የቤት ውስጥ ጥቃት፡ "በትዳሬ ውስጥ ባሪያ የሆንኩ ያህል ይሰማኝ ነበር"

የቤት ውስጥ ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሶሚያ ባሳር፣ ህንዳዊት ናት። ዕድሜዋ 36 ሲሆን ራሷንም "ከቤት ውስጥ ጥቃት የተረፍኩኝ" በማለት ትገልፃለች።

ከአገሯ፣ ከቤተሰቧ፣ ከባህሏና ማንነቷ ተነቅላ በእንግሊዝ ውስጥም በስደተኝነት ትኖራለች።

ሶሚያ ወደ ሲኦልነት ተቀየረብኝ የምትለው የትዳር ህይወቷ የተጀመረው በ19 ዓመቷ ነው።

በሙምባይ ከተማ ነው ከእንግሊዛዊ ባሏ ጋር የተጋቡት። በወቅቱም ይህ ነው የሚባል ትውውቅ አልነበራቸውም።

"ስለጋብቻ የነበረኝ ሃሳብ ብትንትኑ ወጣ። ባርያው እንደሆንኩ ያህል ይሰማኝ የጀመረው ወዲያው ነበር" ብላለች።

ቤት ውስጥ እንደ ሠራተኛ፣ ልጆች ጠባቂ፣ ምግብ አብሳይ እንዲሁም እሷ እንደምትለው "የልጆች መፈልፈያ መሳሪያ አድርጎ ነው ያየኝ" ትላለች።

በዚሁ አልተገታም ሁኔታዎች እየባሱ ከፍተኛ አካላዊ ድብደባ፣ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ያደርስባት ጀመር እንዲሁም ገንዘብ ይከለክላት ነበር።

"ይህ ነው በማይባል ሁኔታ ከፍተኛ ጥቃት ያደርስብኝ ነበር። ሙሉ ህይወቴ በእርሱ ቁጥጥር ስር ነበር" ትላለች።

ለዓመታትም ያህል እንዲህ አይነት ጥቃቶችንና በደሎችን የተቋቋመችው ለልጆቿ ስትል ነበር። "ጎሽ ለልጆቿ ስትል ተወጋች" እንደሚባለው ባሏም ትተሽ ከሄድሽ ልጆችሽን በጭራሽ አታያቸውም፣ እነጥቅሻለሁ በማለት ያስፈራራት ስለነበር በዚህ "ሲኦል" ባለችው ትዳር ቆየች።

ከአስር ዓመታት በላይ በስቃይ ከኖረች በኋላ ባሏን ለመፍታት ወሰነች፤ እንዳለችውም አደረገች። ፍርድ ቤቱም ሦስት ልጆቿ ለእሷ እንዲሰጡ ወሰነ።

ነገር ግን የቀድሞ ባሏ ሦስት ልጆቿን ይዞ ወደ እንግሊዝ ፈረጠጠ። ይህም ሁኔታ በቃላት መግለፅ በማትችለው ሁኔታ ልቧን ሰበረው።

ለወራት ያህልም ልጆቿን ለማስመለስ ስትታገል የቆየች ሲሆን ተስፋ በቆረጠችበትም ወቅት፤ ሳውዝሆል ብላክ ሲስተርስ የተሰኘና የቤት ውስጥ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ የሚያደርግ የእርዳታ ድርጅት ተባበራት።

ሶሚያ ባሳር ከልጆቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Somiya Basar

የምስሉ መግለጫ, ሶሚያ ባሳር ከልጆቿ ጋር

ያለእነሱም እርዳታ ወደ እንግሊዝም መምጣትም ሆነ ልጆቿን ማየት እንደማትችልም ትናገራለች።

ሶሚያ ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች ጥበቃ ከሚያደርገው የመንግሥት አካል ስደተኛ በመሆኗ የገንዘብም ሆነ የሥነ ልቦናዊ ድጋፍ ማግኘት አልቻለችም።

"ይሄ ሁኔታ የበለጠ ተጋላጭ ያደርገኛል፤ አጥቂዬም ይሄንን ተጋላጭነቴን በመገንዘብ በተለያዩ መንገዶች ጥቃት ሊያደርስብኝ ይችላል" በማለት ትናገራለች።

በቅርቡም ያለችበትን ሁኔታ ለማስረዳትም በእንግሊዝ ፓርላማ ቀርባ እሷና እሷን የመሰሉ ሴቶች የሚደርስባቸውን መከራ አስረድታ ነበር።

በእንግሊዝ ያለው ሥርዓት ስደተኛ ሴቶችን የሚያገልና ጥቃት የሚደርስባቸውም ድጋፍን ማግኘት የማይችሉበት መሆኑንም ምስክርነቷን ሰጥታለች።

በቅርቡም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መንግሥት እንዲያፀድቅም እየጠየቁ ነው።

የትኛውም የእድሜ፣ የመደብ ደረጃ ቢሆኑ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እርዳታ ሊያገኙ ይገባል። በሚኖሩበት አገርም የዜግነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ባያገኝም፤ ስደተኛ ቢሆኑ እንኳን በማለት ተሟጋቾች ዘመቻቸውን ጀምረዋል።

ተሟጋቾቹ በዋናነት እየጠየቁትም ያሉት የፓርላማ አባላቱ ስደተኛ ሴቶችን ከቤት ውስጥ ጥቃት መከላከልና መጠበቅ የሚያስችለውን ረቂቅ ሕግ እንዲያፀድቅ ነው።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ስደተኞች የመኖሪያ ሁኔታቸው ያልተረጋጋ በመሆኑ ከመንግሥት የሚገኘውን የገንዘብ፣ ቤት እንዲሁም ሌሎች ድጋፎች ማግኘት አልቻሉም።

የስደተኞችን ጉዳይ በበላይነት የሚያየው ቢሮም በበኩሉ ይህ ረቂቁ ሕግ መፅደቅ ከቻለ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው። የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ የቀረበው ረቂቅ ሕግ ከሰሞኑም ይቀርባል።

በዚህ ዓመትም 2 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብም ጥቃት የደረሰባቸውና ከመንግሥት ድጋፍ ማግኘት ለማይችሉ ሴቶች ድጋፍ ለሚያደርጉ ድርጅቶች እንዲሰጥ ተወስኗል።

ነገር ግን ይህ ገንዘብ እንዳለ ሆኖ ስደተኞች የሚጠበቁበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ሕጋዊ ማዕቀፍ ዋና መሰረታዊ ነገር እንደሆነ እነዚሁ ተሟጋቾች ይናገራለ።

"ከየትም ይምጡ ከየት፤ ሁሉንም ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ልንጠብቃቸው ይገባል" በማለት 'ስቴፕ አፕ ማይግራት ውሜን' የተሰኘው የተሟጋቾች ቡድን ገልጿል።

ሶሚያ ባሳር ከልጆቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Somiya Basar

የምስሉ መግለጫ, ሶሚያ ባሳር ከልጆቿ ጋር

ሶሚያ በዚህ ትስማማለች ይህ ረቂቅ ከፀደቀ ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ለማንኛውም ሴቶች ከለላ ይሰጣልም የሚል ተስፋ አላት።

"እርዳታን ለማግኘት ዋነኛ መስፈርት መሆን ያለበት ጥቃት የደረሰባት ሴት ብቻ መሆን ነው፤ ከየትኛውም አገር የመጣን ብንሆን እንኳን ዋናው ነገር ከለላ ሲያስፈልገን ያንን ማግኘት አለብን" ብላለች።

'ድብደባን ማምለጥ'

ከቶተንሃም የመጣችው ሜሪ (ትክክለኛ ስሟ አይደለም) የባለቤቷ ቤተሰቦች ከእሷ በተጨማሪ ሁለት ልጆቿ ላይ አካላዊ ድብደባ ሲያደርሱባት መሸሻ መደበቂያ አጥታ ነበር።

እሷም እንደ ሶሚያ ስደተኛ ከመሆኗ አንፃር ከመንግሥት ተቋማት እርዳታን ማግኘት አልቻለችም።

በመጨረሻም ጥቃት ከሚያደርሱባት ቤተሰቦች ማምለጥ የቻለችው 'ሲስታህ ስፔስ' በተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት ነው።

ከነበረችበት የሰቆቃ ህይወት አምልጣ ብትወጣም በነበራት ስደተኝነት ወረቀት ምክንያት ቤትም ሆነ ሌላ ድጋፍ ከመንግሥት ሊሰጣት አልቻለም።

"ቤት እንኳን ማግኘት ብችል አንድ ሸክም ከጀርባዬ ቀለል ይለኝ ነበር" ትላለች።

በአሁኑ ወቅት ቤት እንኳን ማግኘት ባትችል በእርዳታ ድርጅቱ አማካኝነት ይደርስባት ከነበረው የስድብ ውርጅብኝና ስድብ መዳን ችላለች።

"ካለ ሲስታህ ስፔስ እዚህ መድረስ አልችልም ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን ድጋፍ የሚሹ በርካታ ሴቶች አሉ። ሁኔታዎች በዚህ ሊቀጥሉ አይገባም፤ መቀየር አለባቸው" በማለትም መልዕክቷን አስተላልፋለች።

በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰራው ዓለም አቀፉ ድርጅት አምነስቲ የዩናይትድ ኪንግደም ቅርንጫፍ ሠራተኛ የሆኑት ኬት አለን እንደሚሉት በርካታ ጥቃት የሚደርስባቸው ስደተኛ ሴቶች ማምለጫ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል ይላሉ።

በርካቶች መሄጃ እንደሌላቸው ስለሚያስቡም ኑሯቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከተውም ያስረዳሉ።

"ብዙ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እርዳታ ለማግኘት ወደ ፖሊስ በሚሄዱበት ወቅት ስደተኞች ስለሆናችሁ ምንም ልናደርግ አንችልም ብለው መልሰዋቸዋል" ይላሉ።

እርዳታ ካለማግኘት በተጨማሪ ለእርዳታ ወደ ፖሊስ ቢሄዱ ሊታሰሩ ወይም ከአገር ሊባረሩ እንደሚችሉ ካላቸው ፍራቻ የተነሳ በተቻለ መጠን ወደ ፖሊስ አይሄዱም ብለዋል።

ነገር ግን የስደተኞችን ጉዳይ የሚያየው የመንግሥት ቢሮ ቃለ አቀባይ በበኩላቸው "ጥቁሮችም ሆኑ እስያውያን፤ የትኞቹም ስደተኞች አስከፊ የሆነውን የቤት ውስጥ ጥቃት ሊደርስባቸው አይገባም" ብለዋል።