እስራኤል የረጅም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሯ አሰናብታ አዲስ መረጠች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ፓርላማ ለረጅም ዓመታት በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር ላይ የቆዩት ቤንያሚን ኔታኒያሁ የሚተኩ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መረጠ።
አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት በሁለት ዓመት ውስጥ በተደረጉ አራት ምርጫዎች ምክንያት ውዝግብ የተጫነውን የእስራኤልን ሕዝብ አንድ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ናፍታሊ ቤኔት ከ12 ዓመታት በኋላ በእልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ከስልጣን ገሸሽ የተደረጉትን ቤንያሚን ኔታንያሁ ተክተዋል።
እሁድ በኢየሩሳሌም ፓርላማ ውስጥ በተደረገው ክርክርም ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚስተር ኔታንያሁ "ተመልሰን እንመጣለን" በማለት ቃል ገብተዋል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም መንግሥታቸው ለሁሉም ሕዝብ ጥቅም እንደሚሰራ ገልፀው በተለይም በትምህርት፣ በጤና እና አሳሪ የሆኑ አሰራሮችን በማሻሻል ላይ እንደሚያተኩርም ተናግረዋል።
ትላንት እሁድ በተደረገው ድምፅ የመስጠት ሂደትም የአንድ ድምፅ ብልጫ (60 ለ 59) በማግኘት ያሸነፈው የቀኝ አክራሪ ብሔረተኛው ክንፍ በእስራኤል ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የተባለለትን የፓርቲዎች ጥምረት በመመስረት አገሪቱን ይመራል።
የያሚና ፓርቲ መሪ የሆኑት ቤኔት በሥልጣን መጋራት ስምምነቱ መሰረት እስከ መስከረም 2023 እኤአ ድረስ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለግላሉ።
በቀጣይ ላሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የለዘብተኛ ፓርቲው መሪ ያሺር አቲድ ስልጣኑን ተረክበው ይመራሉ።
በእስራኤል ታሪክ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት ኔታኒያሁም የፓርቲያቸው መሪ ብሎም በምክር ቤቱ የተቃዋሚ መሪ ሆነው ይቀጥላሉ።
የፓርላማ አባላቱ ለአዲሱ የጥምረት መንግሥት ድምጽ ከሰጡ በኋላ ኔታንያሁ ወደ ቤኔት በመሄድ እጃቸውን ሲጨብጧቸው ታይተዋል።
የ49 ዓመቱ ቤኔት በንግግራቸው ላይ "ይህ የልቅሶ ቀን አይደለም። በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመንግሥት ለውጥ ተደርጓል። ይኸው ነው። ማንም ሰው ፍርሃት እንዳይሰማው የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። እና ዛሬ ማታ ይህንን ደስታ ለማክበር ላሰባችሁም፤ እኛ ጠላቶች አይደለንም፣ አንድ ሕዝብ ነን በሌሎች ህመም ላይ አትጨፍሩ" ሲሉ ተሰምተዋል።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ቃል አቀባይ በበኩላቸው "ይህ የእስራኤል ውስጣዊ ጉዳይ ነው። አቋማችን ሁል ጊዜ ግልፅ ነው፣ የምንፈልገው የፍልስጤም መንግሥት በ1967 ድንበሯ ከነ ዋና ከተማዋ ኢየሩሳሌም ጋር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ጋዛን የሚቆጣጠረው የእስላማዊው ቡድን ሀማስ በበኩሉ "ይህ የወረራ እና የቅኝ ግዛት ኃይል ነው፤ መብታችንን ለማስመለስ በኃይል እንቃወማለን" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ቢደን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ለቤኔት ገልፀው "የመቀራረብ እና ዘላቂ" የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።












