የዓለም ሙቀት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው መጠን ላይ ይደርሳል ተባለ

የካሊፎርንያ ቃጠሎ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቀጣይ አምስት ዓመታት የዓለም ሙቀት መጠን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱ እንደማይቀር ተመራማሪዎች ተነበዩ።

አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ የ2025 የዓለም ሙቀት ኢንዱስትሪ ከመስፋፋቱ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ1.5 ሴንቲግሬድ ይግላል።

በፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ላይ ሁለት የሙቀት መጠኖች ተቀምጠዋል። ከሁለቱ አነስተኛ የሚባለው ደግሞ ይህ 1.5 ሴንቲግሬድ ነው።

የዓለም የሜትሮሎጂ ተቋም ይፋ ያደረገው ጥናት በዩናይትድ ኪንግደም የሜትሮሎጂ ድርጅት ሲመራ፤ አሜሪካና ቻይናን ጨምሮ አሥር አገሮችን ዳሷል።

ባለፈው አሥር ዓመት የነበረው መላ ምት በአንድ ዓመት ውስጥ የዓለም ሙቀት 1.5 ሴንቲግሬድ የሚሆንበት እድል 20 በመቶ ነው የሚል ነበር።

አሁን ግን የስጋት መጠኑ ወደ 40 በመቶ አድጓል።

ከፍተኛ የሜትሮሎጂ አጥኚው ሊዎን ኸርማንሰን እንደሚሉት፤ እአአ ከ1850-1900 ከነበረው የሙቀት ግምት የአሁኑ ከፍ ብሏል።

"1.5 ጋር ባንደርስም እየተቃረብን ነው። በአፋጣኝ እርምጃ መወሰድ አለበት" ብለዋል።

የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት የሙቀት መጠን ጣሪያው በጣም ቢበዛ 2 ሴንቲግሬድ እንዲሆንና መጠኑ ከ1.5 ባያልፍ እንደሚመከር ውሳኔ አሳልፏል።

ይህ የሙቀት መጠን ጣሪያ የተቀመጠው ግን ለአንድ ዓመት ሳይሆን ዓለም ከዓመታት በኋላ ትደርስበታለች ተብሎ ነበር።

የተሰነጣጠቀ መሬት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን የጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ጆሪ ሮጀሊ እንደሚሉት በሜትሮሎጂ ተቋሙ የተተነበየው 1.5 ሴንቲግሬድ እና የፓሪስ ስምምነት ላይ የተቀመጠው 1.5 ሴንቲግሬድ አንድ አይነት አይደሉም።

"የፓሪሱ ስምምነት ያተኮረው የዓለም የሙቀት መጠን ላይ ነው። ይህም ከዓመት ዓመት ያለውን የሙቀት መጠን አስተካክለን መድረስ ያለብንን የሙቀት መጠን ይጠቁማል" ሲሉ ያስረዳሉ።

ሆኖም ግን የሜትሮሎጂ ተቋሙ ያስቀመጠው የዓለም የሙቀት መጠን ግምት "በጣም መጥፎ ዜና ነው" ይላሉ።

የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የተወሰዱ እርምጃዎች በቂ እንዳልሆኑ ያሳያል። የካርቦን ልቀትን በአፋጣኝ ወደ ዜሮ ማድረስ የግድ እንደሆነም ይጠሙማል።

2018 ላይ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ፓናል አንድ ሪፖርት አውጥቷል። በዚህ ሪፖርት መሠረት የሙቀት መጠን ከ1.5 ሴንቲግሬድ ሲዘል ዓለም እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ትገባለች።

አሁን ላይ አገራት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ቃል እየገቡ ነው። ቢሆንም ግን የዓለም የሙቀት መጠን ወደ 3 ሴንቲግሬድ እየተጠጋ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዓለም የሜትሮሎጂ ተቋም ዋና ጸሐፊ ፕ/ር ፔትሪ ታላስ አዲስ የወጣው ጥናት "ከአሐዝ በላይ ነው" ይላሉ።

በፓሪሱ ስምምነት ላይ ወደተቀመጠው የሙቀት መጠን ዓለም እየተጠጋች እንደሆነ ጥናቱ እንደሚያሳይ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

"ጥናቱ አንቂ ደውል ነው። በስምምነቱ የገባነውን ቃል አክብረን የካርቦን ልቀት መጠንን በአፋጣኝ መቀነስ እንዳለብን ነው የሚያሳየው" ይላሉ።

በሬዲንግ ዩኒቨርስቲ የአየር ንብረት ሳይንቲስት የሆኑት ፕ/ር ኤድ ሆውኪንስ እንደሚናገሩት፤ እአአ በ2016 ሁለት ወራት ሙቀታቸው ወደ 1.5 ሴንቲግሬድ ከፍ ብሎ ነበር።

ይህ የሚያሳየው የዓለም ሙቀት እየጨመረ በሄደ ቁጥር በዓመት ውስጥ ብዙ ወራት ሞቃት እንደሚሆኑ ነው።

"መጀመሪያ ብዙ ወራት ሙቀታቸው ከ1.5 ሴንቲግሬድ በላይ ይሆናል። ከዚያም ዓመቱን ሙሉ ሞቃት ይሆናል። ቀስ በቀስ ሙቀቱ ለሁለትና ለሦስት ዓመታት ይዘልቃል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

1.5 ሴንቲግሬድ የሚለው የሙቀት መጠን እንደ ጣሪያ ተቀምጧል ማለት የግድ 1.5 ላይ ሲደረስ እርምጃ ይወሰድ ማለት እንዳልሆነም ያስረዳሉ።

መፍትሔ የሚሆነው የሙቀት መጠንን ጣሪያው ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ መቀነስ እንደሆነ ይመክራሉ።

"የአየር ንብረት ለውጥ አሁንም ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነና በቀጣይ ዓመታት ሊባባስ እንደሚችል እውቅና በመስጠት እርምጃ መውሰድ ያዋጣል" በማለት ይገልጻሉ።

የፊታችን ጥቅምት በግላስጎው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ይካሄዳል። ጉባኤው ለዓለም መሪዎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው።

ከዚህ ጉባኤ በፊት የወጣው የሜትሮሎጂ ተቋም ጥናት ካሁኑ ስለ ጉዳዩ ውይይት ለማጫር ያለመ ነው።