ሴቶች የሚመሯቸው ኩባንያዎች የተሻለ አትራፊ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመለከተ

ከወንዶች ጋር በመንገድ ላይ ጎልታ የምትታይ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሴቶች በአመራርነት የሚሳተፉባቸው ተቋማት በወንዶች ብቻ ከሚመሩት የተሻለ ስኬታማ እንደሚሆኑ አንድ ጥናት አመለከተ።

ጥናቱ የተደረገው ለንደን ውስጥ በሚገኙ ኩባንያዎች ላይ ነው። 350 ግዙፍ ኩባንያዎች በዚህ ጥናቱ ተካተዋል። የጥናቱ መደምደሚያም አንድ ነገር አሳየ።

በከፍተኛ አመራር ላይ ከሚቀመጡ ሦስት ሰዎች ቢያንስ አንዷ ሴት በሆኑባቸው ኩባንያዎች ውስጥ የተሻለ ምርት፣ የተሻለ ትርፍ ከመታየቱም ባሻገር በሴቶች የሚመሩ ኩባንያዎች ደንበኞቻቸውን ፍላጎት ማሟላት እንደቻሉ ተደርሶበታል።

ጥናቱ እንዳስቀመጠው በወንድ ሥራ አስፈጻሚዎች ከሚመሩ ኩባንያዎች ይልቅ በሴቶች የሚመሩት የ10 እጥፍ ብልጫን አሳይተዋል፤ በትርፍም በምርትም።

የሚገርመው ጥናቱ ላይ ከተሳተፉ 350 ኩባንያዎች ውስጥ 14ቱ ብቻ ናቸው በሴት ሥራ አስፈጻሚ የሚመሩት።

ጥናቱን ያደረገው ዘፓይፕላይን የተሰኘ ድርጅት ነው። ከጠቅላላ ኩባንያዎቹ ውስጥ ደግሞ 15 እጅ የሚሆኑት በከፍተኛ አመራር ደረጃ አንዲት ሴት እንኳ አልተወከለችባቸውም።

የጥናት ቡድኑ መሥራች እንዳረጋገጡት ሴት ሥራ አስፈጻሚዎች የሚመሯቸው መሥሪያ ቤቶች የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ነቅሶ በማውጣትና ፍላጎትን በማሟላት የሚስተካከላቸው አልተገኘም።

ከእነዚህ መቀመጫቸውን ለንደን ካደረጉ ኩባንያዎች መካከል ሴቶች በአመራር የሌሉባቸው ድርጅቶች 1.5 በመቶ የትርፍ ህዳግ ብቻ ነበር ያስመዘገቡት። ሴቶች በርከት ብለው በአመራር ደረጃ የሚገኙባቸው ኩባንያዎች በበኩላቸው የትርፍ ህዳጋቸው 15.2 በመቶ ያህል ደርሶ ታይቷል።

ጥናቱ ከዚህ ሌላ በፋይናንስ ዘርፍ የሚገኙ ኩባንያዎች 96 ከመቶ የሚሆኑት በወንዶች እንደሚመሩ ደርሶበታል። ሴቶች በአመራር ደረጃ ከማይቀመጡባቸው ኩባንያዎች ውስጥ የኮንስትራክሽንና የችርቻሮ ንግድ ዋንኞቹ ሆነው ተገኝተዋል።

የጥናት ቡድኑ መሥራች እንዳሉት በችርቻሮ ዘርፍ 80 ከመቶ ሴቶች ተሳታፊ ቢሆኑም በአመራር ደረጃ ግን ድርሽ አይሉም ወይም ዕድሉ አይሰጣቸውም።

በጥናቱ ላይ የተሳተፉት የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒሰትር ቴሬሳ ሜይ እንደተናገሩት በእንግሊዝ ሴቶች በአመራር ደረጃ እንዳይሳተፉ የሚያደርጋቸው አንድም የረባ ምክንያት የለም።

"እያንዳንዱ በእንግሊዝ ኩባንያ ያለ ወንድ ሥራ አስፈጻሚ የቦርድ ስብሰባው ላይ ከ10 ተሰብሳቢዎች 9ኙ ወንዶች መልሰው ሲያፈጡበት ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። ስለሴት ልጁም ማሰብ አለበት" ብለዋል ቴሬሳ ሜይ።