ኮሮናቫይረስ የሴቶችን ሕይወት እየቀየረው ይሆን?

ከቤት ውስጥ የምትስራ እናት

የፎቶው ባለመብት, Dockery

ሴቶች በቤት ውስጥ ሲውሉ በአብዛኛው ልጆችን የመንከባከብና ቤትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የሚጣልባቸው ሲሆን ከኮሮናቫይረስ በኋላ ደግሞ ሥራቸውንም ሊያጡ የሚችሉ ብዙዎች ናቸው።

ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በርካቶች በቤት ውስጥ በመዋላቸው አስርት ዓመታት በሴቶች እኩልነትና ተጠቃሚነት ዙሪያ ሲሰሩ የነበሩ ሥራዎችን መና እንዳያስቀረው እየተሰጋ ነው።

ስዊድናዊቷ አና ዣቪዬር የሁለት ልጆች እናት ስትሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የስምንት ወር ነፍሰጡር ነች። ምንም እንኳን ባለፉት ወራት ከቤተሰቦቿ ቤት በመውጣት የራሷን ቤት በማፈላለግ የነበረች ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነገሮችን እንዳመሰቃቀለባት ትናገራለች።

ከወረርሽኙ በፊትም ለብዙ ዓመታት የሰራችበትን የውበት መጠበቂያዎች አምራች ኩባንያ በመልቀቅ ስቶክሆልም ውስጥ የራሷን የህጻናት መገልገያዎች ማምረቻ ድርጅት ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነበረች።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ እሷና ባለቤቷ ከቤት መስራት የጀመሩ ሲሆን፤ በቤት ውስጥ ያለው የሥራ ክፍፍል ግን የሥራ ሰዓቷን ጭምር እንደሚሻማባት ትናገራለች።

ምንም እንኳን በቤት ውስጥ ለሚያስፈልጉ ነገሮች በየወሩ እኩል የሆነ ገንዘብ አዋጥተው የሚኖ ቢሆንም ፤ እሷ ከባለቤቷ በበለጠ መልኩ ልጆችን የመንከባከብ፣ ምግብ ማብሰልና ቤት የማጽዳት ኃላፊነት አለባት።

"በውይይታችን ወቅት ባለቤቴ የህክምና መሳሪያዎችን ለሚያመርት ድርጅት ስለሚሰራና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደገው ጥረት መንግሥትን ስለሚረዳ ሙሉ ጊዜውን መሰዋት እንዳለበት ተስማማን።"

ነገር ግን ሥራውን ከጨረሰ በኋላ ያሉበትን ቀላል የሚባሉ ኃላፊነቶች እንኳን አሁንም ቢሆን ለመወጣት ፍላጎት አልነበረውም ትላለች አና።

በዚህ ምክንያት መስማማት ባለመቻላቸው በየቀኑ የምትመላለስ ሠራተኛ ለመቅጠር ተገደዋል።

ነፍሰጡርነት፣ የወረርሽኝ ስጋትና የቤት ውስጥ ሥራ ተደማምረው ሕይትን ከባድ እንዳደረጉባት የምትናገረው አና፤ ልጇን ከመውለዷ በፊት ለመጨረስ አስባቸው የነበሩ በራካታ ነገሮች እስካሁን እንዳልተጀመሩ ትገልጻለች።

ልክ ኮሮናቫይረስ በመላው ዓለም መሰራጨት ሲጀምርና ተቋማት ሠራተኞቻቸው ከቤታቸው ሆነው ሥራቸውን አንዲያከናውኑ ማድረግ ሲጀምሩ ብዙዎች ምናልባት የቤት ውስጥ ሥራዎች እኩል በሆነ ሁኔታ ሊሰሩ ነው የሚል ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር።

ባል፣ ሚስትና ልጆች

የፎቶው ባለመብት, Dowley and Morrison

ነገር ግን በበርካታ አገራት በተሰሩ ጥናቶች መሰረት እውነታው የተገላቢጦሽ ነበር። አና እና መሰል ሴቶች እንደውም ከሌላ ጊዜው በበለጠ ልጆቻቸውን የመንከባከብና ምግብ የማብሰል ኃላፊነት ተጭኖባቸዋል።

ከአሜሪካ ቦስተን ተመራማሪዎች በ3000 ሰዎች ላይ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት በቤት ውስጥ ከሚውሉ ሰዎች ውስጥ ሴቶቹ ከወንዶች በበለጠ ሁኔታ በሳምንት ተጨማሪ 15 ሰዓታትን በቤት ውስጥ ሥራና ልጆችን በመንከባከብ ያሳልፋሉ።

ምንም እንኳን በበርካታ አገራት በተለይም በአውሮፓ የእንቅስቃሴ ገደቦቹ እየላሉ ቢሆንም ኮረሮናቫይረስ ያስከተለው ጫና በቀላሉ የሚጠፋ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።

ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ‘የብሪቲሽ ጆርናል ኦፍ ፊሎሶፊ’ ምክትል አርታኢዋ ኤሊዛቤት ሃኖን በትዊተር ገጿ ላይ ባሰፈረችው መልዕክት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሴቶች ለመጽሔቱ የሚያቀርቧቸው ጽሁፎች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን ገልጻ ነበር።

ይህም መልዕክት በመላው ዓለም በሚገኙ ሴቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ ባወጣው አንድ ጥናት ላይ፤ የኮረሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲሰሩ የነበሩ ሴቶችን ወደ አመራርነት ስፍራ የማምጣትና እኩል እድል የመፍጠር ጥረቶችን ሊያደናቅፍ እንደሚችል ጠቁሟል።

በሪፖርቱ መሰረት ከየካቲት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ብቻ አሜሪካ ውስጥ 11.5 ሚሊየን ሴቶች ሥራቸውን ያጡ ሲሆን በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት ሥራቸውን ያጡ ወንዶች ቁጥር ግን 9 ሚሊየን ነው።

ይህ ደግሞ መጀመሪያውኑ ከሴቶቹ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ወንዶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው መገኘታቸው ነገሮችን አሳሳቢ አድርጓል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊት አብዛኛውን ሰዓታቸውን በሥራቸው ምክንያት ውጪ ያሳልፉ የነበሩ አባቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በአግባቡ መስራት የጀመሩበትና ልጆቻቸውን መንከባከብ እያዘወተሩ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን አሁንም ቢሆንም ሴቶች ከቤት ውስጥ ሥራ የአንበሳውን ድርሻ ቢወስዱም ከነጭራሹ ምንም ነገር ሰርተው የማያውቁ አባቶች ወደ ኩሽናዎች ሲገቡ መታየታቸው እንደ ትልቅ የለውጥ ጉዞ መቆጠር አለበት የሚሉም አልጠፉም።

አንድ ካናዳ ውስጥ በተሰራ ጥናት መሰረት ደግሞ 40 በመቶ የሚሆኑ አባቶች ከዚህ በፊት ከሚያደርጉት በተሻለ ምግብ እያበሰሉና ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ልብስ ማጠብና ቤት ማጽዳት መጀመራቸውን ተናግረዋል።