ጋዜጣ አዘጋጅ ሁ ሺን አይስማማም።
ቻይና አገራትን እያብረከረከች ነው የሚለውም ተቀባይነት የለውምም ይላል።
"አንድ መጠየቅ የምፈልገው ነገር ቢኖር ቻይና መቼ ነው አንድን አገር ያለ ፈቃዷ ምንም ነገር ለማድረግ ግፊት ወይም ጫና ያደረገችው?። በአለም ላይ አሁንም ቢሆን አሜሪካ ናት እቀባ በተለይም ኢኮኖሚያዊ እቀባ በመጣል ከፍተኛ ጫና ለማሳረፍ እየሞከረች ያለችው። ቻይና የትኛዋ አገር ላይ ነው ማዕቀብ የጣለችው?" በማለትም ይጠይቃል።
አክሎም "ማዕቀብ ጥለን እናውቃለን። እንደ ሃገር አንዳንድ የማንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ስሜታችንን እናፀባርቃለን ይህም ብዙ ጊዜ የሚፈጠረው የአገራችን ብሄራዊ ጥቅም ሲነካ ነው" ይላል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት ቻይና ከታይዋን አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ካናዳና ህንድ በሆነ መልኩ ተፋጣለች።
በተለይም ከህንድ ጋር በድንበር ከተማዋ ስከርሚሽ ጋር በተያያዘ መሳሪያም ተማዘዋል። ከእንግሊዝና ከአሜሪካም ጋር ያለው መፋጠጥም እንደቀጠለ ነው።
በግሎባል ታይምስ ላይ ያሉት ርዕሰ አንቀፆች የማኦ ዜዶንግን አገዛዝም ያስታውሳሉ ይባላል።
በቅርቡ ርዕሰ አንቀፁ ላይ አውስትራሊያን አስመልክቶም "ከቻይና ጫማ ስር ያለች ማስቲካ" በሚልም አንድ ፅሁፍ አውጥቷል።
አዘጋጁም አውስትራሊያ በተደጋጋሚ በቻይና ላይ ለምታደርገው ጥቃት ምላሽ ነው ብሏል።
"አሁንም ቢሆን የሚሰማኝ በጫማዬ ላይ የተለጠፈች ማስቲካ ነው እንደሆነች ነው። ላራግፈው የማልችል ነገር ግን መጣበቁ ደስ የማይል ስሜት ነው የሚሰማኝ። ይህንን እንደ አገላለፅ ነው የተጠቀምኩበት፤ ይህንን ደግሞ እንደ አስተያየት መስጠት መብቴ ነው" ብሏል።
ለአዘጋጁ በዋናነት የቻይና ፍጥጫ ከአሜሪካ ጋር ነው። በመጪው ህዳር የሚደረገው የአሜሪካ ምርጫን ለማሸነፍ በሚልም ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው ይላል።
መጪው ምርጫም አሜሪካ ከቻይና ጋር ሊኖራት የሚችለውን ግንኙነት የሚወስን ይሆናል።
ሆነም ቀረም በአለም ላይ ኃያሏንና ታላቋን አገር ቻይና አሜሪካም ሆነ ሌሎች አገራት በጠላትነት ሊመለከቷት አይገባም።
አይ ዌይዌይ እንዳለው ለምዕራቡ አለምም ሆነ በአለም ላይ ቻይና ያላትን ተፅእኖ ለመግታት ጊዜው ረፍዷል።












