“የኑሮ ውድነቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል”

ብር የሚቆጥር ሰው
የምስሉ መግለጫ, የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ ነው

ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሆነውና መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሰዎች ሊመደብ የሚችለው ግለሰብ በተለይ የኮቪድ-19 ወረረሽኝ ስጋትን ከመጣበት ከወርሃ ሚያዚያ አንስቶ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር ህይወቱ ላይ የሚጨበጥ ተፅዕኖ ማምጣቱን ለቢቢሲ ይገልፃል።

"ሃገር ውስጥ የሚመረቱ እንደ ሽንኩርት፣ ጤፍ፣ ቲማቲም የመሳሰሉት ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፤ ከዚያ ባሻገር ከውጭ የሚገቡ እንደ መዋቢያ ምርቶች፣ አልባሳት የመሳሰሉትም ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል" የሚለው ይሄው ግለሰብ ምናልባትም ከዓለም አቀፍ ወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የንግድ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው፣ እንደ ወትሮውም በቀላሉ መጓጓዝ ባለመቻሉ የአቅርቦት እጥረት ማጋጠሙ ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ግምቱን ሰንዝሯል።

"ሽንኩርት በአስራዎቹ ብር ደረጃ ነበር የምንገዛው፥ አሁን ወደ አርባ ብር ደርሷል፤ ቲማቲምም እንደዚሁ ከፍ ብሏል፤ እንደዚሁ ሃያ ስምንት ብር ሃያ ዘጠኝ ብር [ገደማ] እየተሸጠ ነው ያለው በኪሎ" የሚለው ይህ ሰው ከዚህም የተነሳ እርሱና በማኅበራዊ ከባቢው የሚያውቃቸው ሌሎች ሰዎች አጠቃቀማቸውን ለማስተካከል መገደዳቸውን ይናገራል።

የፍቼ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ዘውዲቱ አሰፋም ከአዲስ አበባው ነዋሪ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያላት። የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሆኑን ለቢቢሲ ስትገልጽ፤

"ለምሳሌ ሽንኩርት ከ45 እስከ 50 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ሁሉም ነገር ጨምሯል። ጤፍ ከ4300 በላይ እየሆነ ነው። ዘይት ድሮ መንግሥት ያቀርብ ነበር፤ አሁን ግን አያቀርቡም፤ ስለዚህ ከነጋዴ እየገዛን ነው። ዋጋው ጨምሯል። የመንግሥት ሰራተኛ የሆነ፣ ደሞዙ አነስተኛ የሆነ፣ ቤተሰብ ያለው በጣም እየተቸገረ ነው።" ብላለች።

የኑሮ ውድነቱ መናር በአኗኗሩ ላይ ያመጣውን ለውጥ የሚገልፀው የአዲስ አበባ ነዋሪ ". . .በምንጠቀማቸው ምግቦች ውስጥ ቲማቲም የምናዘወትር ከሆነ እርሱን እንተዋለን ማለት ነው፤ ሽንኩርትም የምንገዛውን እየቀነስን ሄደናል"፤ ስለዚህ "የምታገኘው ገቢና ለፍጆታዎችህ የምታወጣው ካልተመጣጠነልህ ፍጆታውን ወደ መቀነስ ብሎም ወደ ማቆም ነው የምንሄደው" ብሏል።

ይኼው ሰው የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ እርግጥ የሆነበት ሰሞን በርካታ ሰዎች፣ የተለያዩ ምርቶችን በጅምላ ይሸምቱና ያከማቹ እንደነበር አስታውሶ፣ በወቅቱ አጋጣሚውን ለመጠቀም በፈለጉ አንዳንድ ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ይጠቅሳል። "እኛ አገር የተለመደው ነገር ደግሞ ዋጋ አንድ ጊዜ ከፍ ካለ በኋላ ተመልሶ የመውረድ ዕድሉ በጣም አናሳ ስለሆነ" በዚያው ከፍ ብሎ ቀርቷል ይላል።

የአርባምንጭ ነዋሪ የሆኑ ሌላ ግለሰብ ለቢቢሲ ሲናገሩ ገበያው "እሳት ነው" ይላሉ። ዋጋውን ለማነጻጸር ሩቅ መሄድ አልፈለጉም፤ "በቅርቡ እንኳ ቲማቲም እንገዛ የነበረው 20 ብር ነው አሁን ግን 30 ገብቷል" ካሉ በኋላ ሽንኩርት ደግሞ 30 ብር መግባቱን፣ ድንች በኪሎ 15 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 150 መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ነጋዴዎችም እንደ ከዚህ ቀደሙ ደፍረው የሚገዙ ደንበኞቻቸው እየቀነሱ መምጣታውን ለቢቢሰ ተናግረዋል።

በላሊበላ የሚኖሩት ሌላው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰብ ኑሯቸው የተመሰረተው ከተማዋን ለመገብኘት በሚመጡ ቱሪስቶች ላይ እንደነበር ተናግረው አሁን ግን በኮቪድ-19 ምክንያት ጎብኚ በመጥፋቱ ኑሯቸው ፈተና ውስጥ መውደቁን ለቢቢሲ አልሸሸጉም።

ከዚህ ቀደም 30 እና 40 ብር ይገዙት የነበረውን ሽንኩርት አሁን 120 ብር እንደሚሸጥም አስረጅ በመጥቀስ ተናግረዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ውሰጥ የሚታዩ ሰዎችና የምግብ ምርቶች
የምስሉ መግለጫ, ከቅርብ ወራት ወዲህ በምግብ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መጨመር ታይቷል

"ጤፍ ከ4000 ብር በላይ ገብቷል" በማለትም ኑሮ ከእለት ወደ እልት እየከበደ መምጣቱን ለቢቢሲ በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነው አስረድተዋል።

ኮሮናቫይረስና የዋጋ ንረት

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ጉቱ ቲሶ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሸቀጣሸቀጥ ዋጋ መጨመሩን ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በኮቪድ-19 እና በተጓዳኝ ችግሮች ምክንያት ምርትና አቅርቦት ላይ መስተጓጎል በመፈጠሩ መሆኑን ያስረዳሉ።

ምሁሩ አክለውም ከየካቲት ወር ጀምሮ ይህ መከሰቱን እና እስካሁን መቀጠሉን ይናገራሉ።

ዶ/ር ጉቱ በተለይ ደግሞ የአለማቸችን የሸቀጣሸቀጥ እቃዎች ዋነኛ አቅራቢ ቻይና በኮሮናቫይረስ ክፉኛ መጎዳቷ ምርቶችን ማስተጓጎሉንና በዚህም የተነሳ የዋጋ ንረት መከሰቱን ገልፀዋል።

"አቅርቦት ሲቀንስ ዋጋ ይጨምራል" የሚሉት ባለሙያው፤ በተፈጠረው የአቅርቦት እጥረት ገበያ ውስጥ ያለውን መቀራመት በመፈጠሩ የምርት ዋጋ መናሩን አብራርተዋል።

ሌላኛው ምርቶችን ከውጪ አገራት ገዝቶ ለማምጣት የውጭ ምንዛሬ በማስፈለጉ እና በበቂ ሁናቴ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት አለመቻል ለዋጋ ግሽበቱ መናር አንዱ አስተዋጽኦ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት አምራቾች የግብአት እጥረት ስለሚገጥማቸው የዋጋ ንረት ይከሰታል የሚሉት ዶ/ር ጉቱ፣ አምራቾች የማምረት ወጪያቸው ሲጨምር አብሮ የምርት ዋጋ ይጨምራል ይላሉ።

አምራቹ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከትራንስፖርትና ከማምረት ጋር የተገናኘ የግብአት አቅርቦት እየተገታና እጥት እየተፈጠረ በመምጣቱ ለምርት እጥረቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልፀዋል።

"ግብአት አቅርቦት ቀነሰ ማለት፣ የግብአት ዋጋ ጨመረ ማለት ነው" በማለትም ናገራሉ።

የማምረቻ ዋጋ ሲጨምር፣ በተዘዋዋሪ አምራቹ ዋጋውን ወደ ሸማቹ እንደሚያዞር የሚያስረዱት ዶ/ር ጉቱ፤ ዋጋው ወደ ተጠቃሚ ሲዞር ምርቱ ላይ ጭማሪ ያሳያል ሲሉ ይተነትናሉ።

ከእነዚህ በተጨማሪ የስርጭት መሰተጓጎል መኖሩን ባለሙያው ጨምረው አስድተዋል።

"በአንድ ቦታ የተመረተ ምርት በሚፈለግበት ወቅት ወደ ተለያየ የአገሪቱ ክፍል ማሰራጨት ሲያቅት፣ እጥረት ስለሚፈጠር ለተጨማሪ ወጪ ይዳረጋል፤ የዋጋ ጭማሪ ይከሰታል።"

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የሰላምና መረጋጋት ጥያቄ ትልቅ ፈተና ውስጥ መውደቁን በማስታወስ፣ ይህ ሁሉ በምርት ሰንሰለት፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በምርት ስርጭቶች ላይ ትልቅ መስተጓጎል መፍጠሩን ይናገራሉ።

በሰላም እና መረጋጋት እጦቱ ፋብሪካዎች ምርታቸውን መቀነሳቸውን፣ ምርት ስርጭት ላይ የተሰማሩም መስተጓጎል ገጥሟቸዋል ሲሉ ይገልጻሉ።

መኪናዎች ጭነት ጭነው መንገድ ላይ ከአንድ ቀን በላይ ተስተጓጉለው መቅረት፣ ለተጨማሪ ወጪ እና ኪሳራ ሲዳርጋቸው በተዘዋዋሪ ሸማቹ ላይ የምርቱ ዋጋ ከተገቢው በላይ ዋጋ እንዲጫን እንደሚያደርጉ ጨምረው ያስረዳሉ።

እነዚህ ነገሮች በጥቅሉ ሲታዩ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም አገልግሎቶችና አቅርቦቶች ላይ የዋጋ ንረት እንደሚያሳዩ ዶ/ር ጉቱ ገልፀዋል።

በአንድ እንቅብ ላይ የተቀመጡ አትክልቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምግብ እህሎች ንረት

ለዋና ዋና ከተሞች የምግብ ፍጆታ ምርቶች የሚመጡት በከተሞቹ አቅራብያ ከሚገኙ የክልል ከተሞች መሆኑን በማስታወስ እነዚህ የግብርና ምርቶች ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ የዋጋ ንረት ማሳየታቸውን ገልፀዋል።

እነዚህ የፍጆታ እቃዎች አሳሳቢ በመባል ደረጃ ዋጋቸው እየጨመረ ነው የሚሉት ምሁሩ፣ ለዋጋ መናር ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሲያስረዱም እነዚህ የእለት ፍጆታ ምርቶች ( እንደ ጥራጥሬ ያሉት) ለገበያ የሚቀርቡት ባለፈው አመት የተመረቱ መሆናውን በመጥቀስ ነው።

ባለው አመት በተለያየ የአገሪቱ ክፍል አካባቢዎቹ የነበሩበት ሁናቴ የነበረውን ሁኔታም በማስታወስ፣ ለማምረት፣ ለመሰብሰብ፣ ለማሰራጨት አስቸጋሪ በሆነ ሁናቴ ውስጥ ማሳለፋቸውን ይጠቅሳሉ።

በዚህ የተነሳ የምርት ማሽቆልቆል ተከስቶ ዘንድሮ ለገበያ ሲደርስ የዋጋ መናር መፈጠሩን ያስረዳሉ።

ባለፉት ወራት የተከሰተውንም በተመለከተ ሲያስረዱም፣ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዳሴ ግድያ በኋላም ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ምርቶች ትልቅ መስተጓጎል እንደገጠማቸው ያብራራሉ።

በተጨማሪም ነጋዴዎች ባለፈው አመት የገዙት ምርት እንኳ ቢሆን በእንዲህ አይነት ወቅት ዋጋ ከመጠን በላይ ጨምረው እንደሚሸጡ ሸማቾችም በገፍ ገዝው እንደሚያከማቹ ይህም ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልጻሉ።

ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው አትዮጵያዊ መደበኛ ባልሆነ ስራ ውስጥ ተሰማርቶ፣ ከእጅ ወደአፍ ገቢ እንደሚያገኝ የሚናገሩት ምሁሩ፤ በዚህም ለበርካታው ኢትዮጵያዊ ኑሮን ማክበዱን ይገልፃሉ።

ገንዘብ ያለውም ቢሆን የፍጆታ እቃዎች ዋጋ በናረበት ቁጥር ያለውን ገቢው በአጠቃላይ ወደ ሚመገበው ነገር ለማዞር ይገደዳል ይላሉ።

ይህም ቁጠባን፣ የወደፊት የማደግ ተስፋውንና ጥረቱን እንደሚያመክን ገልፀው፣ ይህ እንደ ግለሰብ ቢሆንም እንደ አገር ማህበረሳባዊ እድገትንም ፈተና ውስጥ እንደሚጥል ይገልፃሉ።

ምን መደረግ አለበት

እንደ ዶ/ር ጉቱ ከሆነ ለዋጋ ግሽበቱ መፍትሄ ለመስጠት ችግሩ ከምን መነጨ የሚለውን መለየት አስፈላጊ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ለምጣኔ ሃብት ችግር የምጣኔ ሃብት መልስ መስጠት ያስቸግራል የሚሉት ምሁሩ፣ የችግሩ መንስኤ ምጣኔ ሃብታዊ ሳይሆን ማህበራዊ አልያም ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ የተከሰተን የዋጋ ንረት በፍጥነት በሽታውን በቁጥጥር ስር በማዋል፣ ህብረተሰቡ ወጥቶ ሰርቶ መግባት እንዲችል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። ይህን በፍጥነት መቆጣጠር ካልተቻለ የምጣኔ ሃብቱን ቀውስ እያባባሰው እንደሚሄድ ይናገራሉ።

ሌላው በየዓመቱ ያለው የሰላም መደፍረስ ምክንያቱ ተጠንቶ እውነተኛ፣ አሳታፊ እና ግልጽ የሆነ ውይይት ተደርጎ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ይመክራሉ።

በሶስተኛ ደረጃ እንደ ህዝብ ያሉትን ፖሊካዊ ብሶቶችና ጥያቄዎችን የምንገልፅበት መንገድን ቆም ብሎ መመልከት ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ።

ሁል ጊዜ የምጣኔ ሃብት ተቋማትን በማውደም፣ ምርትና ምርታማነትን በማስተጓጎል ብቻ ሳይሆን ሌሎች በተዘዋዋሪ ጫና መፍጠር የተፈለገው አካል ላይ ጫና መፍጠር የሚያስችሉ አማራጮችን መመልከትና መፈተሽ ተገቢ መሆኑን ያስታውሳሉ።

ካልሆነ ግን አሁን የዋጋ ንረቱ እየሄድንበት ያለው ፍጥነትና መንገድ ከምጣኔ ሃብት አንፃር ሲታሰብ አገሪቷን መጥፎ ደረጃ ላይ እያደረሰ መሆኑን ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ኮሮና
Banner