ውዝግብ የፈጠረው የሌኒን ሐውልት ጀርመን ውስጥ ቆመ

የሌኒን ሐውልት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ጀርመን ውስጥ የሚገኘው ግራ ዘመም የፖለቲካ ፓርቲ ውዝግብ የፈጠረውን የሶቪየት ኮሚኒስት መሪ ቭላድሚር ሌኒንን ሐውልት አቆመ።

ብዙም ደጋፊ የሌለው የጀርመን ማርክሲስት ሌኒኒስት ፓርቲ ሐውልቱን ያቆመው በምዕራባዊዋ የጀርመን ከተማ ጌልሰንኪርቸን ውስጥ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ ፊት ለፊት ነው።

የከተማዋ ባለስልጣናት ፖርቲው የሌኒንን ሐውልት ለማቆም የሚያደርገውን ጥረት እንዲተው ለማድረግ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ "ለሌኒን ቦታ የለንም" በሚል መለያ ርዕስ ዘመቻ አካሂደው ነበር።

በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ ሕግ በመውሰድ ሐውልቱ እንዳይቆም ለማሳገድ ቢጥሩን ፍርድ ቤት የሌኒን ሐውልት ቅዳሜ ዕለት ተመርቋል።

የከተማዋ ከንቲባ ፍራንክ ባራኖወስኪ የሐውልቱን መቆም ተቃውመው ባሰራጯቸው የቪዲዮ መልዕክቶች ላይ በበርካታ አገራት ውስጥ ለዘመናት ቆመው በነበሩ ሐውልቶች ዙሪያ ክርክሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ጨምረውም "የቅርብ ዘመን አምባገነንን ሐውልት የመታሰቢያ ሐውልትን ማቆም ከባድ ድርጊት ነው። ምንም እንኳን በሚያሳዝን ሁኔታ ፍርድ ቤት ቢፈቅድም ውሳኔውን የምንቀበለው ቢሆንም ጥያቄ ግን አለን" ብለዋል።

የጀርመን ማርክሲስት ሌኒኒስት ፓርቲ ሊቀ መንበር ጋቢ ፌችነር ግን ሌኒንን "ነገሮችን ቀድሞ የሚረዳ በዓለም ታሪክ ተጠቃሽ የነጻነትና የዴሞክራሲ ታጋይ" ሲሉ መግለጻቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ሌኒን በጎርጎሳውያኑ 1917 የተካሄደው የሩሲያ አብዮት መሪ የነበረ ሲሆን በ1924 ህይወቱ እስኪያልፍ ድረስ አገሪቱን መርቷል።

ሌኒን ከህልፈቱ በኋላ በመላው ዓለም በደጋፊዎቹና በተቃዋሚዎቹ ዘንድ የኮሚኒዝም ሥርዓት መለያ ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል።

የሁለተኛውን የዓለም ጦርነትን ተከትሎ ጀርመን ለሁለት ተከፍላ የበርሊን ግንብ ከ30 ዓመታት በፊት እስኪፈርስ ድረስ ምሥራቃዊው ክፍሏ በሶቪየት ኅብረት በሚደገፈው የኮሚኒስት ሥርዓት ስትተዳደር ቆይታለች።

እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1957 የቀድሞዋ ቼኮዝላቫኪያ ውስጥ ተሰርቶ ጌልሰንኪርቸን ውስጥ በቆመው የሌኒን ሐውልት ዙሪያ የተነሳው ውዝግብ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በተለያዩ አገራት የጸረ ዘረኝነት እንቅስቃሴዎች ከባሪያ ንግድ ጋር የተያያዙ ሐውልቶች እንዲገረሰሱ ካቀረቡት ጥያቄ ጋርም ተያይዞ ነበር።