ናሳ 'ታክሲ ተከራይቶ' ወደ ህዋ በመወንጨፍ አዲስ ታሪክ ሊያስመዘግብ ነው

መንኮራኩሯ

የፎቶው ባለመብት, SPACEX

የአሜሪካ የህዋ ሳይንስ ማዕከል ናሳ ከዚህ ቀደም መንኮራኮር ተከራይቶ አያውቅም። በራሱ መንኮራኮር ነበር የሚወነጨፈው ወይም የሚያስወነጭፈው።

በፈረንጆች 2011 የራሱን መንኮራኮር ጡረታ እንድትወጣ ካደረገ በኋላ ሌላ የተሻለ አማራጭ አግኝቷል።

መንኮራኮር መከራየት።

ስፔስ-ኤክስ የግል ንብረት ነው። ታክሲ ወደ ህዋ ይልካል፤ ሳተላይትን ወደ ምድር ምህዋር ያመጥቃል። አሁን ደግሞ ከናሳ ጋር ሽርክና ገብቶ ሳይንቲስቶችን ወደ ዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያና ወደ ህዋ ሊወስድ ጣጣውን ጨርሷል።

ስፔስ-ኤክስ የማን ነው?

ስፔስ-ኤክስ በ2002 ነው ሥራ የጀመረው። በርካታ ነገሮችን አሳክቷል። የሩቅ ዓላማው የሰው ልጅ በሌላ ፕላኔት መኖር እንዲችል ማድረግ ነው።

ፈጣሪው ኢሎን መስክ ነው። ኢሎን መስክ አስደናቂ ሰው ነው። ፔይ ፓል የተባለውን የክፍያ ዘዴን ከጀመሩት አንዱ ነው። ቴስላን ከመሰረቱት ሰዎችም መካከል ነው።

የሳይንስ ልቦለድ የፈጣራ ፊልሞች ፊልም ብቻ ሆነው መቅረት የለባቸውም ብሎ ያምናል። የሳይንስ ፈጠራ ፊልሞችን ልንኖራቸው፣ ልንፈጥራቸው ካልቻልንማ ቅዥቶች ሆኑ ማለት ነው ይላል።

አሁን ሁለት እውቅ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችን ጭና የምትሄደው እጅግ ዘመናዊ የህዋ ታክሲ በእርሱ ኩባንያ የተሰራች ናት።

ናሳ ለምን የህዋ ታክሲ ይከራያል?

ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው። መልሱ ምጣኔ ሀብታዊ ነው።

አንድ የህዋ ታክሲን (መንኮራኮር) ለመገንባት እጅግ ውድ ነው። ስፔስ-ኤክስ ግን አዲስ ፈጠራ ይዞ መጣ። የህዋ ታክሲዎች (መንኮራኮር) ለአንድ ጊዜ ብቻ ነበር የሚያገለግሉት፤ ለምን ደጋግሞ የሚያመላልስ የህዋ ታክሲ አንሰራም ብለው እነ ኤሎን መስክና ኩባንያው ስፔስ ኤክስ ተነሱ። አደረጉትም።

አንዳንዶች ይህ ለመልሶ አገልግሎት የሚዉል የህዋ ታክሲ መሰራቱና ናሳም ይህን መከራየቱ ቢያንስ ቢያንስ 40 ቢሊዮን ዶላር ወጪን ለናሳ አድኖለታል ይላሉ። ናሳ ይህን ብር ካተረፈ ባለ ታክሲው ስንት አግኝቶ ይሆን?

ዳግ ሄርሊና ቦብ ቤንከን የተባሉ ልምድ ጠገብ ሳይንቲስቶች ናቸው ለመጀመርያ ጊዜ ነገ በኪራይ መንኮራኮር ወደ ምህዋር (ኦርቢት) የሚመጥቁት።

በዚህ ጉዞ ወደ ህዋ የሚኣቀኑት ቦብና ዳግ ኮሮናቫይረስን ወደ ሕዋ ይዘው እንዳይሄዱ ተደጋጋሚ ምርመራና ክትትል ተደርጎላቸዋል።

የህዋ ሳይንስ ምርምርን እጅግ ርካሽ ያደርጋል የተባለው ይህ የስፔስ ኤክስ ፈጠራ አንድን መንኮራኮር በተደጋጋሚ መጠቀም ስለሚያስችል ነው።

ጠፈረተኞቹ ዳግ እና ቦብ

የፎቶው ባለመብት, NASA

የምስሉ መግለጫ, ጠፈረተኞቹ ዳግ እና ቦብ

ታሪክ ሊሰራ ነው

የናሳ ሳይንቲስቶቹ ዳግና ቦብ በሕዋ ሳይንስ ውስጥ አዲስ ታሪክ ነው የሚያስመዘግቡት። ሁለቱ አስትሮኖመሮች ወደ ህዋ ሳይንስ ጣቢያ የሚወነጨፉት ከፍሎሪዳ የመንኮራኮር ማስወንጨፊያ ጣቢያ ነው።

የሚሳፈሩባት የስፔስ ታክሲ (የመንኮራኮር ብልቃጥ) ነው ጉዞውን ታሪካዊ የሚያደርገው።

ናሳ በታሪኩ መንኮራኮር ከራሱ እንጂ ከሌላ ተቋም ተከራይቶ አያውቅም ነበር። መንኮራኮር ራሱ ሰርቶ ራሱ ይወነጨፍበት ነበር። ይህ ነገር በፈረንጆች 2011 ላይ የራሱን መንኮራኮር ጡረታ ሲያስወጣ አብቅቶለታል።

አሁን ሰፔስ-ኤክስ የተባለው ኩባንያ ነው የናሳን ሳይንቲስቶች ወደ ምህዋር አድርሶ የሚመልሰው።

ወደ ምድር ምህዋር የሚደረጉ የቅርብ ርቀት ጉዞዎችን ከእንግዲህ ናሳ በኪራይ ታክሲ እየከፈለ ነው የሚመላለሰው።

የዛሬው ጉዞ ስኬታማ ከሆነ ናሳ የራሱን ሮኬት ሰርቶ መጠቀምን ያቆማል ማለት ነው።

የናሳ አስተዳዳሪ ጂም ብራይደስቲን እንደተናገሩት ከእንግዲህ ቢያንስ የቅርብ የምድር ምህዋር ጉዞ የጥቂት ሳንቲስቶችና የናሳ ጉዳይ ሳይሆን የንግድ ጉዳይ ይሆናል።

ወደዚያ የሚወስዱንን ታክሲዎችም ከግል አጓጓዦች እንገዛለን። የሚያደርሱንን መንኮራኮሮች በዋጋ፣ በጥራታቸውና በሚሰጡን ዋስትናና ደኅንነት እንመዝናቸዋለን።

ስፔስ-ኤክስ የተሰኘው ኩባንያ በርካታ ሳተላይቶችን ወደ ሕዋ ያመላልሳል። መንኮራኮሩ የናሳ ሳይንቲስቶችን ዛሬ አሳፍሮ ሲሄድ ግን የመጀመርያው ነው የሚሆነው።

ዳግና ቦብ ከፍሎሪዳው የኬኔዲ ማስወንጨፊያ ማዕከል ነው ከምድር የሚነሱት።

ይህም በህዋ ምርምር ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ሆኖ ይመዘገባል።

ሁለቱ ሳይንቲስቶች በምድር ምህዋር ላይ ለስንት ቀን እንደሚቆዩ ይፋ አልተደረገም። ሆኖም ለ4 ወራት እዚያው በምድርን ከባቢ እየተሸከረከሩ ይቆያሉ ተብሎ ይጠበቃል።