ሕንድ፡ “ጠቅላይ ሚንስትራችን እባክዎን ወንዶች ቤት ውስጥ ሥራ እንዲያግዙን ንገሩልን”

ፊርማ የማሰባሰብ ሂደቱን የምትመራው ሱምባራ ጎሽ
የምስሉ መግለጫ, ፊርማ የማሰባሰብ ሂደቱን የምትመራው ሱምባራ ጎሽ

በሕንድ የቤት ውስጥ ሥራ አታካች ነው። ጽዳት፣ ልብስ ማጠብ፣ ማብሰል ወዘተ. . .

አብዛኞቹ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች የቤት ሠራተኛ ይቀጥራሉ። አሁን ግን በአገሪቱ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የእንቅስቃሴ ገደብ ስለተጣለ ሠራተኞች ከቤታቸው ስለማይወጡ፤ ሴት የቤተሰብ አባላት የቤት ውስጥ ሥራ ጫናን ብቻቸውን ለመሸከም ተገደዋል።

ይህን በመቃወም ሴቶች ፊርማ እያሰባሰቡ ነው። የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡም ተጠይቋል።

ንቅናቄው እየተካሄደ ያለው ቼንጅ [ለውጥ] በተባለ ድረ ገጽ ነው። መጥረጊያ ላይ ‘ሴቶች ብቻ የሚገለገሉበት ነው እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ተጽፎ በድረ ገጹ ይታያል።

ወንዶች ለምን ልብስ አያጥቡም? ለምን አያበስሉም? ለምን ኃላፊነታቸውን አይወጡም? የሴቶቹ ጥያቄ ነው።

ፊርማ የማሰባሰብ ሂደቱን የምትመራው ሱምባራ ጎሽ ትባላለች። ቤት ሆና የቢሮ ሥራ ከመሥራቷ ጎን ለጎን ታበስላለች፣ ታጸዳለች፣ ልበስ ታጥባለች።

“ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉም ሕንዳዊያን ወንዶች በቤት ውስጥ ሥራ የድርሻቸውን እንዲወጡ እንዲያሳስቡልን እንፈልጋለን” ትላለች።

እስካሁን 70,000 ሰዎች ፊርማቸውን አኑረዋል።

"ስለጫናው ስናገር ሰዎች የቤት ውስጥ ሥራውን ተይው አሉኝ”

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በሕንድ ከተማ ቀመስ አካባቢዎች ሴቶች በቀን 312 ደቂቃ ሳይከፈላቸው ሲሰሩ፤ ወንዶች ግን ለ32 ደቂቃ ብቻ ይሠራሉ።

ሙምባይ የምትኖረው ሱምባራ፤ ፊርማ ማሰባሰብ የጀመረችው የራሷን እንዲሁም በአካባቢዋ ያሉ ሴቶች የሚደርስባቸውን ጫና መነሻ አድርጋ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች።

“የቤት ሥራ የሴት ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል። አበስላለሁ፣ አጸዳለሁ፣ አልጋ አነጥፋለሁ፣ ልብስ አጥፋለሁ፣ በቃ ሁሉንም ነገር እሠራለሁ” ትላለች።

የባንክ ሠራተኛው ባለቤቷ አንዳችም እገዛ አያደርግላትም። ሁለት ልጆቿ አልፎ አልፎ ይረዷታል።

ሱምባራ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ነው የምትሠራው። እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ከተጣለ ወዲህ ከቤት የቢሮ ሥራዋን ብትቀጥልም፤ በቤት ውስጥ ሥራ ስለምትጠመድ እንደቀድሞው በቢሮ ሥራዋ ውጤታማ መሆን አልቻለችም።

“በጣም ስለሚደክመኝ የቢሮ ሥራዬን በአግባቡ መሥራት አልቻልኩም። ስለጫናው ስናገር ሰዎች የቤት ውስጥ ሥራውን ተይው አሉኝ።”

ከዚያም ለሦስት ቀን ቤት ውስጥ ምንም ሳትሠራ ዋለች። ቤቱ ባልታጠበ እቃ እና በቆሸሸ ልብስ ተሞላ። ባለቤቷና ልጆቿ መቆጣቷ ገብቷቸው እቃና ልብስ አጠቡ፣ ቤትም አጸዱ።

“ባለቤቴ አሁን አሁን ያግዘኝ ጀምሯል። የቤት ውስጥ ሥራ ምን ያህል ጫና እንደሚያሳድር ተረድቷል። ሆኖም ግን በርካታ ወንዶች የቤት ውስጥ ሥራ እየሠሩ አላደጉም።”

ሕንድን ጨምሮ በሌሎችም አባታዊ ሥርዓት በሰፈነባቸው ማኅበረሰቦች ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ የቤት ውስጥ ሥራ እንዲያከናውኑ ይጠበቃል።

የቤት ውስጥ ሥራ የሴቶች ብቻ ግዴታ እንደሆነ ይታመናል። ሴቶች መደበኛ ሥራ ሲይዙ የቤት እና የቢሮ ሥራን ደርበው እንዲሠሩም ይገደዳሉ።

“ልጅ ሳለሁ ቤት ውስጥ እኔ ብቻ ነበርኩ የምሠራው። ወንድሜ ለራሱ እንኳን ምሳ አያቀረብም ነበር” ስትል ፓሊቪ ሳረን የተባለች ሴት ጽፋለች።

አፓሳና ባሀት የተባለች ሴት ደግሞ “የቤት ውስጥ ሥራ የሴት ኃላፊነት ተደርጎ ይወሰዳል። ወንዶች እናግዝ የሚሉትም ወላጆቻቸው በአቅራቢያቸው ከሌሉ ነው” ብላለች።

ኦክስፋም እንደሚለው፤ ሕንድ ሴቶች በየቀኑ ከሦስት ቢሊዮን ሰዓታት በላይ ያለ ክፍያ ይሠራሉ። ይህ ወደ ገንዘብ ሲቀየር በትሪሊዮን ሩፒ የሚቆጠር የአገር ውስጥ ምርት ይሆናል።

ኦክስፋም እንደሚለው፤ ሕንድ ሴቶች በየቀኑ ከሦስት ቢሊዮን ሰዓታት በላይ ያለ ክፍያ ይሠራሉ።
የምስሉ መግለጫ, ኦክስፋም እንደሚለው፤ ሕንድ ሴቶች በየቀኑ ከሦስት ቢሊዮን ሰዓታት በላይ ያለ ክፍያ ይሠራሉ።

"ለምን ስለ ጾታ እኩልነት አይናገሩም?”

ሱምባራ ታዳጊ ሳለች እናቷ እና አክስቶቿ በቤት ውስጥ ሥራ ደፋ ቀና ሲሉ ስታይ፤ “እኔ ሳድግ እንደነሱ አልሆንም” ትል ነበር።

ስታገባ በቤቷ እኩልነት የሰፈነ ቢመስልም፤ እውነታው ግን የሥራ ጫና ሙሉ በሙሉ እሷ ላይ መውደቁ ነው።

“እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ሲጣል፤ እኔ ላይ የተጣለው የቤት ኃላፊነት በግልጽ መታየት ጀመረ” ትላለች።

በምትኖርበት አካባቢ ያሉ ሴቶችም ተመሳሳይ እሮሮ ያሰማሉ። ለጠቅላይ ሚንስትሩ አቤቱታ ለማሰማት የወሰኑትም ለዚሁ ነው።

አንዳንድ ሴቶች አጋራቸው መሥራት እንደሚጠበቅበት ላያስቡም ይችላሉ። “የማበስለውን ምግብ ቅሬታ ሳያሰማ ነው የሚበላው፤ እንዴት ያለ መልካም ወንድ ነው” የሚሉም አሉ።

ሱምባራ እንደምትለው ችግሩን በቀላሉ መቅረፍ ያልተቻለው እነዚህ ወንዶች የቅርብ ሰው ስለሆኑ ነው።

“የገዛ አባትሽን፣ ወንድምሽን፣ ባልሽን እንዴት ትወቅሻለሽ? ከባድ ይመስላል። ግን ጉዳዩ የኔም ጭምር ስለሆነ ከመናገር ወደኋላ አልልም” ትላለች።

ባለቤቷ ፊርማ እያሰባሰበች መሆኑን ሲሰማ ደግፏታል። ጓደኞቹ ግን እንደተሳለቁበት ትናገራለች። “ቤት ውስጥ ባለቤትህን ብታግዝ ኖሮ ለሞዲ ደብዳቤ አትጽፍም ነበር” ብለውታል።

ባለቤቷ “አብዛኞቹ ወንዶች ከባለቤታቸው ይልቅ ሞዲን ይሰማሉ” ሲል ለጓደኞቹ ምላሽ ሰጥቷል።

ሱምባራ ፊርማ በማሰባሰቧ የወቀሷትም አልታጡም። ጠቅላይ ሚንስትሩን “በተራ ጉዳይ” እያስቸረች ነው ያሏትም አሉ።

“አንዳንድ ሰዎች የሕንድ ሴቶች መሥራት አለባቸው ብለው ጽፈውልኛል። አዎ መሥራት አለብን። ግን ወንዶችስ?” ስትል ትጠይቃለች።

ለመሆኑ ሞዲ በቀጣይ ንግግር ሲያደርጉ ስለ ቤት ውስጥ ሥራ ክፍፍል ያወራሉ ብለሽ ትጠብቂያለሽ? የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ ለሱምባራ ቀርቦላት ነበር። እንዲህ ስትል መልሳለች፦

“ሞዲ በርካታ ሴት ደጋፊዎች አሏቸው። ስለዚህ ለሴቶች ስለሚጠቅም ጉዳይ መናገር አለባቸው። ክረምቱ ሲገባ ስለ ብርድና ስለ ሳል አውርተዋል። ታዲያ ለምን ስለ ጾታ እኩልነት አይናገሩም?”