ኢኮኖሚ፡ የብር የምንዛሪ ዋጋ በገበያ መወሰኑ ምን ይዞ ይመጣል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብሔራዊ ባንክ የብር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የብር ዋጋ በገበያ ተመን እንዲወሰን ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ በሦስት ዓመታት ውስጥ ብርን ወደ ፍሎቲንግ ካረንሲሥርዓት (የገንዘብን ተመን በገበያ ዋጋ ላይ መመስረት) እንደምትሸጋገር ተገልጿል።
ለመሆኑ ፍሎቲንግ ካረንሲ ምንድነው? ኢትዮጵያ ፊቷን ወደዚህ ሥርዓት ማዞሯ ምን ያስከትላል? በንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ላይ የሚያሳድረሰው ተጽዕኖ ምንድነው? በተራው ዜጋ ህይወት ላይስ ምን አንድምታ አለው?
ለእኒዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡን የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑቱን እዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) እና አቶ ዋሲሁን በላይን ጠይቀናል።
የውጪ ምንዛሬ ሥርዓቶች
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ የተለያዩ አይነት የውጪ ምንዛሬ ሥርዓቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። የገንዘብን ዋጋ በገበያ መሠረት መተመን (Floating Exchange Rate)፣ የገንዘብ ዋጋ መጠን በማዕካለዊ ባንክ የሚወሰንበት (Fixed Exchange Rate) እና ማዕከላዊ ብንኩ እንደ አስፈላጊነቱ ጣልቃ የሚገባበት (Managed Floating Exchange Rate) ይጠቀሳሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ሁሉም አይነት የውጪ ምንዛሪ ሥርዓቶች የራሳቸው የሆነ አውንታዊና አሉታዊ ውጤቶች እንዳላቸው ይስማማሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ፤ አገራት የተወሰነ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓትን ስለመረጡ ብቻ ውጤታማ ይሆናሉ ማለት አይደለም ይላሉ።
እንደምሳሌም ሳዑዲ አረቢያ ምንዛሪው በማእከላዊ ባንክ የሚወሰን የተመን ሥርዓትን እየተከተለች ውጤታማ መሆኗን በማስታወስ፤ "ዋናው ቁምነገሩ የውጪ ምንዛሬ ሥርዓቱን በነጻ ገበያ ወይም በመንግሥት የሚወሰን አይደለም። የአገር ውስጥ ምርታማነትን በማሳደግ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማሳደግ ነው" ይላሉ።
በገበያ ከሚወሰነው ምንዛሪ ኢትዮጵያ ምን ታተርፋለች?
ብር በአሁኑ ወቅት ከሚገባው በላይ ዋጋ እንዳለው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ስለዚህም የብር ዋጋ በገበያ ወደሚተመንበት ሥርዓት ሲሸጋገር ዋጋው አሁን ካለው እንደሚቀንስ ወይም በብር እና በዶላር መካከል ያለው ልዩነት እንደሚሰፋ ይታመናል።
አቶ ዋሲሁን የብር የመግዛት አቅም ሲቀንስ ኢትዮጵያ የምታመርታው ምርት ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ርካሽ ይሆናል ይህም የአገር ውስጥ አምራቾችን ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል ይላሉ።
"ለምሳሌ 1 የአሜሪካ ዶላር 25 ብር ነው ብለን እናስብ። አንድ አሜሪካዊ 1 ዶላር ይዞ ቢመጣ፤ 25 ብር ዋጋ ያለውን እቃ በ1 ዶላር ይገዛናል። የብር የመግዛት አቅምን በቀነስን ቁጥር ከውጪ የሚመጣ ሰው በርካሽ ዋጋ እንዲገዛን እያደረግን ነው። የዚህ እሳቤ ምንድነው ብዙ ምርት ለገበያ ባቀረብን ቁጥር ብዙ ዶላር እናገኛለን ማለት ነው።"
አቶ ዋሲሁን በሌላ በኩል ደግሞ የዚህን ተገላቢጦሽ እንመልከት ይላሉ። "የ1 ዶላር ወደ 33 ከፍ ተደረገ ብለን እናስብ። አሁን የ1 ዶላር እቃ ለመግዛት 33 ብር መያዝ ያስፈልገናል። በፊት ግን 25 ብር ነበር የሚያስፈልገው" ብለዋል።
በዚህም ይህ የሚያሳየን ብር ከዶላር ጋር ያለውን ልዩነት በሰፋ ቁጥር ኢትዮጵያዊ እቃ ከውጪ ለመግዛት ይወደድበታል። የአገር ውስጥ ምርትን ግን ውጪ ለመሸጥ ተወዳዳሪ ይሆናል። ይህ ማለት የአገራችን የውጪ ምንዛሪ ክምችት ያድጋል፤ ምርትና ምርታማነት ይጨምርልናል ሲሉ ሊኖረው የሚችለውን ውጤት ይናገራሉ።
ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል ይችላል
በአሁኑ ጊዜ ብር ከሚገባው በላይ ዋጋ እንደተሰጠው የሚናገሩት እዮብ (ዶ/ር)፤ የብር የዋጋ በገበያው መሠረት ሲተመን ከውጪ አገራት ገንዘብ ጋር የሚኖረው ልዩነት እንደሚሰፋ ይገልጻሉ። ለምሳሌ አንድ የአሜሪካ ዶላር ዛሬ ላይ በባንኮች 35 ብር የሚመነዘር ከሆነ፤ በትክክለኛው የገበያ ዋጋ ይተመን ቢባል አንድ ዶላር እስከ 45 ብር ድረስ ሊመነዘር ይችላል።
"በዚህም ወደ በገበያ ዋጋ በሚወሰን የምንዛሪ ተመን ስንሸጋገር የብር ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ ሊያሽቆለቁል ይችላል፤ ይህም የዋጋ ግሽበትን ይከሰታል። ሌሎች እክሎችም ሊከሰቱ ይችላሉ" ይላሉ እዮብ (ዶ/ር)።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ወደዚህ የውጪ ምንዛሬ ሥርዓት ሽግግር ሲደረግ ከሚያጋጥሙ አሉታዊ ተጽዕኖዎች መካከል ዋነኛው የዋጋ ግሽበት ሊሆን ይችላል ይላሉ።
"ለምሳሌ ከሰሞኑ መንግሥት የ1 ዶላር ምንዛሬን ከ32 ወደ 35 ብር ከፍ ብሏል። ይህ ከ5 እና 6 ወራት በኋላ እስከ 24 በመቶ ድረስ በእቃዎች ላይ ጭማሪ ያመጣል" ሲሉ ይናገራሉ።
አለማየሁ (ዶ/ር) በሱዳን የተከሰተውን እንደምሳሌ ያነሳሉ። 1 የአሜሪካ ዶላር 29 የሱዳን ፓወንድ ሳለ ሱዳን የውጪ ምንዛሬ ሥርዓቷን በገበያ ወደ ሚወሰነው አሰራር መቀየሯን ያስታወሳሉ።
"በዚህም ሱዳን ውስጥ የ1 ዶላር ምንዛሪ 48 የሱዳን ፓወንድ ገባ። በሕገ-ወጡ ገበያ ደግሞ 1 ዶላር 58 የሱዳን ፓወንድ ደረሰ። በዚህን ጊዜ ሰዎች በሱዳን ፓወንድ ላይ እምነት አጡ" በዚህም ሁሉም ሰው ወደ ኤቲኤም በመሄድ ገንዘብ ማውጣት ላይ ተረባረበ፤ ባንኮች ደግሞ የሚከፍሉት ማጣታቸውን አለማየሁ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
"ከዚያም ችግሩ ተባብሶ ሄዶ እንደ ዳቦ ባሉ መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ ጭማሪ ታየ። ተቃውሞ ተቀስቅሶ አሁን ለመጣው የመንግሥት ለውጥ ምክንያቶች መካከል አንዱ ሆነ " ይላሉ።
የውጪ ምንዛሬ ስርዓት ከ3 ዓመት በኋላ ይቀየራል መባሉ 'ግራ አጋቢ ነው'
ብሔራዊ ባንክ የብር ዋጋ በገበያው የሚተመነው በሦስት ዓመት ውስጥ ነው ማለቱ ይታወሳል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሬ ሥርዓቷን በዚህ ጊዜ ውስጥ መቀየር ይቻላታል?
እዮብ (ዶ/ር) በበለጸጉ አገራት ዘንድ የውጪ ምንዛሬ ሥርዓታቸውን በሦስት ዓመት ውስጥ የመቀየር ልምድ እንዳለ አውስተው፤ በብሔራዊ ባንክ በኩል ግን ቅድሞ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እያሉ "ከሦስት ዓመት በኋላ የተባለው ከምን ተነስቶ እንደሆነ 'ግራ አጋቢ' ነው" ይላሉ።
በኮቪድ-19 ምክንያት የዓለምና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እድገት እየተጓተት መሆኑን ያስታወሱት እዮብ (ዶ/ር)፤ በወረርሽኙ ሳቢያ የተወሰነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፍል ክፉኛ መጎዳቱን ይናገራሉ።
"ከእነዚህ ጫናዎች ሳንላቀቅና የኮቪድ-19ን ሙሉ ጫና ሳንረዳ ከአሁኑ ሦስት ዓመት ብሎ መወሰን ለእኔ ግራ አጋቢ ነው። በበኩሌ የምቀበለው ነገር አይደለም" ሲሉ ይሞግታሉ።
እዮብ (ዶ/ር) እንደሚሉት ወደዚህ አይነት የውጪ ምንዛሬ አስተዳደር ለማምረት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጉ በማውሳት፤ ኢትዮጵያ ወደዚህ ከመሸጋገሯ በፊት "የማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ያስፈልጋል፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ያስፈልጋል፣ በቂ የውጪ ምንዛሬ ክምችት መኖር ይኖርበታል እንዲሁም የንግድ ሚዛን ጉድለት መጥበብ ይኖርበታል" ሲሉ ይመክራሉ።
እንደ እዮብ (ዶ/ር) አመለካከት በገበያ ወደሚወሰን የምንዛሪ ሥርዓት ከመሸጋገራችን በፊት የዋጋ ግሽበት መጠንን ወደ አንድ አሃዝ ማምጣት "እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።"
"በገበያው ላይ በቂ የሆነ የውጪ ምንዛሪ መኖር ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በቂ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያም የውጪ ምንዛሪ የምታገኘባቸውን መንገዶች መጨምር ይኖርባታል። ከውጪ የሚላክ ገንዘብ እንዲጨምር ማበረታቻ ማድረግ፣ ቱሪዝምና ኤክስፖርት ማደግ ይኖርባቸዋል" ይላሉ።
ይህን የውጪ ምንዛሬ ሥርዓት ለመተግበር የተማረ ሰው ኃይልና ተቋማዊ ለውጥ የግድ እንደሚልም እዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) ያሳስባሉ።
አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ግፊት
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ገንዘቧ በገበያ ዋጋ እንዲተመን ግፊት እንደሚያሳድሩ ይነገራል።
እዮብ (ዶ/ር) ለዚህ አንዱን ምክንያት ሲያስረዱ፤ አይኤምኤፍ ከተመሰረተባቸው ምክንያቶች አንዱ የዓለም አገራት የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ እንዲረጋጋ ለማድረግ በመሆኑ ነው።
"በእነሱ ፍልስፍና የምንዛሪ ተመን የተረጋጋ የሚሆነው ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነጻ ሲሆን ነው። ምክንያቱም ምንዛሪ እንደማንኛውም ሸቀጥ ዋጋ አለው። እንደ ሌሎች ሸቀጦች ሁሉ ይህ ዋጋ በገበያ ኃይል መወሰን አለበት ብለው ያምናሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።
አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልከው ምርት በላይ ከውጪ የምታስገበው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ይህንን ልዩነት ለማጥበብ የብር ዋጋ በገበያ ቢወሰን በተሻለ መልኩ የውጪ ምንዛሪ እንዲገኝ ይረዳል የሚል እሳቤ ስላለ አገሪቱ ወደዚህ ሥርዓት እንድትገባ ጫና እንደሚደረግ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ አለማየሁ (ዶ/ር) እንደሚሉት በኢትዮጵያዊያን ላኪዎች እንደችግር ከሚቀርቡት መካከል የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት ትልቁ ራስ ምታት አይደለም ባይ ናቸው።
"እኔ ከመቶ በላይ ላኪዎችን አነጋግሬ የደረስኩበት ነገር፤ ለእኛ አገር ላኪዎች መሠረታዊ ችግር የሆነው የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት፣ የመሬትና የፋይናንስን አቅርቦት ችግር፣ ሙስናና ጉምሩክ ላይ ያለው ውጣ ውረድ ነው እንጂ የዶላር እጥረት የላኪዎች ትልቁ ችግር አይደለም" ይላሉ።
"ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት በትይዩ ገበያ [ጥቁር ገበያ] እና በባንክ መካከል ያለው ልዩነት እንዲሁም ወደ አገር በሚገባውና ወደ ውጪ በሚላከው መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ነው።"
በእነዚህ መካከል ልዩነቱ የሰፋበት ዋነኛ ምክንያት ወደ ውጪ የሚላከው ምርት ስላላደገ እንደሆነ የሚናገሩት አለማየሁ (ዶ/ር) "በእኔ ስሌት ወደ አገር በሚገባውና ከውቺ በሚመጣው መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ወደ ውጪ የምንልካቸው ምርቶች በአማካይ በዓመት 20 በመቶ ለስምንት ተከታታይ ዓመት ማደግ ይኖርበታል" ይላሉ።
ስለዚህም የመንግሥት ትኩረት መሆን ያለበት "ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች የሚጨምሩበትን መንገድና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት አምራቾችን ማበረታት ላይ ነው" ይላሉ አለማየሁ (ዶ/ር)።
አዋጭ ነው? የባለሙያዎቹ ጠቅላላ ግምገማ
ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በኋላ የብር የዋጋ ተመን በገበያ እንዲወሰን ብታደርግ ያዋጣታል? የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ማጠቃለያ ሃሳብ የሚከተለው ነው።
እዮብ (ዶ/ር) - የምንዛሪ ሥርዓት መቀየርና በገበያ ዋጋ መወሰን እንዳለበት አምናለሁ። አካሄዱ ግን ቀስ በቀስ በሂደት መሆን አለበት። ብሔራዊ ባንክ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ መከናወን ያለባቸው ነገሮችን መሰራት ይኖርበታል፤ ለዚህ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያና ተቋም ያስፈልጋል።
አለማየሁ (ዶ/ር) - ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። የውጪ ምንዛሪ ሥርዓታችንን ከመቀየራችን በፊት ቀድሞ መከናወን ያለባቸው የቤት ሥራዎች አሉ።
አቶ ዋሲሁን - በጠቅላላው አዋጭ ነው ብዬ አስባለሁ። ሥርዓቱ በራሱ ጊዜ ወደ ዚያው እየወሰደን ይገኛል። በመጪው ሦስት ዓመታት ውስጥ የሚጠበቅብንን የቤት ሥራዎች ማከናወን የምንችል ከሆነ የሚየቀሩ ነገሮች ቢኖሩም ከሦስት ዓመታት በኋላ የብር ዋጋ በገበያ እንዲተመን ማድረጉ ትክክለኛ አካሄድ ነው።















