ሕንድ ከቻይና ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በወታደራዊ ኃይል እጠብቃለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሕንድ እና የቻይና ወታደሮች ሰኞ ዕለት መጋጨታቸውን ተከትሎ 20 ሕንዳውያን ወታደሮች ተገድለዋል። ሕንድም አስፈላጊ ከሆነ ድንበሬን በወታደራዊ ኃይል እከላከላለሁ ብላለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ እንዳሉት፤ አንድም የውጪ ወታደር ወደ አገራቸው አልገባም። ከድንበር ወሰናቸው የተወሰደ መሬት እንደሌለም ተናግረዋል።
በቻይና እና በሕንድ የሄማልያ ድንበር ላይ በተከሰተው ግጭት ምን ያህል ወታደሮቿ እንደሞቱ ቻይና አልተናገረችም።
አገራቱ ድንበር በመጣስ ጸብ በማጫር አንዳቸው ሌላቸውን ይከሳሉ።
ከቀናት በፊት ላዳክህ በሚባለው ግዛት በሚገኘው ጋልዋን ወንዝ አቅራቢያ ነበር የቻይና እና ሕንድ ወታደሮች የተጋጩት።
ጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ እንዳሉት በሁለቱም ወገን ጉዳት ደርሷል።
“የሕንድ ኃይሎች ድንበር ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስተር ሞዲ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው።
ቻይና በወሰደችው እርምጃ መላው ሕንድ ተቆጥቷል ሲሉም ተደምጠዋል። “ሕንድ ሰላምና ወዳጅነት ትፈልጋለች፤ ነገር ግን ለሉአላዊነቷ ቅድሚያ ትሰጣለች” ብለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 1996 ላይ በተደረሰነ ስምምነት መሠረት በአካባቢው የጦር መሣሪያም ሆነ ፈንጂ መጠቀም አይቻልም። የሰኞ ዕለት በተከሰተው እና 20 የሕንድ ወታደሮችን ህይወታቸውን ባጡበት ግጭትም አንድም ጥይት አልተተኮሰም ነበር። በግጭቱ ወደ 76 የሕንድ ወታደሮች መጎዳታቸውም ተዘግቧል።
በዚህም ምክንያት ሐሙስ የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት በሁለቱ አገራት ወታደሮች መካከል በነበረው ግጭት ላይ ሚስማር የተበየደባቸው የብረት ዘንጎች ወቅት ጥቅም ላይ ውለው ጉዳቱን አድርሰዋል።

በሕንድ እና በቻይና ድንበር ያሉ የሕንድ ከፍተኛ የጦር ኃላፊ ለቢቢሲ የብረት ዘንጎቹን የሚያሳይ ፎቶ ሰጥተዋል። ዘንጉን የተጠቀሙበት የቻይና ወታደሮች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የእነዚህ መሣሪያዎች ፎቶግራፍ በሕንድ በትዊተር መሰራጨቱን ተከትሎ ሕዝቡ ተቆጥቷል። የቻይናም ይሁን የሕንድ ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ ያሉት ነገር የለም።
መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ ወታደሮቹ የተጋጩት 4,300 ሜትር ከፍታ ላይ ስለነበር ጋልዊን ወንዝ ውስጥ የገቡ ወታደሮች አሉ።
በአካባቢው ለምን መሣሪያ ተከለከለ?
ጋልዊን ወንዝ የሚገኘው በላዳካህ ተራራማ አካባቢ ሲሆን፤ የአየር ሁኔታው አስቸጋሪ ነው። አካባቢው ሁለቱም አገራት የእኔ ነው በሚሉት አክሲ ቺን አቅራቢያ የሚገኝ ወንዝ ነው።
በአካባቢው መሣሪያ ቢታገድም፤ ሕንድ እና ቻይና ከተለመደው የሽጉጥና ፈንጂ መሣሪያ ውጪ በመጠቀም ሲጋጩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ለመጨረሻ ጊዜ የተጋጩት በ1975 አራት ሕንዳውያን ወታደሮች ሲገደሉ ነበር። 1966 ላይ ሁለቱም አገሮች መሣሪያ ላለመማዘዝ ተስማምተዋል።
“በድንበሩ በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ጦር መሳሪያ ወይም በፈንጂ ተጠቅሞ ጥቃት ማድረስ ወይም እንስሳት ማደንም አይቻልም” ሲሉም ተፈራርመዋል።
ነገር ግን የድንበር አካባቢው በውጥረት የተሞላ ነው። ግንቦት ላይ የቻይና እና ሕንድ ወታደሮች ተደባድበው ነበር።
ሕንድ፤ ቻይና በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ድንበር ላይ አሰማርታች፣ 38 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይዛለች ስትል ትከሳለች።
ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ሁለቱን አገራት ለማሸማገል የተደረገው ጥረት አልተሳካም።












