ቻይና ሰራዊቷን 'በማርሻል አርትስ ላሰለጥን ነው' አለች

የቻይና ሰራዊት

የፎቶው ባለመብት, AFP

ቻይና ሰራዊቷን በቲቤት ኮረብታማዎቿ ቦታ የማርሻል አርት ልታሰለጥን መሆነኑን አስታውቃለች። ለዚህም 20 የሚሆኑ የማርሻል አርት አሰልጣኞችን መድባለች።

ስልጠናው ባሁኑ ሰዓት ለምን እንደተጀመረ ይፋዊ ምክንያት ባይሰጥም ባለፈው ከነበረው የቻይናና ህንድ የድንበር ግጭት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ግምቶች እየተሰጡ ነው።

3500 ኪሎሜትር ርዝማኔ ባለውና በዓለም ረዥሙ በሚባለው ሁለቱ አገራት በሚጋሩት የሂማሊያ የተራራ ሰንሰለት፣ ጋልዋን ሸለቆም 20 የሕንድ ወታደሮች ተገድለዋል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል በጎርጎሳውያኑ 1996 በተደረገው ስምምነት በአካባቢው የጦር መሳሪያ ወይም የሚቀጣጠሉ ነገሮች በድንበር አካባቢ መያዝ አይቻልም የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ ነበር።

ቻይና በግጭቱ ስለደረሰባት ጉዳት መረጃ ባትሰጥም ህንድ በበኩሏ በተጨማሪ 76 ወታደሮች እንደቆሰሉባት አስታውቃለች።

የቻይና ሰራዊት አባላት ማርሻል አርት ሊሰለጥኑ እንደሆነ የተነገረው ከሳምንት በፊት መሆኑንም የሆንግ ኮንግ ሚዲያ ዘግቧል።

የቻይና የመንግሥት ሚዲያ ሲሲቲቪ እንዳለው ከኢኖቦ ፋይት ክለብ የተውጣጡ 20 ተፋላሚዎች በቲቤት መዲና ላህሳ ላይ ሰራዊቱን ያሰለጥናሉ። በሁለቱ ሃገራት ድንበር ላይ ያሉ ሰራዊቶችን ያሰለጥናሉ ስለሚለው ጉዳይ ምንም አልተባለም።

የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ታጣቂ የሆኑት ሁለቱ አገራት በጋልዋን ሸለቆ በሚገኘው ላዳክሆን የተታኮሱት ሰኔ 8፣ 2012 ዓ.ም ነው። ግጭቱን የጀመረውን አካል ኃላፊነት በሚመለከት እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ።

በከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኘው ቦታ፣ የአየር ንብረቱ በረዷማ ሲሆን ሁለቱ ሃገራት በይገባኛል የሚበጣበጡበት ቢሆንም በቻይና ቁጥጥር ስር ነው የሚገኘው።

በቅርቡ በተደረገው ግጭት የሞቱት ወታደሮች ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ የተፈጠረ ነው ተብሏል።

ነገር ግን ባልተማከለው አወዛጋቢ ድንበራቸው ሁለቱ ሃገራት ከተፋጠጡ ዘመናትን አስቆጥረዋል።