ቲክ ቶክ፡ የዓለም መንግሥታት ለምን ቲክ ቶክ ላይ አደሙ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቲክ ቶክ የተሰኘው የተንቀሳቃሽ ምስሎች መጋሪያ በአሜሪካ ድርጅት ካልተገዛ ሊያግዱት እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ በሚሊዮኖች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈ ማሕበራዊ ድር-አምባ እንዴት የአሜሪካ መንግሥት የደህንነት ስጋት ሊሆን ቻለ?
ቲክ ቶክ ላይ የሚለጠፉ ምስሎች አብዛኛውን ጊዜ ፈገግ የሚያሰኙ ናቸው። አንዳንዶቹ ከጥቂት ሰከንድ በላይ ዕድሜ የላቸውም። ቢሆንም ግን ድርጅቱ ከእነዚህ ምስሎች ሚሊዮኖች ያተርፋል።
መተግበሪያው የዓለም ገበያን የተቀላቀለው ታኅሣሥ 2010 ነው። ነገር ግን በፍጥነት የሚሊዮኖችን ተንቀሳቃሽ ስልክ ለማዳረስ ጊዜ አልወሰደበትም።
በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞቹ ወጣቶች ናቸው።
ቲክ ቶክ ልክ እንደሌሎቹ ታዋቂ ማሕበራዊ ድሮች ወጣቶች ሰብሰብ ብለው የፈጠሩት አይደለም።
ቲክ ቶክ የሶስት መተግበሪያዎች [አፕሊኬሽኖች] ቅይጥ ነው። መጀመሪያ ሚዩዚካሊ የሚባል መተግበሪያ ነበር። በፈረንጆቹ 2014 የተፈበረከው ይህ 'አፕ' አሜሪካ ውስጥ ተወዳጅ ነበር። ይህን የተመለከተው ባይትዳንስ የተሰኘው ኩባንያ ዶይን የተሰኘ ተመሳሳይ ቅርፅ ያለው 'አፕ' ፈበረከ።
ዶይን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በቻይናና በታይላንድ 100 ሚሊዮን ደንበኞች አተረፈ።
የመተግበሪያውን ትርፋማነት የተመለከተው ድርጅቱ በአዲስ ስያሜ ብቅ ማለት ፈለገ። ይሄኔ ነው ቲክ ቶክ የተሰኘው 'አፕ' የተፈበረከው። ባይትዳንስ ሚዩዚካሊን ሙሊ በመሉ ገዝቶ የራሱ ንብረት አደረገ። ከዚያም ቲክ ቶክን ማስፋፋት ተያያዘ።
ቲክ ቶክ ከሌሎች አፖች ለየት የሚያደርገው ሙዚቃን የሚጠቀምበት መንገድና ጠንካራ ስልተ-ቀመር [አልጎሪዝም] ተግባራዊ ማድረጉ ነው። ስልተ ቀመር ማለት መተግበሪያ ደንበኞች ምን እንደሚፈልጉ በቶሎ መማር ይችላል ማለት ነው።
ተጠቃሚዎች በርካታ ሙዚቃዎችን፣ ማጌጫዎችንና ምስሎችን መርጠቅ መጠቀም ይችላሉ።
የቢቢሲ ዜና እወጃ ሙዚቃን ጨምሮ አሜሪካዊው ራፐር ሊል ናስ ኤክስ ያቀነቀነው ኦልድ ታውን ሮድ ሙዚቃ በቲክ ቶክ ምክንያት የሚሊዮኖች መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
'ፎር ዩ ፔጅ' የተሰኘው የመተግበሪያው ገፅታ ተጠቃሚዎች ከዚህ በፊት የተመለከቷቸውን ምስሎች መሠረት አድርጎ ይዘቶችን ያቀርባል።
ቲክ ቶክ ላይ ምንም ያክል ያነሰ ተከታይ ቢኖርዎት መተግበሪያው ገፅዎ ላይ የለጠፉት ይዘት ሊወደድ ይችላል ብሎ ካሰብ ለብዙዎች ያጋራዋል።
የቲክ ቶክና እህት ኩባንያው ዶይን ብዙዎች ከገመቱት በላይ በፍጥነት እየተመነደገ ነው።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ሁለቱ አፖች አንድ ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ስልካቸው ላይ እንደጫኗቸው ይፋ አድርገዋል። ከነዚህ መካከል ግማሽ ቢሊየኑ የዕለተተተ ለት ተጠቃሚዎች ናቸው።
ከአንድ ዓመት በኋላ 2 ቢሊዮን ሰዎች አፖቹን ስልካቸው ላይ ሲጭኑ፤ 800 ሚሊዮን ገደማ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ተጠቃሚዎች እንዳላቸው ይፋ ተደረገ።
ይህ የቲክ ቶክ በፍጥነት ማደግ ኩባንያው በፖለቲከኞች ዕይታ ሥር እንዲወድቅ አድርጎታል። አንድ የቻይና 'አፕ' እንዴት በአጭር ጊዜ ይሄ ሁሉ ተጠቃሚ ሊኖረው ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ይመስላል።
ምንም አንኳ ወቀሳዎቹ እስካሁን የተጨበጠ መሠረት ባይኖራቸውም ሕንድና አሜሪካ ቲክ ቶክ ከጠተቃሚዎች የግል መረጃ እየሰበሰበ ለቻይና መንግሥት እየሰጠ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
ሕንድ መጀመሪያው ቲክ ቶክ ጥቅም ላይ እንዳይውል ያገደችው ባለፈው ዓመት ነበር። ይህም የሆነው አንድ ዳኛ መተግበሪያው የወሲብ ፊልሞችን እያስፋፋ ነው ብለው እግድ በመጣላቸው ምክንያት ነበር። የዳኛው ውሳኔ በይግባኝ ተቀልብሶ እንደነበር አይዘነጋም።
ሕንድ ዘንድሮም ቲክ ቶክ ሌሎች በርካታ የቻይና ምርት የሆኑ መተግበሪያዎች እንዲዘጉ የወሰነችው መንግሥት እኒህ መተግበሪያዎች የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ እየበረበሩ ነው በሚል ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትም ድር አምባው እንዴት እንደሚሠራ እንዲጣራ መርማሪ ያቋቋመው ባለፈው ዓመት ነበር።
በቅርቡ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፓምፔዮ፤ ቲክ ቶክ ለቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ መረጃ ከሚያቀብሉ መተግበሪያዎች መካከል ነው ማለታቸው ይታወሳል።
የዩናይትድ ኪንግደም መረጃ ኮሚሽንና የአውስትራሊያ ደህንነት መሥሪያ ቤት መተግበሪያውን እየመረመሩ እንደሆነ አሳውቀዋል።
ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ሃገራት ከቻይና ጋር ያላቸው ግንኙነት የሻከረ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከቻይና ጋር የንግድ ጦርነት ላይ ናት። የሕንድና የቻይና ወታደሮች ድንበር ላይ ተዋግተዋል። ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በሆንግ ኮንግ ምክንያት ከቻይና ጋር ዓይንና ናጫ ሆናለች። አውስትራሊያም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ከቤይጂንግ መንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ላይ ናት።
ቲክ ቶክ በይፋ ከተጠቃሚዎች መረጃ እንደሚሰበስብ የግላዊ መረጃ ስምምነቱ ላይ ተቀምጧል። የሚሰበሰቡት መረጃዎች ከታች ያሉትን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡
• ተጠቃሚዎች ምን ዓይነት ይዘት እንደሚወዱ
• የት እንደሚኖሩ
• የስላካቸው 'ሞዴል' ምን እንደሆነና ምን ዓይነት አሰራር [ኦኤስ] እንደሚጠቀም
• እንዲሁም ተጠቃሚዎች ምን ዓይነት የመተቢያ ቴክኒክ እንደሚጠቀሙ
ነገር ግን በይፋ የሚታወቀው የቲክ ቶክ መረጃ ስብሰባ መንገድ ከሌሎች መረጃ ለመሰብሰብ ሁሌም ከተጠሙት እንደ ፌስቡክ ያሉ መተግበሪያዎች አይለይም።
የድርጅቱ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ አሜሪካዊው ኬቪን ሜየር ቲክ ቶክ ባለሙያዎች ድርጅቱ መረጃ እንዴት እንደሚሰበስብ ማጣራት እንዲችሉ እንፈቅዳለን ብለዋል።
ስጋቱ ቲክ ቶክ መረጃ የሚሰበስብበት መንገድ ብቻ አይደለም። ባይትዳንስ የተሰኘው የቲክ ቶክ አቃፊ ኩባንያ ለቻይና መንግሥት መረጃ አሳልፎ ይሰጣል ወይ የሚለውም ጭምር እንጂ።
ሁዋዌ የተሰኘው የቻይና ቴሌኮሚዩኔክሽን ኩባንያም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞታል።
2017 ላይ የፀደቀው የቻይና ብሔራዊ ደህንነት ሕግ ማንኛውም ድርጅትም ሆነ ዜጋ ከሃገሪቱ ደህንነት መሥሪያ ቤት ጋር የመተባበር ግዴታ እንደላበት ደንግጓል።
ቲክ ቶክም ሆነ ሁዋዌ ለቻይና መንግሥት ምንም ዓይነት መረጃ አሳልፈን አልሰጠንም ሲሉ ያስተባብላሉ።
ቲክ ቶክ የሚደርስበት ወቀሳ መረጃን የተመለከተ ብቻ አይደለም። አምባው አንዳንድ ድምፆችን ለማፈን ወይም ለማጮህ ጥቅም ላይ ይውላል የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ለምሳሌ ወርሃ ግንቦት ላይ የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት [#BlackLivesMatter] የተሰኘውን ንቅናቄ በርካቶች ቢያራግቡትም መተግበሪያ ሆነ ብሎ ይህን ተቃውሞ አፍኗል ተብሎ ይተቻል።
አልፎም የኩባንያው ይዘት ተቆጣጣሪዎች የፈለጉትን ነገር የማስቀረት ወይም ጎልቶ እንዲታይ የማድረግ መብት አላቸው ሲል ዋሽንግተን ፖስት ፅፏል።
ዘ ጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ ደግሞ ቲክ ቶክ የቲቤት ነፃ አውጭ ንቅናቄንና የቲያናንሜን ተቃውሞዎችን ድምፅ አፍኗል ሲል መዘገቡ አይዘነጋም።
የቢል ጌትስ ማይክሮሶፍት የቲክ ቶክን የአሜሪካ ገበያ ለመግዛት ማቀዱ ተሰምቷል። ይህ ቲክ ቶክ ምን ያክል ጠንካራ ድርጅት እንደሆነ ማሳያ ነው።
ቲክ ቶክ ከ25 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች መገናኛ መድረክ ሆኗል። ትዊተርና ኢንስታግራም ደግሞ ዕድሜያቸው ከ25 በላይ ለሆኑ ሰዎች የተተዉ ይመስላሉ።
ቲክ ቶክ አሜሪካ ውስጥ ቢዘጋ ለድርጅቱም ሆነ ለወጣቶች ኪሳራ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ተመሳሳይ ገፅታ ያላቸው አንዳንድ መተበግሪያዎች ከሰሞኑ ገበያዎች እንደደራም ተሰምቷል።
ነገር ግን አብዛኛዎቹ ተጠቃሚዎች ቲክ ቶክ እስኪዘጋ ድረስ እንጠቀማለን ባይ ናቸው።














