አሜሪካ፡ ትዊተር ቲክቶክን ለመግዛት ፍላጎት አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራምፕ የቻይናው ቲክቶክ ለአሜሪካው ኦራክል እንዲሸጥ እንደሚፈልጉ ተናገሩ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የአሜሪካው ኦራክል ቲክቶክን ቢገዛው መልካም ነገር ነው አሉ፡፡
ይህን የተናገሩት ኦራክል የቻይናውን ዝነኛ የማኅበራዊ ትስስር መተግበሪያ ቲክቶክን ለመግዛት እየተነጋገረ ባለበት ሰዓት ነው፡፡
ኦራክል ቲክቶክን የሚገዛው በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በኒዊዚላንድ ያለውን ድርሻና ገበያ ነው፡፡
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ለቲክቶክ ባለቤት ባይትዳንስ ኩባንያ የአሜሪካ ድርሻውን በ90 ቀናት ውስጥ እንዲሸጥ አስጠንቅቀው ካልሆነ ግን ቲክቶክ በአሜሪካ ይዘጋል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
የኦራክል ሊቀመንበር ላሪ ኤሊሰን የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ ሲሆኑ ለምርጫ ቅስቀሳ የገንዘብ መዋጮ ከሚያሰባስቡላቸው ሰዎች አንዱ ነው፡፡
አሁን እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ኦራክል ቲክቶክን ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት አድሮበታል፡፡ ከተቻለም ከአውስትራሊያ፣ አሜሪካና ኒውዚላንድ ገበያው በተጨማሪ የካናዳን ለማካተት ይፈልጋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ እንደተናገሩት ከሆነ ቲክቶክ ለአሜሪካ ኩባንያ ሲሸጥ መንግስት የተወሰነ ገንዘብ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ ይህ በአሜሪካ የነጻ ኢኮኖሚ ሥርዓት የተለመደ ነገር አይደለም፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ቲክቶክ ከአሜረካ ድርሻውን ሽጦ ይውጣ በሚል 90 ቀናትን ያስቀመጡት ድርጅቱ የዜጎችን መረጃ እየቃረመ ለቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አሳልፎ ይሰጣል በሚል ነው፡፡
ባይትዳንስ በበኩሉ ክሱን አስተባብሏል፡፡
ብዙዎች ቲክቶክ በቻይናና በአሜሪካ የንግድ ጦርነት ውስጥ የጦስ ዶሮ ሆኗል ብለው ያስባሉ፡፡
ከኦራክል ሌላ ማይክሮሶፍት ቲክቶክን ለመግዛት ከባለቤቱ ባይትዳንስ ኩባንያ ጋር ንግግር መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ከሁለቱ ግዙፍ ኩባንያዎች ሌላ ትዊተርም ቲክቶክን ለመግዛት ፍላጎት አሳይቷል፡፡
ቲክቶክ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ተወዳጅ የስልክ መተግበሪያ መሆኑን የሚያሳየው በዚህ ዓመት ብቻ 2 ቢሊዮን የዓለማችን ሰዎች ስልካቸው ላይ ጭነውታል፡፡















