ማኅበራዊ ሚዲያ ፡ በርግጥ ትዊተር ዘረኛ ይሆን?

ሚች ኮኔል (በስተግራ) ባራክ ኦባማ (በስተቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, US Gov

የምስሉ መግለጫ, አንድ ተጠቃሚ ትዊትር የሚች ኮኔል ምስልን ከባራክ ኦባማ በማስበለጥ እንደሚያሳይ ደርሶበታል

የማኅበራዊ ሚዲያዎች የተጠቃሚዎቻቸውን ምስል በማሳየት ረገድ የዘር መድልዖ ይፈጽማሉ ብለው አስበው አያውቁ ይሆናል፤ ትዊተር ግን እጅ ከፍንጅ ተይዟል።

ትዊትር የተጠቃሚዎቹ ምስልን በማሳየት ረገድ ከጥቁር ፊት ይልቅ የነጭን የበለጠ መምረጡን ከደረሱበት በኋላ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቋል።

ተጠቃሚዎች እንዳስተዋሉት ከሆነ አንድ የጥቁር ሰው ፊት እና የነጭ ሰው ፊት በተመሳሳይ ፖስት ላይ ቢኖሩ ትዊተር ለሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ማሳየት የሚመርጠው የነጩን ግለሰብ ፊት ነው ተብሏል።

ኩባንያው በበኩሉ የሚሰራበት አልጎሪዝም [የአሰራር ቀመር] የዘር እና የጾታ ፈተና ፍተሻ እንደተደረገለት አብራርቷል።

አክሎም "የበለጠ ምዘና ማድረግ እንዳለብን ግልጽ ሆኗል" ሲል ተናግሯል።

ትዊትር በሰሌዳው ላይ የለጠፈው አስተያየት

የፎቶው ባለመብት, Twitter

የትዊተር የቴክኖሎጂ የበላይ ኃላፊ ፓራግ አግራዋል እንዳሉት "ሞዴላችንን ተግባራዊ በምናደርግበት ወቅት ፍተሻ አድርገን ነበር፤ ነገር ግን ተከታታይ የሆነ ማሻሻያ ያስፈልገዋል።"

በዚህ አላበቁም፤ "ይህንን የሕዝብ አስተያየትና ተከታታይ ፍተሻ ወድጄዋለሁ፤ እናም ከዚህ ለመማር ዝግጁ ነን" ብለዋል።

ትዊትር ከተጠቃሚዎቹ ጥያቄ የተነሳበት በቫንኮቨር ካናዳ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት የዩኒቨርስቲ አስተዳዳሪው ኮሊን ማድላንድ ከባልደረባቸው ጋር በዙም [በኢንተርኔት] ስብሰባ እያደረጉ እያለ የጓደኛቸውን ጭንቅላት ማየት መቸገራቸውን ተከትሎ ነበር።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሶፍትዌሩ የጥቁር ሰውን ጭንቅላት እንደ ጀርባ ምስል (background) በመቁጠር ማስወገዱ ነው።

ከዚያም ይህንኑ ቅሬታቸውን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ሲያኖሩ ሌላ ነገር አስተዋሉ።

ይህም ከጥቁር ወዳጃቸው ምስል ይልቅ የእርሳቸው የነጩን ምስል ተለይቶ በሞባይል ስልካቸው ላይ መታየቱ ነው።

ይህ የግለሰቡ ግኝት በርካታ የትዊተር ተጠቃሚዎች የተለያዩ ነገሮችን እንዲሞክሩ አድርጓቸዋል።

የትዊተር ዲዛይን ኃላፊ የሆኑት ዳንትሌይ ዳቪስ እንዳረጋገጡትም የትዊተር አልጎሪዝም የጥቁሩን ሰው ጢም እና መነጽር የሚያስተካክለው ምክንያቱ "ከቆዳው ጋር ያለው ውህደት ለማስተካከል" መሆኑን ተናግረዋል።

ለቀረበው ትችትም በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ምላሽ ሲሰጡ "የናንተኑ ያህል ተናድጃለሁ። ይህንን ማስተካከል ያለብኝ እኔው ነኝ አስተካክለዋለሁ" ብለዋል።

አክለውም "መቶ በመቶ ጥፋቱ የእኛ ነው። ማንም ኃላፊነቱን ሊወስድልን አይችልም" ሲሉ ስህተታቸውን ለማረም እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።