ኮሮናቫይረስ፡ ዓለምን ለሁለት የከፈለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ

በዝናብ እጥረት የተሰነጣጠቀ መሬት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ በተሰራ አንድ ዓለማቀፍ ጥናት መሰረት የዓለማችን ዜጎች የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተና መወሰድ አለበት ብለው በሚያምኑት እርምጃ ዙሪያ ከባድ ስጋት እንዳለባቸው በመጠቆም በዚሁ ረገድ ግን በሁለት የተከፈለ ሀሳብ እንዳለ ይፋ አድርጓል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው በድሀ አገራት የሚኖሩ ዜጎች የአየር ጸባይ ለውጥ ጉዳይ ልክ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተሰጠውን አይነት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ከፍተኛ እምነት አላቸው ተብሏል።

ነገር ግን በሀብታም አገራት የሚኖሩ ዜጎች የአየር ጸባይ ለውጥ ላይ ለዘብ ያለ አመለካከት እንዳላቸው ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል ደግሞ የዌልሱ ልዑል የአየር ጸባይ ለውጥ ጉዳይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ጉዳት እንደውም ያሳንሰዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

ግሎብስካን የሚባል ተቋም በሰራው በዚሁ ጥናት መሰረት የዓለማችን ሕዝቦች የአየር ጸባይ ለውጥ ጉዳይ እጅጉን እያሳሰባቸው እንደሆነና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ ከባድ እንዳደረገባቸው አስታውቋል።

በዓለማችን ከሚገኙ 27 አገራት በተሰበሰበው መረጃ መሰረት 90 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች የአየር ጸባይ ለውጥ ጉዳይ እጅግ በጣም አሳሳቢ ወይም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ እንደሚገኝ ያምናሉ።

ሰዎችም ሆኑ ፖለቲከኞና ባለሀብቶች ጉዳዩን በተመለከተ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ አለባቸው ብለው ከሞገቱት መካከል የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ሕንድ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና የአሜሪካ ዜጎች ይገኙበታል።

ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጉዳዩ እምብዛም ትኩረት ባይሰጡም አሜሪካ ውስጥ የአየር ጸባይ ለውጥ እንደ ትልቅ የዓለማችን ችግር መታየት አለበት ብለው የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር በአውሮፓውያኑ ከነበረበት 60 በመቶ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ሰኔ ካይ ወደ 81 በመቶ ከፍ እንዳለ ጥናቱ ጠቁሟል።

ሕንድ ውስጥ ደግሞ በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት ጉዳዩ በእጅጉ ያሳስበናል የሚሉ ሰዎች ቁጥር ከ70 በመቶ ወደ 93 በመቶ ከፍ ብሏል።

ነገር ግን ዜጎች ልክ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ የታየው አይነት መነሳሳትና ቁርጠኝነት መንግሥታቸው የአየር ጸባይ ለውጥን በተመለከተ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ አለበት ወይ በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ለሁለት ተከፍለዋል።

ልዩነቱ ደግሞ ያለው በደሃና ሀብታም በሚባሉት አገራት መካከል ነው።

በጃፓን፣ ስዊድን፣ አውስትራሊያ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከሚገኙ ዜጎች መካከል መንግሥታቸው የአየር ጸባይ ለውጥን በተመለከተ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለው የሚያምኑት 45 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ናቸው።

ነገር ግን በኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ሜክሲኮ፣ ቱርክና አርጀንቲና የሚገኙ ዜጎች መንግሥታት ፈጣንና ውጤታማ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ብለው የሚያምኑት ከ70 በመቶ በላይ መሆናቸውን ይሄው ጥናት ጠቁሟል።

በተመሳሳይ በአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት ማነው ዋነኛ ተጎጂ ተብለው የተጠየቁት የነዚሁ አገራት ዜጎች 60 በመቶ የሚሆኑት ድሀ የዓለማችን ዜጎች የቀጥታ ተጎጂ እንደሆኑ ያምናሉ።

ነገር ግን በጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ሰዎች መካከል ከ40 በመቶ በታች የሚሆኑት ብቻ ናቸው ዋነኛ ተጎጂዎች በድሀ አገራት የሚኖሩ ሰዎች እንደሆኑ የሚያስቡት።

በዩናይትድ ኪንግደም በዳሰሳ ጥናቱ ከተካተቱ ሰዎች መካከል 13 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው የዓለማችን ሙቀት መጨመር በግል ሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ የገለጹት።

ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምን ያክል ተጽዕኖ አሳደረባችሁ ተብለው ከተጠየቁት እነዚሁ ሰዎች መካከል 34 በመቶ የሚሆኑት አዎ ቀጥተኛ ተጽህኖ አሳድሮብናል ብለዋል።

ይሄው አይነት ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንደ አሜሪካ፣ ስዊድን እና ጃፓን ባሉ አገራትም ተስተውሏል።

ነገር ግን በሜክሲኮ፣ ቱርክ፣ ቪዬትናም እና ኬንያ በመሳሰሉት አገራት ከሚገኙ ሰዎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት የአየር ጸባይ ለውጥ በሕይወታቸው ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዳሳረፈባቸው ገልጸዋል።

ይህ ጥናት የተሰራው ከእያንዳንዱ 27 አገራት የተመረጡ 1ሺ አዋቂዎችን በማሳተፍ ነው።

ጥናቱም ይፋ የተደረገው በኒውዮርክ እየተካሄደ ለሚገኘው ዓለም የአየር ጸባይ ሳምንት 2020 መክፈቻ ላይ ሲሆን በዚህ ዓመት ከሚካሄዱ የአየር ጸባይ ለውጥን ከሚመለከቱ ትልልቅ ስብሰባዎች መካከል አንዱ ነው።

ኮሮና
Banner