ጀርመን፡ በዓለም ለደንብና ለሥርዓት ተገዢ ዜጎች ያሏት አገር ማን ናት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከበርሊን ወደ ዱሱልዶፍ ከተማ በሚከንፍ ፈጣን ባቡር ውስጥ ነኝ። አጠገቤ ከተቀመጠው ወጣት ጋር ወግ ይዘናል። "እኔምልህ. . . . በጀርመንና በአሜሪካ ባሕል መካከል ምን ልዩነት አስተዋልክ?" አለኝ።
በዚህ መሀል አንዲት ሴትዮ በወንበሮች መሀል በመተላለፍያው ወደ መቀመጫ ወንበሯ እየተመለሰች ነበር። "እሽሽሽ. . . " ስትል እንደ ልጅ ተቆጣችን። ድምጻችሁን ቀንሱ ማለቷ ነው።
እኛ ያለንበት የባቡሩ ፉርጎ ድምጽ አይመከርም።
ምክሯን ቸል ብለን ወሬያችንን መሰልቀጥ ያዝን. . .
በድጋሚ ሞባይል ማነጋገር እንደማይፈቀድ የሚያመላክተውን ባቡሩ ፉርጎ ላይ የተለጠፈ ምልክት በጣቷ ጠቆመችን። በምሥል ከገባቸው በሚል. . .
አደብ አንገዛ ስንላት ደግሞ ወደኛ ጠጋ ብላ በሹክሹክታ "ድምጻችሁን መቀነስ ይኖርባችኋል" አለችን፣ በትህትና።
አጠገቤ ወደተቀመጠው ወዳጄ ዞር ብዬ ቀደም ሲል ለጠየቀኝ ጥያቄ መልስ እንዳገኘሁ ነገርኩት።
"በአሜሪካና በጀርመን ባሕል መካከል ያለው ልዩነት ይቺ ሴትዮ ናት።"
ምን ማለቴ እንደሆነ ሳይገባው አልቀረም።
የጀርመናዊያን ወግ አጥባቂነት፣ ደንብ አክባሪነት…
አራት ዓመት በጀርመን ስኖር "እባካችሁ ዝም በሉ" ያለችን ሴትዮ የምትወክለውን ኅብረተሰብ አይቻለሁ።
ፍጹም ለወግ-ባሕል፣ ለደንብ ሥርዓት ተገዢ ማኅበረሰብ ነው። በሁሉም ሁኔታና ከባቢ ሕዝቡ ሕግ አክባሪ ነው ማለት ይቻላል።
በዚያ ምድር ሥርዓት የሚባለው ነገር የትም አለ። በቃ በሕይወት ውጣ ውረድ ከደንብና ሥርዓት ውልፍ የለም። ምክንያቱም በጀርመን ባሕል ዝነኛው አባባል የትኛው ይመስላችኋል?
"ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው" የሚለው? አይደለም።
"መማር ያስከብራል፣ አገርን ያኮራል" የሚለው? አይደለም።
በጀርመን ዝነኛው አባባል. . . "Ordnung Muss Sein" (ሥርዓት ሊኖር ይገባል!) የሚለው ነው።
በቃ! የመላው ጀርመናዊያን ሕይወት የሚመራው በዚህ አባባል ነው ማለት ይቻላል። ከልጅ እስከ አዋቂ ለዚህ አባባል ይገዛል። ሥርዓት ሊኖር ይገባል! ሥርዓት ሊኖር ይገባል! ሥርዓት ሊኖር ይገባል!

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሥርዓት በምን ይገለጻል?
በጀርመን የቆሸሹና ንጹህ ጠርሙሶች በአንድ አይጣሉም። በጀርመን ምሽት ከ4፡00 ሰዓት በኋላ የሚረብሽ ድምጽ ማሰማት የለም።
በጀርመን ቀይ መብራት ከበራ ለምን ገጠር ውስጥ አይሁንም፣ ለምን እልም ያለ የገበሬ ማኅበር ያለበት አይንም. . . ለምን እግረኛ ሰው ቀርቶ እግረኛ-ወፍ መንገድ እየተሻገረች አይሆንም ትራፊክ የለም ብሎ ሕግ አይጣስም። አረንጓዴው እስኪበራ እግር ፍሬን ላይ ጠቆም ይደረጋል! ጡሩንባ ማንባረቅ የለም፤ ጸጥ ረጭ! ውልፍ ዝንፍ የለም!
በዚህ አገር አንድ ነገር ለማስፈጸም ከፈለጋችሁ ቀጥተኛ አካሄድ ነው ያለው።
መጀመርያ ቅጽ መሙላት፤ በቅጹ ላይ በትክክል ስምና አድራሻን መጻፍ፣ ከዚያ ቀጠሮ መያዝ ያስፈልጋል።
ቅጽ የሚሞላ ሰው መቼስ መሳሳቱ የት ይቀራል። ከተሳሳተ ተደውሎ ይጠራል። ቅጹን አስተካክሎ መሙላት ግዴታው ነው። ምክንያቱም በጀርመን "ሥርዓት ሊኖር ይገባል!"
የማርቲን ሉተር ውርስ?
ከላይ ከላዩ ሲታይ ጀርመን የደንብና ሥርዓት አገር ትመስላለች። ሁሉ ነገር እስትክክል ያለባት አገር ናት። ነገር ግን ጀርመን እንደሚባለው ሁሉ ነገር ደንብና ሥርዓት የያዘባት፣ በዚያ ላይ ደግሞ ለለውጥ እጅ የማትሰጥ አገር ናት ወይ? ብለን ከጠየቅን መልሱ አሉታዊ ሊሆን ይችላል።
ይህን ለመመለስ ወደ ማርቲን ሉተር ዘመን መመለስ ሳይኖርብን አይቀርም።
ሉተር ጀርመንም ሆነች ዓለም እንዴት ጌታ እየሱስ ክርስቶስን ማምለክ እንዳለባቸው ሥር ነቀል ለውጥ እንዳመጣ ሁሉ ባለፉት 500 ዓመታት የጀርመን "ሪፎርሚስቶች" በጀርመን ባሕል ላይ ትልቅ አሻራን አሳርፈዋል።
እንዲያውም ይህ ዝነኛ የጀርመኖችን የሕይወት መመሪያ የጻፈው ማርቲን ሉተር እንደሆነ ነው የሚነገረው። Ordunug Muss Sein Unter Den Leuten (በሕዝቦች መካከል ሥርዓት ሊኖር ይገባል!) እንዲል ማርቲን ሉተር።
ጀርመኖች የቢራ ፍቅራቸው (ለጠመቃም ለመጠጥም)፤ የመጽሐፍ ፍቅራቸው (ለመጻፍም ለንባብም)፣ የዳቦ ሱሳቸው (ለመጋገርም ለመግመጥም) አይጣል ነው።
በዓለም የተወደዱላቸው የአውቶሞቢል ዝርዝር ዘለግ ይላል፤ መርሴዲስ ቤንዝ፣ ቮልስዋገን፣ ቢኤምደብሊው፣ አውዲ፣ ፖርሸ የትም ቢኬድ የጀርመኖችን ጥንቁቅነት ያሳብቃሉ።
ከዚህ ሁሉ ልቆ የጀርመኖችን ፈጠራ መስመር ያስያዘ፣ ከጀርመኖችም አልፎ በዓለም ተጽእኖ የፈጠረ አንድ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት አለ። ባውሐውስ (Bauhaus) ይባላል። ስለእርሱ ትንሽ ካላልን ጀርመኖችን ማወቅ አንችልም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባውሐውስ ምንድነው?
ባውሐውስ የሥነ ጥበብና ሥነ ሕንጻ ትምህርት ቤት ነው። በቫይማር ጀርመን በ1919 በእውቁ አርክቴክት ዋልተር ግሮፒየስ አማካኝነት የተመሰረተ ትምህርት ቤት ነው።
ከዚያ በኋላ በወቅቱ ድንቅ የተባሉ ጥበበኞች ዋልተር ግሮፒየስ ዘንድ ተሰባሰቡ። የአንደኛው የዓለም ጦርነት ያንኮታኮተውን አገር መልሶ ለመገንባት ይህ ስብስብ ቆርጦ ተነሳ። አገር 'በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል!' እንዳለች ቁጠሩት።
ባውሐውስ በጀርመኖች ዘንድ በሥነ ሕንጻና ዲዛይን የፈጠረው ተጽእኖ የትየለሌ ነው።
ከዚህ ትምህርት ቤት የወጡ አዲስ ጽንሰ ሐሳብ መሞከር ያዙ።
ለምሳሌ ቦታ የሚይዝ ሕንጻ ሳይሆን ቦታ የሚፈጥር ሕንጻ መገንባት ያዙ።
ለምሳሌ ከፈትፈት ያሉና አንድ ሰው ቤቱ ወይም ቢሮው ውስጥ ሆኖ ደጅ ያለ ስሜት የሚፈጥሩ ኪነ ሕንጻዎች ያን ዘመን ነበር እየተለመዱ የመጡት። አሁንማ አውሮፓን ያጥለቀለቁት እነዚህ የኪነ ሕንጻ አሰራሮች ናቸው። በዚያ ዘመን ግን አዲስ ነበሩ።
ለምሳሌ የሕንጻ ጣሪያ ሲሚንቶ ኮንክሪት የሚሞላ ጠፍጣፋ ሜዳ እየተደረገ መሠራት ተጀመረ። ከዚያ በፊት ሾጣጣ ነበር።
የሕንጻዎች የፊት ገጽታ (Façade) ቀላልና ለዓይን ማራኪ ሆነው መገንባት ያዙ። የግንባታ የውስጥ ደረጃዎች ጥምዝ (spiral) መሆን ጀመሩ።
ከፈትፈት ያሉ ብርሃን እንዲዘልቅ የሚያደርጉ የመስታወት ግድግዳዎች፣ በብርሃንና በጥላ ዙርያ ውብ ገጽታ መፍጠርና መጠበብ የባውሐውስ ኪነ ሕንጻ ፍልስፍና ያመጣው ነው።
እንዴት እንዲህ ዓይነት የሥነ ጥበብ አብዮት ሊመጣ ቻለ ያልን እንደሆን አባት አርክቴክት ዋልተር ግሮፒየስን ማውሳት ይኖርብናል።
አርክቴክት ግሮፒየስ በጀርመን የፈጠረው ባውሀውስ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ሁሉም ተማሪዎች የሚወስዱት የወል ስልጠና አዘጋጀ፤ ይህን የወል ኮርስ ሳይወስዱ መመረቅ ቀረ።
በዚያው ትምህርት ቤት አዲስ የቅርጻ ቅርጽና የዕደ ጥበብ ስልት በስዊዛዊው አርቲስት ዮሐንስ ኢትን ተነደፈ። ተማሪዎች ፈጠራን መሠረት አድርገው እንዲሰሩ መሠረት ተጣለ።
ከዚያ ዘመን በኋላ በሥነ ጥበብ፣ በዕደ ጥበብ፣ በሥነ ሕንጻና በሌሎችም ፈጠራዎች ስለ ቀለም፣ ስለ ቅርጽ፣ ስለ ውበት መጨነቅ መጠበብ፣ መፈላሰፍ ባሕል እየሆነ መጣ።
ቀይ፣ ቢጫና ሰማያዊ መደበኛ ቀለሞች፣ አራት ማዕዘን፣ ክብና ሦስት ማዕዘን ቅርጾች የፈጠራ መንሸራሸሪያ የባውሃውስ መለያ ሆኑ።
ባውሃውስ በ1933 በሂትለር እስኪዘጋ ድረስ በመላው አውሮፓ ኪነ ሕንጻም ሆነ ሌሎች የሥነ ጥበብ ውጤቶች ላይ አሻራውን ጥሎ አልፏል። የጀርመኖች ቤትና ደጅ፣ አስተሳሰብና ድርጊት፣ ሁለመናቸውን ያሰመረውም ይኸው ትምህርት ቤት ነው ይባላል።
ጀርመኖች መጽሐፍ፣ ቢራና ዳቦ እንደሚወዱት ሁሉ የባውሀውስ ጥበብንም ይወዳሉ ይባላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ሥነ ሥርዓት ይከበር!' ማን የጀመረው ነው?
ሉተር በነገረ መለኮት ጉዳዮች በጻፋቸው ጽሑፎች ሕዝብ ለመሪዎች ይታዘዝ ይላል። 'ሥነ ሥርዓት ይከበር!' በሚል የጻፈው ግን ማኅበረሰብን በቀጥታ የሚመለከት ሳይሆን የሰው ልጅ በግሉ ሥርዓት ሊያከብር የሚገባው ፍጡር ነው ብሎ ያምን ስለነበረ ነው።
ከሉተር በኋላ ይሄ ሥነ ሥርዓት የሚለውን ሐረግ ዝነኛ ያደረገው ሰው የቫይማር ሪፐብሊክ የመጨረሻው ፕሬዝዳንት ፖል ቮን ሂደንበርግ ሳይሆን አይቀርም።
በ1934 ዝነኛው የታይም መጽሔት ሂደንበርግን በሽፋኑ ሲያወጣው ከእርሱ ፎቶ ስር የተጻፈው "ሥነ ሥርዓት ይከበር!" የሚለው እውቅ አባባሉ ነበር። ይህም እሱንም አባባሉንም ዝነኛ አደረጋቸው።
ክርስቲና ሮጀርስ የጀርመን ባሕል አጥኚና ተመራማሪ ናት። ይሄ ሥነ ሥርዓት በጥብቅ የማክበር ነገር ገና ድሮም የፕሩሲያ (የድሮዋ ጀርመን) ባሕል ነበር ትላለች።
ግዴታን መወጣት፣ ቀጠሮን አለማዛነፍ፣ ሐቀኝነት እና ጠንካራ ሠራተኝነት ድሮም የጀመርኖች ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ባሕል ነው።
ክርስቲና ይህን ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣን ሥነ ሥርዓት በተመለከተ ከጀርመኖች ጋር የቢዝነስ ሽርክና ለሚጀምሩ የሌላ አገር ዜጎችና ትልልቅ ኩባንያዎች ታማክራለች። ምክንያቱም ጀርመኖች ስንፍናን ላይታገሱ፣ ቸልተኝነትና እንዝህላልነት ቶሎ ሊያስቆጣቸው የሚችሉ ሕዝቦች ስለሆኑ ነው።
ይህ 'ሥርዓት ይከበር!' የሚለው ነገር ከየትም ይነሳ የት፣ ማንም ይጀምረው ማን፤ ዛሬ በጀርመኖች ደም ውስጥ የተቀበረ ጥብቅ ባሕል እንደሆነ ግን አያጠራጥርም።
ደስ የሚለው ነገር የዛሬዎቹ ጀርመኖች ስለ ሥነ ሥርዓት ሲያወሩ አይሰሙም። ውስጥ ውስጡን ተግባብተው ጨርሰዋልና። ይኖሩታል አንጂ አያወሩትም።
የጀርመን ባሕል አጥኚዋ ክርስቲን ይህ ሥርዓት አክባሪነት ለጀርመን ልጆች "በውሃ ቧንቧቸው በኩል የሚመጣላቸው የላም ወተት ነው" ስትል ትቀልዳለች።
ሥነ ሥርዓት ማክበርን ሁሉም የጀመርን ሕጻናት ገና ጨቅላ እያሉ ክፍላቸውን ከማጽዳት ይጀምራሉ። እቃ እቃ መጫወቻዎቻቸውን በሥነ ሥርዓት በማስቀመጥ ይቀጥላል። በዚያው የሕይወት ዘይቤያቸው ሆኖ ያድጋሉ።
ክርስቲን ነገሩን ስታጠቃልለው እንዲህ ትላለች።
"አንድ ሰው ሲናገር የቋንቋ ሰዋሰውን እያሰበ እንደማይናገረው ሁሉ ጀርመኖች ደንብና ሥርዓት ያከብራሉ እንጂ ስለ ደንብና ሥርዓት አያወሩም።"

የፎቶው ባለመብት, Joe Baur
ሁሉ ነገር ከሥርዓት መከበር ጋር ይያያዛል
ጀርመናዊያን የተረበሻችሁ መስሎ ከታየው "Alles in Ordnung?" ይሏችኋል፤ በጀርመን አፍ። ምን ማለት ነው? የአባባሉ መንፈስ ወደ እኛ ሲተረጎም "አማን ነው? ሁሉ ሰላም?" እንደምንለው ዓይነት መሆኑ ነው።
ነገር ግን የጀርመንኛው አባባል ቃል በቃል ስንፈታው "ሥነ ሥርዓት ተከብሯል?" እንደማለት ነው። አባባሉ አስቂኝ ይመስላል።
ከአስቂኝነቱ ባሻገር ግን የሚነግረን አንድ ቁም ነገር አለ። ለዚያ ሕዝብ "ሥነ ሥርዓት" የሚለው ቃል በቋንቋው ውስጥ ጭምር በምን ያህል ጠልቆ እንደገባ ነው።
ይኸው ቃል በጀርመን የደንብ ተቆጣጣሪዎች የደንብ ልብስም ላይ ተጽፏል።
ኦርድኖንግስአምት (Ordnungsamt) የሚባሉት የጀርመን የማኅበረሰብ ደንብ አስከባሪ ቢሮ መኮንኖች ናቸው። የእነዚህ መኮንኖች ሥራ ሥርዓት ማስከበር ነው።
ለምሳሌ አንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ ሙዚቃ የሚያስደልቅ ረባሽ ካለ የቅጣት ትኬት ይቆርጡለታል። እንዲሁም መኪና ማቆሚያ ውስጥ መኪናውን በአግባቡ ያላቆመውን ዋጋውን ይሰጡታል።
በጀርመን ውሻ ራሱ ስንት ጊዜ መጮኸ እንዳለበት ተደንግጓል ብትባሉ ታምናላችሁ? ጸጥታ መስፈን ባለበት ሰዓት በአንድ ጊዜ የእርስዎ ውሻ ከአስር ጊዜ በላይ ከጮኸ ጉድ ፈላ!
ይህ ማለት ግን ጀርመን ውስጥ ዝንፈት የለም ማለት ነው እንዴ? በፍጹም።
በመንገድ ላይ የተቀመጡ የቆሻሻ ቅርጫቶችን በጠረባ የሚያጎናቸው ሰካራም ጀርመናዊ መቼም አይጠፋም። ስካሩ ሲለቀው ግን "ሥነ ሥርዓት ይከበር!" እያለ ሊጮኽ ይችላል።













