ሕንድ፡ የዓለማችን 'ትልቁ' ቤተሰብ አባወራ ሞቱ

ቻና በዓለማችን ትልቁ ቤተሰብ አባወራ መሆናቸው ይታመናል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሕንድ የበርካቶች ወላጅ አባት እንደሆኑ የሚታመኑት የ76 ዓመቱ አዛውንት አረፉ።

አዛውንቱ በሕንድ ሞሚዞራም በምትባል ግዛት ነዋሪ የነበሩ ሲሆን እሁድ እለት መሞታቸው ተገልጿል።

ዚዮና ቻና የሚባሉት እኚህ አዛውንት በርካታ ሚስቶችን ማግባት የሚፈቅድ ሐይማኖት ተከታይ የነበሩ ሲሆን፤ 38 ሚስቶችን አግብተው፣ 89 ልጆችን እንዲሁም 36 የልጅ ልጆችን አፍርተው ነበር።

የአዛውንቱ መሞት በአካባቢው አስተዳዳሪ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ በትዊተር ሠሌዳቸውም ላይ በሞታቸው የተሰማቸውን ሐዘን አስፍረዋል።

አዛውንቱ የደም ግፊት እና ስኳር ሕመምተኛ እንደነበሩ ክትትል ሲያደርጉላቸው የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ገልፀዋል።

እንደ ሕክምና ባለሙያዎቹ ገለጻ ከሆነ አዛውንቱ በመኖሪያ ቤታቸው ሕመማቸው ጠንቶባቸው የቆዩ ሲሆን ወደ ሕክምና ተቋም እሁድ ምሽት ቢመጡም ወዲያውኑ ማረፋቸውን አስታውቀዋል።

ቻና በዓለማችን የትልቁ ቤተሰብ አባወራ ናቸው ቢባልም ሌሎች ሁለት ግለሰቦች በተመሳሳይ የትልቁ ቤተሰብ አባወራ የሚለው መጠሪያ እንደሚገባቸው ይናገራሉ።

የቻና ትክክለኛውን የቤተሰብ ቁጥር ለማወቅ አዳጋች መሆኑም በተጨማሪ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም አዛውንቱ ከ39 ሚስቶች 94 ልጆች መውለዳቸው እንዲሁም 33 የልጅ ልጆች እና አንድ የልጅ ልጅ ልጅ ማየታቸው ተዘግቦ ነበር።

ይህም ከእርሳቸው እና ከልጆቻቸው የሚወለዱትን እንዲሁም ሚስቶቻቸውን ጨምሮ 181 ሰዎች መድረሳቸውን ያሳያል።

በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የዜና አውታሮች አዛውንቱን የዓለማችን ትልቁ ቤተሰብ አባወራ እያሉ ቢጠራቸውም የዓለም ክብረወሰን ግን በማን እንደተያዘ ግልጽ የሆነ መረጃ የለም።

ቻና እና ቤተሰባቸው የአገር ጎብኚዎችን ትኩረት የሳቡ ሲሆን ወደ ሚኖሩበት መንደርም በርካታ ጎብኚዎች እንዲመጡ አድርጓል።

የቻና አስደናቂ ሕይወት የበርካታ መገናኛ ብዙሃን አብይ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ተዘግቦ ያውቃል።

ይህ በርካታ ቁጥር ያለው ቤተሰብ 100 ክፍል ባለው በባለ አራት ፎቅ ቤት ውስጥ በጋራ ይኖራል።

ሚስቶቻቸውም ቢሆኑም የቻና መኝታ ክፍል አቅራብያ በጋራ እንደሚኖሩ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይህ የአዛውንቱ እና የሚስቶቻቸው መኖሪያ የአገር ጎብኚዎችን ቀልብ የሳበ ጉዳይ ሆኖ የሚኖሩባትን መንደር በበርካታ ቱሪስቶች እግር እንዲረግጥ ሆኗል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ቻና የተወለዱት በ1945 ነው። በ17 ዓመታቸው በሦስት ዓመት የምትበልጣቸውን የመጀመሪያ ባለቤታቸውን አገቡ።

ቻና የሚከተሉት እምነት 2000 ተከታዮች ያሉት ሲሆን በአያታቸው በ1942 የተመሰረተ መሆኑ ይነገራል።

ይህ እርሳቸው የሚከተሉት እምነት ወንዶች ከአንድ በላይ ሚስት እንዲያገቡ ይፈቅዳል።