ሕንድ የቻይና ምርቶች ላይ ማዕቀብ መጣል ያዋጣታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት በሥርዓት ባልተማከለው አወዛጋቢ ድንበራቸው ኃያላኑ ቻይናና ሕንድ ተጋጭተዋል። 3500 ኪሎሜትር ርዝማኔ ባለውና በዓለም ረዥሙ በሚባለው ሁለቱ አገራት በሚጋሩት የሂማሊያ የተራራ ሰንሰለት፣ ጋልዋን ሸለቆም 20 የሕንድ ወታደሮች ተገድለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በሕንድ ፀረ- ቻይና ስሜቶች ዳብረዋል። በሕንድ ጎዳናዎች ላይ ቻይናን የሚያጣጥሉ መልዕክቶች እየተሰሙም ነው። በምዕራብ ህንዷ ግዛት አህመዳባድም ሆነ በመዲናዋ ደልሂ የሚገኙ ነጋዴዎችና ተቃዋሚዎች የቻይና ምርቶችንም አቃጥለዋል።
ተቃውሞው የተሰማው ከነዋሪው ብቻ አይደለም፤ ከሕንድ ባለስልጣናትም ጭምር ነው። አንደኛው ሚኒስትርም የቻይና ምግብም ወደሚሸጡ ሬስቶራንቶች ከመሄድ እንዲታቀቡ ለነዋሪው ጥሪ አድርገዋል። በሕንድ ውስጥ የቻይና ምግብ ተወዳጅ ነው።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንዲሁ በግሬደር ላይ ሆነው የቻይና ስልክ አምራች የሆነውን የኦፖን የተሰቀለ ቢልቦርድ ሲያጠቁሩ ታይተዋል። በዚህ ተቃውሞም የሚያስገርም ነገር የተፈጠረ ሲሆን የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ ጋር ተመሳስሎባቸው የኪምን ሞዴል ሃውልትም ሲያቃጥሉ ተቃዋሚዎች ታይተዋል።
የሕንድ መንግሥት ይፋዊ በሆነ ሁኔታ የቻይና ምርቶች ላይ ማዕቀብ ባይጥልም የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በአገሪቱ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች ውላቸው እንዳይራዘም መልዕክት ተላልፎላቸዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ በባቡር መንገድ ፕሮጀክት ተቋራጭነት ሲሰራ የቆየው የቻይና ኩባንያም ፈቃዱ ተሰርዟል። ከዚህም በተጨማሪ ከአገሪቱ የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በኤሌክትሮኒክስ ንግድ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችም የሚሸጧቸው ምርቶች ስሪታቸውን ማሳየት አለባቸው ተብሏል።
የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ታጣቂ የሆኑት ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር 15 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ግጭቱንም ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቁላልም ተብሏል።
ሕንድ ከቻይና ለሚገቡ ማንኛውም ምርቶች ተጨማሪ ታሪፍ እንዲሁም ሌሎች የግብር አይነቶችንም ልታስተዋውቅ አቅዳለች። ነገር ግን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንዲህ አይነት ማዕቀቦችን እጥላለሁ ማለት ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ከቻይና ውጭ ምን አማራጭ አለ?
ለሕንድ ከአሜሪካ በመቀጠል ቻይና የንግድ አጋሯና ሸሪኳ ናት።
ወደ አገሪቱ ከሚገቡ የኬሚካል፣ የመለዋወጫ ቁሳቁሶች፣ ኤሌክትሮኒክስና የህክምና መገልገያዎች ውስጥ አስራ ሁለት በመቶ የሚሆነው ከቻይና ነው።

የፎቶው ባለመብት, STR
"ለመድኃኒት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው የሚመጣው ከቻይና ነው" የሚሉት የሕንድ ፋርማሲዎች ጥምረት ፕሬዚዳንት ሱዳንርሻን ጄይን ናቸው
ምንም እንኳን ሕንድ በመድኃኒት ግብዓቶች ራስ የመቻል ፖሊሲ ብታውጅም ይህ ግን ረዥም ጊዜን እንደሚወስድ ሱዳንርሻን ይናገራሉ።
በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ ያለውም የተንቀሳቃሽ ስልኮች ኢንዱስትሪም በከፍተኛ ሁኔታ ርካሽ በሆኑት የቻይና ኦፖ ዛኦሚና በመሳሰሉት የስልክ አምራቾች ላይ ጥገኛ ነው። በአገሪቱ ውስጥ ባለውም የገበያ ሁኔታ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት እነኚሁ ስልኮች ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የኤሌክትሮኒክስ አምራቾችም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከቻይና ማስገባት ካልቻሉ ሽባ እንደሚሆኑም እያስጠነቀቁ ነው።
"ስላለቁ ምርቶች ብዙ አያስጨንቀንም። ነገር ግን በዓለም ላይ ቁልፍ የሚባሉ ግብዓቶችን የሚመጡት ከቻይና ነው" በማለት የውሃ ማቀዝቀዣ፣ የአየር ማጣሪያ የሚያመርተው ብሉ ስታር ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቢ ቲያጋርጃን ይናገራሉ።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም በአገር ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ግብአቶች አቅርቦትን ለመጨመር ጊዜ ይፈጃል ብለዋል።
ቻይናና ሕንድ የንግድ ሸሪክነታቸው በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በቅርብ ዓመታት ደግሞ ይሄው ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በሕንድ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥ አሊባባና ቴንሰንት የመሳሰሉ ኩባንያዎች በሕንድ ላሉ ዞማቶ፣ ፓይቲም፣ ቢግ ባስኬትና ኦላ ለተባሉ የቴክኖሎጂ ጀማሪዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የገንዘብ ልገሳ አድርገዋል።
እነዚህ የቻይና ትልልቅ ኩባንያዎች በሕንድ ማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሃብትና የቴክኖሎጂ ሥርዓትንም ሰብረው መግባት ችለዋል፤ የበላይም ለመሆን እየሰሩ እንደሆነም ጌትዌይ ሃውስ የተባለው የቦምቤይ ምርምር ቡድን አሳውቋል።
"በቻይና ኢንቨስትመንት አማካኝነት የተቋቋሙ 80 የሚሆኑ የሕንድ ጀማሪ ተቋማት አሉ አብዛኛዎቹም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ነው የተመሰረቱት። ከሰላሳዎቹ 18 የሚሆኑት የቴክኖሎጂ ጀማሪዎች አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ ሲሆን ከጀርባቸው የቻይና ኢንቨስተሮች አሉበት" ይላል በጌትዌይ ሃውስ ተንታኝ የሆነው አሚት ብሃንዳሪ።
ቻይና በሕንድ ያላት ከውጭ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 6.2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን በአንፃራዊነትም አነስተኛ የሚባል ነው።

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto
ነገር ግን አሚት እንደሚለው አሊባባን የመሳሰሉ ኩባንያዎች በሕንድ ላይ ያላቸው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ገበያውን በበላይነት እንዳይቆጣጠሩት ሊገቱ እንደሚገባም ያስረዳል።
ሕንድ ከውጭ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው ኢንቨስትመንት ፖሊሲዋንም በቅርቡ ያሻሸለች ሲሆን ይህም አገር በቀል ኩባንያዎቿን በቻይና እጅ ስር እንዳይወድቁ ለመላከልም ነው።
ይህንንም ተከትሎ ቻይና ሕንድ የዓለም ንግድ ድርጅት መርሆችን እየጣሰች ነው በማለት ወንጅላታለች። "ያለው ግጭት የንግድ መርሆችን ለመጣስ ምክንያት ከሆነ ውሳኔዎቹን ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ የለም" በማለት የህግ አማካሪ የሆኑት ዙልፊቀር ሜሞን ይናገራሉ።
ይህም ሁኔታ ሕንድ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች እንድትቀንስና በሯሷም እንድትቆም መንገድ ይጠርግላታል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ሕንድ ከቻይና ጋር በምታደርገው ንግድ 50 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ያልተወራረደ ገንዘብ ያለ ሲሆን በሁለቱ አገራት ቁርሾ ፈጥሮ ቆይቷል። ምናልባት በዚህ ወቅትም ይህንን ልዩነት ለማጥበብም መስራት እንዳለባትም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ራስን መቻል መልስ ይሆናል?
የሕንድ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከቻይና የሚመጣውን 25 በመቶ የምርት አቅርቦት ሊሸፍን እንደሚችል አኪዩት የተባለው ድርጅት ጥናት አመልክቷል። ይህም ማለት ሕንድ በዓመት 8 ቢሊዮን ዶላርን ታድናለች።
ለምሳሌ ሕንድ በዚህ ዓመት 431 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የእደ ጥበብ ሥራዎች ከቻይና አስገብታለች። ሆኖም ባሃንዳሪ እንደሚሉት ህንድ ከቻይና የምታስገባው ምርት ላይ ሙሉ በሙሉ ማዕቀብ መጣል እንደማትችል ነው። በሕንድ ታዋቂ የሆነውን የቻይናው ማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ቲክቶክ ላይ ማዕቀብ መጣሉ ሌሎችም አማራጮች ስላሉ አዋጭ ነው ይላሉ።
ሕንድ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ ማዕቀብ እጥላለሁ ብትል ከፍተኛ ጫና ምጣኔ ሃብቷ ላይ ያደርሳል፤ ወደ ድቀትም ሊመራት ይችላል።
ቻይና በበኩሏ ሕንድ ላይ ማዕቀብ ብትጥል ምንም አትጎዳም። ወደ ውጭ ከምትልከው ውስጥ የሕንድ ድርሻ ሶስት በመቶ ብቻ ስለሆነ ለቻይና ኢምንት ነው።
ለዚያም ነው ሕንድ ውስጥ ለሚታዩ ፀረ-ቻይና እንቅስቃሴዎች ምላሽ ያልሰጠችው። ከሰሞኑ የቻይናው ግሎባል ታይምስ ርዕሰ አንቀፅ ላይ "ግጭቶችን ከማጦዝ ይልቅ የምጣኔ ሃብት ማገገሙ ላይ ማተኮር ይሻላል" የሚል መልዕክት አስተላልፏል።













