ዋትስአፕ ተጠቃሚዎቹ ቢቆጡም የመተግበሪያ አሠራር ለውጥ ሊያደርግ ነው

ዋትስአፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዋትስአፕ አነጋጋሪ የሆነውን የመተግበሪያ አሠራር ለውጥ ሊተገብር ነው።

ከወር በፊት መተግበሪያው ላይ ለውጥ እንደሚያደርግ ሲያስታውቅ በርካታ ተጠቃሚዎች ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችም ዋትስአፕን ጥለው ወደ ቴሌግራም እና ሲግናል ሄደዋል።

ዋትስአፕ ግን በመተግበሪያው ላይ የማደርገውን ለውጥ በድጋሚ አይቼ ልተገብረው ወስኛለሁ ብሏል።

ዋትስአፕ የሚያደርገው ለውጥ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለፌስቡክ አሳልፎ የሚሰጥ ነው በሚል ብዙዎች ተቃውሞ አሰምተዋል።

ዋትስአፕ ተጠቃሚዎቹ ምቾት እንዲሰማቸው ከዚህ በኋላ ስለሚያደርገው ለውጥ መተግበሪያው ላይ የጽሑፍ ጥቆማ እንደሚሰጥ ተናግሯል። የአሠራር ለውጡ ግንቦት ላይ ይተገበራል ተብሎም ይጠበቃል።

ዋትስአፕ እንደሚለው፤ ከአጋር ድርጅቱ ፌስቡክ ጋር የሚጋራው መረጃ የተጠቃሚዎችን የጽሑፍ መልዕክትና የስልክ ጥሪ አያካትትም።

ዋትስአፕ አሁንም ቢሆን ከፌስቡክ ጋር መረጃ ይጋራል። ይህም ተጠቃሚዎች ያሉበትን ቦታ፣ ስለ ስልካቸው ዝርዝር መረጃ እና መተግበሪያውን ተጠቅመው ያካሄዱትን ሸመታ ያካትታል።

ዋትስአፕ የሚያደርገው የአሠራር ለውጥ ተጠቃሚዎች በመተግበሪያው የንግድ መረጃ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያስችላል ተብሏል። ለውጡ ልዩ የግል መረጃ ጥበቃ ሕግ ባላቸው አውሮፓ እና ዩናይትድ ኪንግደም አይተገበርም።

የግል መረጃ ጥበቃ ባለሙያው ሬይ ዋልሽ እንደሚሉት አሁንም ቢሆን ዋትስአፕ መረጃን ከፌስቡክ ጋር ይጋራል። "ዋትስአፕ ለውጥ ላደርግ ነው ሲል የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ከመሆኑ በፊት ብዙ ተጠቃሚዎች የዋትስአፕ መረጃ ለፌስቡክ ተላልፎ እንደሚሰጥ አያውቁም ነበር" ብለዋል።

ዋትስአፕ ባወጣው መግለጫ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚላክ መልዕክትን እንደማያገኙ፣ ለሌላ ወገን አሳልፈው እንደማይሰጡም ያስረግጣል።

"የግል መረጃና ደህንነትን በመጠበቅ ረገድ ሕዝቡ እንዲያምነን እንፈልጋለን" ብሏል ዋትስአፕ።

የዋትስአፕ ትልቁ ገበያ ያለው ሕንድ ሲሆን፤ 340 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት። የሕንድ መንግሥት ከወር በፊት ዋትስአፕ ሊያደርግ ያሰበውን የአሠራር ለውጥ እንዲሰርዝ መጠየቁም ይታወሳል።