ከባድ የጤና ችግር ኖሮባቸው ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, Bryony Hopkins
'ከባድ የጤና እክል ቢኖርብኝም ከቫይረሱ አገግሜያለሁ'
ሌሎች አሳሳቢ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዝ በጣም አስፈሪ ነገር ሊሆንባቸው ይችላል። ምናልባትም ብዙዎች ስለዚህ ጉዳይ ሲያስቡ በጣም ሊጨነቁ ይችላሉ። ነገር ግን አስጊ የሚባል የጤና ሁኔታ ላይ ሆነው እንኳን ከቫይረስ እያገገሙ ያሉ ሰዎች አሉ።
ብርዮኒ ሆፕኪንስም በከባድ የጤና ችግር ውስጥ ሆነው ቫይረሱን ማሸነፍ ከቻሉት መካከል አንዷ ስትሆን ታሪኳን እንዲህ ትናገራለች።
አንድ ቀን በድንገት መተንፈስ ሲያቅተኝ ደረቴ አካባቢ ከባድ ጭንቀት ተሰማኝ። ምንም የተለየ ነገር እየሰራሁ አልነበረም፤ በቤቴ ውስጥ ደረጃ እየወጣሁ ነበር። ኮሮናቫይረስ ያዘኝ? ደረጃው እንዲህ ከባድ ነው? ሰውነቴ ምን ሆነ? ሳንባዬስ ምን ችግር ገጠመው? የሚሉ ጥያቄዎች ተመላለሱብኝ።
‘ክሮንስ ዲዚዝ’ የሚባል በሽታ ተጠቂ ነኝ። በሆዴ ውስጥ የሚገኘው የሥርዓተ ልመት እራሱን በራሱ ያጠቃል። በጣም ከባድ የጤና እክል እንደሆነ አውቃለው።
ይህንን በሽታ ለማከም በዋነኛነት ጥቅም ላይ የሚውለው ህክምና ‘ኢሚዩኖሰፕረሲቭ ቴራፒ’ የሚባል ሲሆን መድኃኒቱ በሰውነቴ ውስጥ ያለውን የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ ነው ሥራው።
ይሄ ደግሞ ለኢንፌክሽንና እንደ ኮሮናቫይረስ ላሉ የመተንፈሻ አካላትን ለሚያጠቁ በሽታዎች ተጋላጭ ያደርገኛል።
መጀመሪያ አካባቢ እንደ ትኩሳትና የድካም ስሜትን የመሳሰሉ የመጀመሪያዎቹ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ሲሰሙኝ ብዙም አላሳሰበኝም ነበር።
ምልክቶቹ እየተባባሱ ሲመጡ ግን ጭንቅላቴ በጣም በሚያስፈሩ ሀሳቦች መሞላት ጀመረ። ያነበብኳቸው አስፈሪ የሞት ዜናዎችና የሆስፒታል መጨናነቆች ትዝ አሉኝ።
ሆስፒታል መግባት ሊኖርብኝ ይሆን? የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ያስፈልገኝ ይሆን? በቫይረሱ ምክንያት ሕይወቴ ታልፍ ይሆን? እያልኩ ብዙ ተጨነኩኝ።
በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ሆስፒታል ሄዶ መመርመር የማይታሰብ ነው። ሆስፒታሎች በእጅጉ ተጨናንቀው ነበር። ነገር ግን አንድ ዶክተር በተቻለ መጠን እንድመረመርና ሁኔታዎች እየባሱ ከሄዱ ድንገተኛም ክፍል ቢሆን እንድሄድ ነገረኝ።
ነገር ግን ከስምንት ቀናት በኋላ ምልክቶቹ መቀነስ ጀመሩ። ከዚህ በፊት ባለብኝ የጤና እክል ምክንያት እንዲዳከሙም ተደርጎ የነበረው በሽታ የመከላከል አቅሜ ቫይረሱን ተዋግቶ አሸንፎታል።
ይሄ ታሪክ የእኔ ብቻ እንዳልሆነ አስባለሁ፤ በርካቶች ተጓዳኝ አስጊ የጤና እክሎች እያሉባቸው እንኳን ቫይረሱን ማሸነፍ ችለዋል።

"ምንም እንኳን ሁኔታው በጣም አስፈሪ ቢሆንም ጥሩ ጥሩውን እያሰብኩ አሳልፌዋለው።"

የፎቶው ባለመብት, Khadija
ከድጃ እንግሊዝ ሊድስ ውስጥ የምትኖር የ25 ዓመት ወጣት ናት። ‘ታይፕ 1’ የሚባለው የስኳር በሽታ ታማሚ ነች። ጣፊያዋ ኢንሱሊን የሚባለውን ንጥረ ነገር ማምረት ስላቆመ በዶክተሮች አማካይነት ነው ኢንሱሊን ለሰውነቷ የሚሰጠው።
"ልክ በቫይረሱ ከተያዙ የመሞት እድላቸው ከፍተኛ ከሆኑት ሰዎች መካከል መሆኔን ሳውቅ በጣም ነበር የፈራሁት። ኮሮናቫይረስ ሊይዘኝ ይችላል፤ ቢይዘኝስ ምን እሆናለሁ እያልኩ ብዙ እጨነቅ ነበር።"
በሆስፒታል ውስጥ በነርስነት ከምታገለግል ከእናቷ ጋር የምትኖረው ከድጃ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድሏ ከፍ ያለ ነበር። ከአራት ሳምንታት በፊትም አንዳንድ የቫይረሱን ምልክቶች ማሳየት ጀመረች።
የአጥንት መቆረጣጠም፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ደረት አካባቢ ከባድ ህመምና ትኩሳት ነበረባት።
"ልክ ምልክቶቹን ሳስተውል በጣም ፈራሁ፤ ምክንያቱም በዜና የምሰማው ሁሉ ሞት ብቻ ነበር። በቫይረሱ ተይዘው ስላገገሙ ሰዎች እምብዛም አይወራም ነበር። በጭንቅላቴ ቫይረሱ ተገኝቶበት ወደ ሆስፒታል የሄደ ሰው በሙሉ እንደሚሞት ነበር የማስበው።"
በመጀመሪያ የህክምና ባለሙያዎች ወደቤታችን ተልከው መጡ። ነገር ግን ወደ ሆስፒታል መሄድ እንደሌለብኝ ወስነው በቤት ለቤት ምርመራ እንደምካተት ነገሩኝ። ነገር ግን እሱም አልተሳካም።
በሚያስገርም ሁኔታ ከድጃ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተሻላት። ከቤት ባለመውጣቴም ደኅንነት ተሰምቶኛል ትላለች።

ከነባለቤቱ በበሽታው ተይዞ የዳነው ጆ

የፎቶው ባለመብት, Joe Dunster
ጆ ጀስትነር ደግሞ ‘ኒፍሮቲክ ሲንድረም’ የሚባል የኩላሊት ችግር አለበት። በፈረንጆቹ 2000 ላይ የኩላሊት ንቀለ ተከላ እስከማካሄድም አድርሶታል ይሄው በሽታ።
"ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ሰዎች ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን ስሰማ እራሴን መከላከል እንዳለብኝ ተሰማኝ። ወደቤት ገባሁና እራሴን ከሰዎች ንክኪ አራቅኩኝ" ይላል።
ነገር ግን እራሱን ከሰዎች ቢለይም የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ግን ማሳየቱ አልቀረም። ምናልባትም በሽታው ከህክምና ባለሙያ ባለቤቱ ሳይዘው እንዳልቀረ ይገምታል። እሷም አንዳንድ ምልክቶችን ማሳየት ጀምራ ነበር።
"ሁለታችንም ደረታችን አካባቢ መታፈን ይሰማን ነበር። ምናልባት ጭንቀቱ ሊሆን ይችላል ብለን ነበር። ነገር ግን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደረቅ ሳል ማሳል ጀመርኩ።"
ጆ ትንሽ ቆይቶ ትኩሳትና ሌሎች የኮሮረናቫይረስ ምልክቶችን ለማሳየት ጊዜ አልፈጀበትም።
"ለሚቀጥሉት ቀናት ጤናዬ ተቃወሰ፤ ማሳልና ማስነጠሱም እስከ አስረኛው ቀን ድረስ አልተወኝም ነበር።
ቀስ በቀስ ግን እሱ እና ባለቤቱ የጤና ሁኔታቸው እየተስተካከለ መጣ። ሌላው ቀርቶ አስጊ የጤና ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች እንኳን በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ቀላል የሚባሉ ምልክቶችን ብቻ አሳይተው መዳን እንደሚችሉ ተገነዘብኩ ይላል ጆ።














