ዋትስአፕ የተጠቃሚዎች መልዕክት ምስጢራዊነትን በተመለከተ ዘመቻ ጀመረ

ዋትስአፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ግዙፉ የመልክት መላላኪያ መተግበሪያ ዋትስአፕ በተጠቃሚዎች የግል ሚስጥር አጠባበቅ ላይ የመጀመሪያ የሆነውን የማስታወቂያ ዘመቻ በአንግሊዝ ማካሄድ ጀምረ።

ተቋሙ ይህንን ማድረግ የጀመረው በቅርቡ ካደረገው የደንብ እና ግዴታዎች ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ከደንበኞቹ በገጠመው መጠነ ሰፊ ተቃውሞ በኋላ ነው።

ዋትስአፕ የእንግሊዝ መንግሥትን ጨምሮ ከተለያዩ መንግሥታት እየቀረበበት ላለው የመልዕክትቶችን ሚስጥራዊነት (ኢንክሪፕሽን) እንዲያላላ እየደረሰበት ያለውን ጫና እንደማይቀበልም ገልጿል።

የዋትስአፕ ኃላፊ ዊል ካትካርት "ባለሥልጣናት ያነሰ የደንበኞች መረጃ ደኅንነት እንዲኖር ከሚጠይቁ የበለጠ እንዲጠነክር መጠየቅ አለባቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የሰዎችን ደኅንነት በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጠንካራ የግል ምስጢር አጠባበቅ ሥርዓት ሲኖር ነው። መንግሥታትም ተቋማት ደካማ የደኅንነት ሥርዓት እንዲኖራቸው ማበረታታት የለባቸውም" ሲሉ ገልጸዋል።

"ተቋማት የደንበኞቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ የመጀመሪያው እርምጃ ጠንካራ ደኅንነት ጥበቃ እንዲኖር ማድረግ ሲሆን፤ እኛ መንግሥታት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ደካማ ደኅህንነት እንዲያቀርቡ ለማበረታታት መጣር የለባቸውም ብለን እናስባለን" ብለዋል።

"ይልቁኑስ ተቋማቱ በተቻለ መጠን ጠንካራ የደኅንነት ጥበቃ እንዲኖራቸው ማበረታት ብሎም ማስገደድም ጭምር አለባቸው" ሲሉ አክለዋል።

ዋትስአፕ የጀመረው ይህ ዘመቻ ከሰኞ ጀምሮ በአንግሊዝ እና በጀርመን መካሄድ ይጀምር እንጂ በመላው ዓለም እንደሚቀጥል አስታወቋል።

ዋትስአፕ የሚታወቅበት የመልዕክት ሥርዓት አንድ መልዕክት በሁለቱ የመልዕከት ተላላኪዎች መካከል ብቻ የሚቀርበት ወይም 'ኢንድ-ቱ- ኢንድ ኢንክሪፕሽን' የተሰኘው ሥርዓቱ ነው። ይህም የደንበኞቹን መልክት የዋትሳፕ ባለቤት የሆነው ፌስቡክም ሆነ የሕግ አስከባሪዎች መልክቶቹን መመልከት አይችሉም።

የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል ይህ ሥርዓት ሕገወጥ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ከማጋራት ጋር ተያይዞ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ገልፀዋል።