ኮሮናቫይረስ፡ ኮቪድ-19 ያስተጓጎለው የኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና

የካንሰር ታማሚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች ላይ ጫና ተፈጥሯል

የ33 ዓመቷ ሸምስያ ጀበል ተወልዳ ያደገችው ደሴ ነው። ወሎ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ምግብ ቤት ትሠራ ነበር። አምና የመጀመሪያ ልጇ ሲታመምባት ለህክምና ከደሴ ወደ አዲስ አበባ ተላከች። የአራት ዓመት ልጇ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተደረገለት ምርመራ የደም ካንሰር እንዳለበት ተነገራት።

ሸምሲያ ይህን ስትሰማ ዙሪያው ገደል እንደሆነባት ታስታውሳለች። ልጇን የምታሳክምበት ገንዘብ አልነበራትም። የሚደግፋትም ሰው አልነበረም። የካንሰር ህክምና ደግሞ እጅግ ውድ ነው።

ልጇ የደም ካንሰር እንዳለበት በተነገራት በአንድ ወሩ፤ የልጇ አባት ‘አቅሜ አይችልም’ ብሎ ጥሏት እንደሄደ ትናገራለች። በወቅቱ የወር ከ15 ቀን ነፍሰ ጡር ነበረች።

“ልጄ ደም በየጊዜው [ኬሞ ቴራፒ] ይወስዳል። ታዲያ የማሳክምበት ብር ጨርሼ ህክምናውን አቋርጬ ልሄድ ነበር። ጥቁር አንበሳ ያሉ ሀኪሞች ግን የካንሰር ህሙማንን የሚደግፍ ማኅበር አገናኙኝ። እዚህ ማኅበር ባልገባ ልጄ በሕይወት አይኖርም ነበር።”

ሸምሲያ ማረፊያ ካገኘች በኋላ ለልጇ ህክምና መከታተል ከቀጠለች ሰባት ወራትን አስቆጥራለች።

አሁን ግን መላው ዓለምን ያመሰቃቀለው ኮቪድ-19 የሸምስያም ስጋት ሆኗል። ልጇን ለማሳከም ወደ ሆስፒታል በሄደች ቁጥር በበሽታ ይያዝብኝ ይሆን ብላ ትሳቀቃለች።

ሁለተኛ ልጇን ከወለደች አራት ወር ሆኗታል። የካንሰር ታማሚ ልጇን ይዛ ወደ ጥቁር አንበሳ ስትሄድ ሁለተኛ ልጇንም አስከትላ ነው።

“. . . ህጻኑን የአራት ወር ልጄን ይዤ ነው የምሄደው። እና እንዴት እንደምጠነቀቅ ራሱ ግራ ይገባኛል። ካንሰር የሚታመመው ልጄ ደግሞ ቀልቃላ ነው። እሱን መከታተል እንዴት ከባድ መሰለሽ። እሱን አሳክሜ እስክመለስ ይጨንቀኛል። እዚ [ማኅበሩ ውስጥ] አልኮል አለ፤ እጃችንንም ስለምንታጠብና አጠቃላይ ጥንቃቄውም የተሟላ ስለሆነ ይቀለኛል። ስወጣ ግን ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ራሱ በጣም ያስፈራል።”

እንደ ሸምስያ የካንሰር ታማሚ ልጅ የሚያስታምሙ እንዲሁም የተለያየ አይነት የካንሰር ህመም ያለባቸው ሰዎችም ስጋቷን ይጋራሉ። በተለይም ካንሰር፣ ስኳር፣ አስም፣ ደም ግፊትና ሌላም ህመም ያለባቸው ሰዎች ለኮቪድ-19 ተጋላጭ መሆናቸው ፍርሀታቸውን ያባብሰዋል።

ሸምስያ ልጇን በየ15 ቀኑ ወደ ጥቁር አንበሳ ትወስዳለች። ኮሮናቫይረስ ያለበት ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተገኘ ከተገለጸ ወዲህ እያንዳንዱ የሐኪም ቤት ቀጠሮ ለሸምስያ ጭንቅ ነው።

“ካንሰር ጊዜ የሚሰጥ በሽታ አይደለም። ቀጠሮ አይዘለልም። በመመላለሴ ደስተኛ አይደለሁም። ግን ደግሞ መመላለስ ግዴታዬ ነው። ለምን ብትይ ካልሄድኩ ልጄ ይሞታል። ከዚህ በፊት አብረውኝ የኖሩ ሰዎች የልጆቻቸውን ሕይወት ሲያጡ አይቻለሁ. . . በተቻለኝ አቅም ራሴን እየጠበቅኩ ልጄን እያሳካምኩ እመጣለሁ። እንግዲህ ፈጣሪ ከጎኔ ይሁን።”

በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል ምልክት የማያሳዩ መኖራቸውን ስታስብ ፍርሀቷ ይጨምራል። ሆስፒታል ውስጥ የምታሳልፈው እያንዳንዱ ሰዓት ያሳስባታል።

ሐኪሞች በቀዶ ህክምና ክፍል

የፎቶው ባለመብት, QUEEN VICTORIA HOSPITAL

“ወረፋ አለ፣ ደም ሊያስፈልገው ይችላል። ለምሳሌ ቀይ ደም ስድስት ሰዓት ከተሰጠው እስከ ዘጠኝ ሰዓት መቆየት አለበት። መቼም ሐኪም ቤት በጣም ብዙ ሰው ነው ያለውና በጣም ነው የምፈራው።”

ሸምስያ ከሁለቱ ልጆቿ ጋር የምትኖርበት ማቲዎስ ወንዱ የካንሰር ማዕከል ውስጥ የማህጸንና የጡት ካንሰር እንዲሁም ሌላ አይነት የካንሰር ህመም ላለባቸው ድጋፍ ይደረጋል።

የማዕከሉ የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ዘላለም መንግሥቱ እንደሚሉት፤ ኮቪድ-19 ለካንሰር ህሙማንና ቤተሰቦቻቸው ተደራቢ ፈተና ሆኗል። የካንሰር ህሙማን በሽታ የመከላከል አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው። በበሽታው ከተያዙም ተቋቁሞ ለመዳን ይቸገራሉ።

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። የካንሰር ህሙማን ደግሞ ጥቁር አንበሳ ለሚያደርጉት ህክምና ወደ አዲስ አበባ መምጣት ግድ ስለሚላቸው አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ይናገራሉ።

ሌላው ፈተና የህክምና ተቋማትና ባለሙያዎች አብዛኛውን ትኩረታቸውን ወደ ኮቪድ-19 ማድረጋቸው ነው።

“ጥቁር አንበሳ መጀመሪያ ላይ ቀጠሮ በማራዘም፣ ታካሚዎች ባሉበት ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ጀምረው ነበር። ቀጠሮ ሲራዘም ቶሎ መድኃኒትና ህክምና ማግኘት ያለበት ታካሚ ይጎዳል። በሽታውን ከፍ ወዳለ ደረጃም ይወስደዋል። ወረርሽኙ ከሌሎች ህሙማን በበለጠ የካንሰር ህሙማን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍ ያለ ነው” ይላሉ አቶ ዘላለም።

ካንሰር ዘላቂ የሐኪም ክትትል (ቼክአፕ) እንዲሁም ህክምና የሚያስፈልገው ህመም ነው። የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ከቤት መውጣት መቀነስ፣ አካላዊ ርቀት መጠበቅም አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። የካንሰር ታማሚዎች ወደ ህክምና መስጫ መሄድ ግዴታቸው ስለሆነ ከቤት በወጡ ቁጥር መጨነቃቸው አይቀርም።

አቶ ዘላለም እንደሚሉት፤ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚሰበሰቡ ሰዎችን መቀነስ ስለሚያስፈልግ ማዕከላቸው የሚቀበለውን የህሙማን ቁጥር ቀንሷል። ቀድሞ በአንድ ክፍል እስከ ስድስት ሰው ይይዝ የነበረን ክፍል ወደ አንድ ታካሚና አስታማሚ ለመቀነስ ተገደዋል።

“ሌላው ችግር የትራንስፖርት ዋጋ መጨመሩ ነው። ይሄ ከባድ ጫና ፈጥሮባቸዋል። ካንሰር ረዥም ጊዜ የሚወስድ ህክምና በመሆኑ ታካሚና ቤተሰብም ከባድ ሥነ ልቦናዊ ጫና ውስጥ ይገባል። አሁን ያለው ሁኔታ ደግሞ ነገሮችን አባብሷል” ሲሉ ያስረዳሉ።

ተደራራቢ ጫና

ካንሰር ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ጫና የሚያሳድር የገንዘብ አቅምን የሚፈትንም ህመም ነው። በዚህ ላይ ኮቪድ-19 ሲጨመር ደግሞ ችግሩ ይባባሳል።

ፈተናው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ብቻ አይደለም። የተሻለ የምጣኔ ኃብት ደረጃ ላይ መድረሳቸው የሚነገርላቸው አገሮችም እየተፈተኑ ነው።

በተለያዩ አገሮች የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ኮሮናቫይረስ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ባልተናነሰ ሁኔታ በወረርሽኙ ሳቢያ የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሕይወት ያሳጣሉ።

ለምሳሌ በቫይረሱ ሥርጭት ሳቢያ አገራት በረራ ላይ እገዳ በመጣላቸው፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት የሚያስፈልጋቸውን ክትባት ማግኘት አልቻሉም። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ ወረርሽኙ ቢያንስ የ68 አገሮችን የጤና ዘርፍ ስለሚያቃውስ፤ 80 ሚሊዮን ጨቅላዎች ክትባት ባለማግኘት ለኩፍኝ፣ ፖሊዮና ሌሎችም በሽታዎች ይጋለጣሉ።

የምግብ እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ማድረስ ባለመቻሉም ለምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ አሉ። የዓለም አቀፉ የምግብ ተቋም ዋና ኃላፊ ዴቪድ ቢስሊ፤ ዓለም ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው አይነት ቸነፈር ይጠብቃታል ብለዋል። 130 ሚሊዮን ሰዎች ለዚህ ተጋላጭ ናቸው። አሁን ላይ 135 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል።

በሌላ በኩል የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የአዕምሮ ጤና፣ ካንሰር እንዲሁም ሌሎችም መደበኛ የህክምና ክትትሎችም ችላ ተብለዋል። በመላው ዓለም ያሉ የካንሰር ህሙማን፣ የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸው፣ አስቸኳይ ቀዶ ህክምና የሚሹ ሰዎችም ሰሚ አጥተናል እያሉ ነው።

አቶ ዘላለም እንደሚሉት፤ አሁን ላይ አጠቃላይ የህክምና ዘርፉ ወደ ኮቪድ-19 መዞሩ የካንስር ህክምና ላይ ጫና አሳድሯል።

“በፊትም እንደ ካንሰር ያሉ ህመሞች ጫና አለባቸው። አሁን ደግሞ የበለጠ ተጽዕኖው እየተሰማን ነው” ይላሉ።

ያለው ተደራራቢ ጫና ታማሚዎች ህክምና እንዲያቋርጡ እንዳያረጋቸው አቶ ዘላለም ይሰጋሉ።

“ካንሰር ከጊዜ ጋር የሚሄድ በሽታ ነው። ቶሎ ታክሞ ውጤቱን ማሻሻል ካልተቻለ ወደከፋ ደረጃ ይደርሳል። በዛ ላይ ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ ያለው ማዕከል አንድ ጥቁር አንበሳ ነው። የቅዱስ ጳውሎስ እና የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎቹ (ጎንደር፣ ጅማ፣ ዓለማያ፣ሐዋሳ፣ ሀሮማያ) ማስፋፊያ ሲጠናቀቅ ነገሮች ይሻሻሉ ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ያስረዳሉ።

በኮቪድ-19 ምክንያት እስካሁን የካንሰር መድኃኒቶች እጥረት ባይፈጠርም፤ ለዓመታት ሲነሱ የነበሩት የመድኃኒቶች ውድነትና እንደልብ ያለመገኘት ጥያቄዎች አሁንም እንዳልተመለሱ አቶ ዘላለም ይናገራሉ።

ኮሮና
Banner

ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀት አለመቻሉ

ካንሰር የተባባሰ ደረጃ ላይ ሲደርስ ህክምናው የበለጠ አስቸጋሪ ስለሚሆን፤ ሰዎች በጊዜ ህክምና እንዲጀምሩ ይመከራል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የጡትና የማህጸን ጫፍ ካንሰር የመሰሉትን ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለዚህም ካንሰር ላይ የሚሠሩ ተቋሞችና ማኅበራት በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ያዘጋጃሉ። አሁን ግን መሰል መድረኮችን ለማሰናት አስቸጋሪ ነው። ይህም ካንሰር የሚመረመሩ ሰዎችን ቁጥር እንደሚቀንሰው አቶ ዘላለም ይናገራሉ።

“የጤና ባለሙያዎች አሁን ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ ሙቀት እየለኩ፣ ስለ ኮሮናቫይረስ ግንዛቤ እየሰጡ ነው ያሉት። እና በዚህ ወቅት ስለ ጡት ካንሰር ባወራ የሚሰማኝ የለም።”

በዚህ ምክንያት ቶሎ ተገኝተው ህክምናቸው ሊጀመር የሚገባ በሽታዎች እንደሚባባሱ አቶ ዘላለም ያስረዳሉ።

ዩናይትድ ኪንግደምን እንደምሳሌ ብንወስድ አገሪቱ በኮቪድ-19 ምክንያት እንቅስቃሴን ስትገታ የካንሰር ምርመራ ቆሟል። የአገሪቱ የካንሰር ማዕከል እንዳለው ይህ ማለት ቀድሞ በየወሩ ይገኙ የነበሩት 1,600 የካንሰር ህሙማን አሁን በሽታቸው አይታወቅላቸውም ማለት ነው።

በዩኬ ህሙማን ከቤታቸው እየወጡ ስላልሆነ መደበኛ ምርመራ ማቆማቸው ሌላው ስጋት ነው። አንድ የአገሪቱ የካንሰር ሐኪም እንደሚሉት፤ ሕክምና በመጓተቱ ሳቢያ ወደ 60 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ።

አቶ ዘላለም እንደሚሉት፤ አሁን ላይ ሰዎች የካንሰር ምልክት ቢያዩ ወደ ህክምና መስጫ ላይሄዱ፣ ሄደውም አፋጣኝ ምላሽ ላያገኙ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ለበሽታው ህክምና መሰጠት ያለበትን ጊዜ ያዘገየዋል።

“በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ መድኃኒትና ኬሞቴራፒ ውድ በሆነበት አገር፣ ራድዮቴራፒ በአንድ ማዕከል ብቻ ስለሚሰጥ ወረፋ ለሚጠበቅበት አገር በአፋጣኝ ህመሙ ተገኝቶ ህክምና መገኘት አለበት። ደረጃው በጨመረ ቁጥር አክሞ ለማዳን ከባድ ይሆናል።”

መፍትሔው ምንድን ነው?

ካንሰር በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በአገር ማኅበራዊ መዋቅርና ምጣኔ ኃብት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር አቶ ዘላለም ይናገራሉ። የካንሰር ህክምና በኮቪድ-19 ሳቢያ ለሚደርስበት ተጽዕኖ መፍትሔው ምንድን ነው? የሚለውን በቀላሉ መመለስ አይቻልም ይላሉ።

ችግሩ ውስስብ መሆኑ ግልጽ መፍትሔ ማስቀመጥን አስቸጋሪ ቢያደርገውም፤ በጤናው ዘርፍ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የካንሰር ህክምናን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው ይላሉ።

“የሆነ ተዓምራዊ መፍትሔ የለውም። ከማኅበረሰቡ ጀምሮ ብዙ ሥራ ያለበት ጉዳይ ነው። ሆኖም የጤና ውሳኔዎችና ፕሮግራሞች ካንሰርን ከግምት ማስገባት አለባቸው” ሲሉም ያስረዳሉ።